የመለስ ዜናዊ አገዛዝ መዋቅራዊ ዘረኛነትን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥም እያስፋፋ እንደሆነ ተነገረ

የኢትዮጵያን የመንግስት ስልጣን ከአንድ ዘር በተውጣጡ ጥቂቶች ቁጥጥር ስር ያዋለው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የዘር አድሎ ምህዳሩን ከጊዜ ወደጊዜ እያሰፋ ሄዶ በአሁኑ ሰዓት መዋቅራዊ ዘረኛነትን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ እያሰፈነ እንደሆነ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለሪፖርተራችን ገልጸዋል።

አየር መንገዱን ወደ ከፍተኛ የስኬት ደረጃ እንዳወጡ የሚነገርላቸው የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ግርማ ዋቄ በሰኔ 2001 በፓርላማ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ በዘር ላይ የተመሰረተ የሰራተኛ ቅጥር እንዲፈጽም በአገዛዙ ጫና እየተደረገበት እንደሆነና በዚህም ምክንያት አደጋ እንዳንዣበበት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ግርማ ዋቄ ባለፈው መስከረም ከስራቸው ተወግደው የትግራዩ ገዢ ቡድን አባል ተወልደ ገብረማሪያም መሾሙ ይታወቃል።

በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰሩ ምንጮች ለሪፖርተራችን እንደገለጹት፥ ድርጅቱ ቀስ በቀስ የአንድ ቤተሰብ ንብረት እየመሰለ ሄዷል። ከቁልፍ ባለስልጣናቱ ጀምሮ እስከ በረራ አስተናጋጆች ድረስ ሆን ተብሎ የገዢው ቡድን አባላት እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።