የቱኒዚያው ማእበል የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እያስጨነቀ መሆኑ ታወቀ

በቅርቡ ቱኒዚያ ውስጥ የተቀሰቀስው የህዝብ አመጽ ተቀጣጥሎና ማእበልን ፈጥሮ የሃገሪቱ ፕሬዘዳንት ቢን አሊ ወደ ሳውዲ አረቢያ እንዲፈረጥጥ ማስገደዱ የታወቀ ሲሆን ይህን ክስተት ተከትሎ በወያኔው አምባገነን አገዛዝ ባለስልጣናት ላይ ጭንቀትና ውጥረት መፈጠሩን ዘጋቢያችን ታማኝ የሆኑ የውስጥ ምንጮችን በመጥቀስ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ሪፖርት ለማወቅ ችለናል::

በቱኒዚያ የታየውን ችግር የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ በሚያስተዳድራቸው የአገር ውስጥ ዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች አንድም ነገር እንዳይዘገብ እንዳስከለከለ፤ ህዝቡ ግን በሳታላይት አማካይነት ከውጪ ወደአገር በሚገቡት እንደ ኢሳት ተሌቪዥን፤ ዶቼ ቨለ ፤ የአሜሪካ ን ድምጽ ሬዲዮ እና በግንቦት 7 ድምጽ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ከአገር ቤት እየደረሱን ያሉት መረጃዎች ይገልጻሉ።

በተያያዘ ዜና በሃገሪቱ የሚታተመውና ለመንግስት ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ የወያኔው አገዛዝ በፖሊሲ ደረጃ ያስቀመጠው የዋጋ ዕድገት ከሰባት በመቶ መብለጥ ስለሌለበት በአንድ ጤናማ ኢኮኖሚ የዋጋ ዕድገት ከሰባት በመቶ በላይ ካለፈ አደጋ አለው በማለት የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አህመድ ቱሳን ጠቅሶ መዘገቡን ለማወቅ ተችሎአል። ፡፡አህመድ ቱሳ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በቱኒዝያ የፈጠረውን ችግር በማስታወስ ችግሩ እዚህ መደገም የለበትም ፣ በመሆኑም በኢትዮጵያ የዋጋ ንረቶች ከተቀመጣላቸው የዕድገት ደረጃ በላይ እንዳይሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል ማለቱም ታውቁአል፡፡

በሌላም በኩል የወያኔው አገዛዝ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩሉ፣ የኑሮ ውድነቱ ጉልበተኛና ቀማኛ በመፍጠር አገር ችግር ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሊሆንና ሰላማዊ ኑሮንም ሊያደፈርስ ይችላል ማለቱንም ዘግቡአል፡፡

ዘጋቢያችን ከዚሁ ጋር በማያያዝ በላከልን ዘገባ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ በቅርቡ ዋጋን ለማረጋጋት በሚል የወሰደውን ዕርምጃ ተከትሎ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን እየተወያዩ እንደሆነ ታውቁአል፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች አንዱ አሠሪዎች ፌዴሬሽን እየተባለ በሚጠራው የወያኔ አገዛዝ ተቁአም የተዘጋጀው አንዱ ሲሆን፣ ነጋዴዎችም የወያኔው አገዛዝ ይህን ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሊያወያየን ይገባ ነበር ማለታቸው ታውቁአል፡፡ ለሆዳቸው ያደሩና ዘረኛውን የወያኔ አገዛዝ ወክለው የመጡት የሥራ ኃላፊዎችም በአገሪቱ ውስጥ የታየው ያልተገባ የዋጋ ግሽበት ትልቅ አደጋ ሆኗል፣ ግሽበቱ ደሃው ከሚሸከመው በላይ እየሆነ በመምጣቱ ለአገርም አደጋ ስለሆነ የዋጋ ቁጥጥሩን ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ባሁኑ ወቅት በወያኔው አገዛዝ ባለስልጣናት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ መደናገጥና ጭንቀት እየታየባቸው መሆኑን ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በቱኒዚያ በተፈጠረው ክስተት መደሰታቸውንና ከዚህም ተሞክሮ መውሰድ የሚገባቸውን ልምድ በማሰላሰል ላይ መሆናቸውን ገልጹአል::