የጂቡቲ መንግስት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ከወያኔ በማግኘቱ ላይ እምነት የለውም ተባለ

የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ከኢትዮጵያ ለመግዛት በወያኔ ቁጥጥር ስር ካለው የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጋር ኮንትራት ተፈራርማ የነበረችው ጅቡቲ በአገዛዙ ብቃት ላይ እምነት እንደሌላት ከአሜሪካ ኤምባሲ የወጣ የሚስጥር መልክት አጋልጧል።

ዊኪሊክስ በተባለው ድረ-ገጽ ላይ የወጣው እና በጅቡቲ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ የተላከው መልክት፤ ጂቡቲ ከወያኔ አገዛዝ ጋር የተፈራረመችው ውል ላለባት የሃይል ቀውስ መፍትሄ ይሆነኛል ብላ ተስፋ አድርጋ ቢሆንም፤ ወያኔ በገዛ አገሩ እያሳየ ያለው የብቃት ጉድለት ለአገሪቱ ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። የጂቡቲ የኢነርጂ ሚኒስቴር ለአሜሪካው አምባሳደር እንደነገሩት፥ በኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ጋር የተያያዙ ግንባታዎች መዘግየት እና በድርቅ የሚሳበበው የሃይል እጥረት አገራቸውን ለስጋት ዳርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ በወያኔ ቁጥጥር ስር ያለው የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ገና አቅርቦቱ ሳይሳካለት ከጅቡቲ እና ከሱዳን ጋር በተዋዋለው ውል ላይ የዋጋ ጭማሬ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ ታውቋል። ምንም እንኳ ባለስልጣናቱ ገንዘብ ከአገር ማሸሻቸውን ቢቀጥሉም፤ አገዛዙ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ቀውስ እንዳለበት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በከፍተኛ የብቃት ጉድለት የሚተዳደር ድርጅት ሲሆን፤ አሰራሩን ለማሻሻል ባለመቻሉም መፍትሄ ይሆናል በሚል ሶስት ቦታ ለመከፋፈል በዝግጅት ላይ እንዳለ ካፒታል የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ዘግቧል። አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፥ “ይህ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” የሚባለው አይነት ነው ፤ መሰረታዊው ችግር ሳይቀረፍ የመዋቅር ለውጥ ምንም መፍትሄ አያመጣም ብለዋል። የአገሪቱ የተማረ የሰው ሃይል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ቁጥር መሰደዱን እስከቀጠለ ድረስ፣ በሁሉም የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታየው የብቃት ጉድለት እና አስተዳደራዊ በደል እየከፋ እንጂ እየተሻሻለ አይሄድም ሲሉ አስረድተዋል።