የወያኔ አገዛዝ በኑሮ ውድነት ምክንያት ህዝብ ይነሳብኛል የሚል ስጋት አለበት ተባለ

የኑሮ ውድነት ብዙሃኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ለረሃብ እና ለችጋር እየዳረገ ባለበት፣ የዋጋ ንረት እየጨመረ እንደሄደ ዘገባዎች አመልክተዋል። የታህሳስ ወር የምግብና የሌሎች ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ከህዳር ወር ጋር ሲነጻጸር ከአራት በመቶ በላይ ጭማሬ ማድረጉን ሬውተርስ የዜና አገልግሎት በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ያለውን የእስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጠቅሶ ዘግቧል። ይህ የአራት በመቶ ጭማሬ ደግሞ ቀድሞውኑ ከናረ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በመሆኑ፤ የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ከጥቂት አመታት በፊት ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ ማሻቀቡን ያሳያል። የዜና አውታሩ እንደ ዳቦ ያሉ ምግቦች ዋጋ ባለፈው አመት ብቻ ዋጋቸው በእጥፍ መጨመሩን አመልክቷል።

አገዛዙ የዋጋ ንረት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ይቀንሳል ብሎ ቃል ቢገባም፤ ከአሁኑ መቆጣጠር ተስኖት እራሱ ለፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ነጋዴዎችን ማጥቃት ጀምሯል። የኢኮኖሚ ተንታኞች የዋጋ ንረቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ እንደሚተነብዩ የሬውተርስ ዘገባ ጠቅሷል።

ከሁለት አመታት በፊት እንደ ግብጽ እና ሃይቲ ባሉ አገራት በተከሰተው የምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት ህዝባዊ አመጽ መፈንዳቱ ይታወሳል። በወቅቱ በነዚህ አገራት የነበረው ንረት አሁን ኢትዮጵያ ካለው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። መለስ ዜናዊ እና የቅርብ አማካሪዎቹ ከዚህ የተነሳ ከፍተኛ ጥበት ላይ እንደሚገኙ አንዳንድ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።

የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው የፖለቲካ ተንታኝም፥ በቅርብ ጊዜ በነጋዴዎች ላይ የተከፈተው ጥቃት አገዛዙ ያለበትን የስጋት ደረጃ የሚያንጸባርቅ ነው ይላሉ። በርግጥም ነጋዴዎችን ከገበያ አስወጥቶ ኢኮኖሚውን ከአንድ ዘር በተውጣጡ ምርጦች ቁጥጥር ስር ማዋል ከመሰረታዊ አላማው ጋር የሚሄድ ቢሆንም፤ መለስ ዜናዊ ህዝቡ የኑሮ ውድነቱ ከሚሸከመው በላይ እንደሆነበት ሳይገነዘብ አይቀርም ብለዋል።

በቅርቡ በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የተከሰተው የስራ ማቆም አድማ፤ የሱሉልታ ነዋሪዎች በአገዛዙ ባለስልጣናት ላይ የፈጸሙት ጥቃት፤ በጋምቤላ፣ በአላማጣ እና እንዲሁም በአፋር ህዝቡ በተናጠል እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ እና የመሳሰሉት፤ ላለፉት ጥቂት አመታት ታፍኖ የቆየው ህዝብ በምሬት እየተነሳሳ ስለመሆኑ አመላካች በመሆናቸው በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ስጋት ሳይፈጠር እንዳልቀረ የፖለቲካ ተንታኙ ግምታቸውን ገልጸዋል።