የትግራዩ ገዢ ቡድን በርካታ ንግድ ቤቶችን ዘጋ፤ ህዝቡ “ይህ ለኛ አይደለም” እያለ ነው
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ በገዛ እጁ ለፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ነጋዴዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እና ኢኮኖሚውን ከአንድ ዘር በተውጣጡ ምርጦች ቁጥጥር ስር ለማኖር የሚያደርገውን ሩጫ እንደገፋበት ከሰሞኑ የወጡ ዘገባዎች ገለጹ።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ብቻ በአስርት የሚቆጠሩ ንግድ ቤቶች መዘጋታቸውን ሪፖርተራችን ገልጿል። ሬውተርስ የዜና አገልግሎት በበኩሉ እስከ ሐሙስ ድረስ 103 የችርቻሮ ንግድ ቤቶች እንደተዘጉ ዘግቧል። ነጋዴዎቹ የተቀጡት ባለፈው ሳምንት የተዋወቀውን የዋጋ ማስተካከያ በስራ ላይ አላዋላችሁም በሚል ነው።
ንግድ ቤቶችን የመዝጋቱ ዘመቻ እንደሚቀጥል እና አዋጁን በስራ ላይ አውለው ያልተገኙ ነጋዴዎችም የገንዘብ እና የእስር ቅጣት እንደሚደረግባቸው ለማወቅ ተችሏል።
አዲሱ አዋጅ የጅምላ ነጋዴዎችን እንጂ እነሱን እንደማይመለከት ተነግሯቸው የነበሩት ቸርቻሪዎች፤ የዋጋ ማስተካከያው ከተላለፈ በኋላ ሌላው ቀርቶ የሂሳብ ማወራረጃ ማሽናቸውን ወይም “ካሽ ሬጂስተሮችን” እንዲያስተካክሉ ጊዜ አልተሰጣቸውም። በሱቆቻቸው የሞሏቸውን እቃዎች ከጅምላ ነጋዴዎች የገዙት በቀድሞው ዋጋ በመሆኑም በርካቶች ከፍተኛ ኪሳራን እንደሚቀምሱ ይጠበቃል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የአገሪቱ የዋጋ ንረት እየጨመረ እንደሚሄድ ቀድሞውኑ ሲተነብዩ የቆዩ ሲሆን፤ አገዛዙ ያወጣው የዋጋ ገደብ ህገ-ወጥ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረግ ቁሳቁሶችን የባሰ እንደሚያስወድድ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ያናገራቸው ነዋሪዎች አገዛዙ የወሰደው እርምጃ ህዝብ እንዲጠቅም የታለመ አይደለም ይላሉ። በመለስ ዜናዊ እርምጃዎች ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳላቸው የተናገሩት አንድ ግለሰብ፣ አዲሱ አዋጅ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ የተላለፈ እንደሆነና እነሱ ለፈጠሩት ችግር ህዝቡ ነጋዴዎችን እንዲወቅስ ለማድረግ ነው ብለዋል። የዋጋ ገደቡ ለተወሰነ ጊዜ ይረጋ እንደሆን እንጂ በዘላቂነት ሊቀጥል ይችላል ብለው እንደማያምኑም ለዘጋቢያችን ነግረዋል።