ክተት የአገር ልጅ ዘለቀ ጀምበሩ (ከቶሮንቶ)

ተነስ ጎጃሜ ታጠቅ ጎምጎፋ
አይንህ እያየ አገር አትጥፋ
ንገር ለወሎ ይስማ ኢሉባቡር
አሩሲ ሀረር ወለጋ ጭምር
ክተት ይጠራ ይሰብሰብ አገር
አቅራራ ሸዋ ሸልል በጌምድር
ጀግንነት እማ ከአባት አልነበር

ታጠቅ ሲዳሞ ከፋ አስከ ባሌ
የዚያ ጀግና ዘር መጥቷል አመሌ
ከትግሬም ይምጣ አገር ወዳዱ
እንበል ጠርቀምቀም ይፈላል ጉዱ
ይታወጅ ሸዋ ከመናገሻው
መድኃኒቱ ነን ከእነማርከሻው
ጃሎ በል ፋሲል ዛሬ አለ ነገር
እንዴት በባንዳ ትታመስ አገር

ሸኙ መርቁን ሽማግሎቹ
ስንቄን ቋጥሩልኝ ወይዛዝሮቹ
ወንድም ጋሼ ና ታጠቅ እንውጣ
አበራይተነው በድል እንምጣ
ጉብሎች ደግሞ አምባው ላይ ውጡ
እምቢልታ ንፉ ይበርታ ምጡ
እስከመቼ ነው መለማመጡ
ሳንገላገል የት አለ ጌጡ

አምጣልኝ እና ጥመድ በሮቹን
ዳልችን እና ጠቋቁሮቹን
መጣሁ የአንቺ ልጅ ላንቺ ወሮታ
ከተጠመደ የማይፈታ
ቀን አበራይቶ ይወቃል ማታ

ማን ጥጋበኛ ማን ጦም አዳሪ
የትኛው ደፋር ማንኛው ፈሪ
ማንኛው ሽንታም ማን ባለ ሱሪ
አንደኛው ገዳይ ሌላው ቀባሪ
ሁኖ እስከመቼ ምድር መስክሪ

ይኼ ቅጥረኛ የባንዳ ውላጅ
አገር አልቦ ነው እንዳለው ወዳጅ
አማልዱኝ ጎበዝ ይበል ይቅርታ
ቀኑ ሳይጨልም ሳያመነታ
ምከሩት ዘመድ ያላችሁ ሁሉ
ቃታ ሳይሳብ ሳይጠፋው ውሉ
ኧረ ምከሩት ምክር ይበልጣል
አጉል ሰው መናቅ ውርደት ያመጣል

እኖር ብየ እንጂ ችየ ባገሬ
ማየት አልሻም ተደፍሮ ክብሬ
ዘራፍ የዚያ ልጅ የዚያ ጎፈሬ
የነብይ ወንድም የእነ ሽብሬ
ለወዳጁ ማር ለጠላቱ አውሬ
በቃኝ ከእንግደህ ልውረድ ጉራሬ
ኧረ ጃሎ በል ጉድ አለ ዛሬ

ጉድ አለ ዛሬ እምቢ በል እንጃ
ሀሞት ይበልጣል ከእርሱ ጠብ-መንጃ
መታገስ ፈሪ ካስመሰለማ
አገርን ማፍቀር ካስገደለማ
በቃኝ እንግዲህ እንዴት ላቅማማ
መጣሁ ልታደግ ስሚኝ እማማ

ጠላቷ ይቅዘን ፋሲል ያቅራራ
ይቀስቀስ ቴዎድሮስ ይምጣ ከቋራ
አለኝ ቀጠሮ ራስ ዳሸን ላይ
ጠላት ሊያላዝን እኔ ላበራይ
አለኝ ቀጠሮ ሰቲት ሁመራ
መሃላየ ነው እርሱን ላሳራ
ማዶ ለማዶ አነጣጣሪ
ጋራ አዘልሎ ወንዝ አሻጋሪ
አሻግረህ በለው እስኪንጠራራ
ደግሞ ለእምየ ለአንዷ ባንዴራ

ትዕግስቴ በዝቶ ካስጠቃኝ መቻል
ይኼ ቅጥረኛ ለጠብ ይመቻል
ውረዱ እንውረድ በቁልቁለቱ
አይዘሩ በቀል ከመጣበቱ
የባንዳ ውላጅ የደደቢቱ
አላርፍ ካለ ከእነ ትዕቢቱ
አበራይተነው ደፍተን በአናቱ
ወይ ያኔ … ወይኔ ትበል እናቱ

እክት-ት-ት-ት-ት-ት-ት