ከቱኒዝያ ህዝባዊ ትግል የምንማራቸው ቁም ነገሮች
ዚን አል-አብዲን ቤን ዓሊ ለሃያ ሶስት ዓመታት ቱኒዚያና ህዝቧን ገዝቷል። ሞልቃቃዋ ሚስቱ ለይላ፣ ነስሪንና ሌሎች አምስት ልጆቹ የቱኒዝያን ህዝብ ሃብት በመርጨት ተዝናንተዋል። የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን “ቱኒዝያ ቤን ዓሊን የመሰለ ምርጥ ልጅ ኖሯት አያውቅም” ሲሉ ቀስቅሰዋል። ቤን ዓሊ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት የቅርብ ወዳጅ የነበረ ሰው ነው። በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንም “የነፃ ገበያ አራማጅ፤ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል አጋር፤ የምዕራቡ ዓለምና የስልጣኔ ወዳጅ” እየተባለ ተሞካሽቷል።
የቤን ዓሊ መንግሥትና ደጋፊዎቹ ስለ እድገትና ብልጽግና ቢያወሩም የህዝቡ የእለት ተእለት ኑሮ ግን እያሽቆለቆለ ነበር። ወጣቶች የዩኒቨርስቲ ትምህርት አጠናቀው ሥራ ማግኘት አልቻሉም። በአንፃሩ ደግሞ የቤን ዓሊን ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው ነበር። ዝምድናና ወገንተኛነት የሁሉም ነገር ቁልፍ ሆነ። የቤን ዓሊን መንግሥት ሞልቶ ስለተትረፈረፈው ነፃነት ሲያወራ ህዝቡ ግን የልቡን ለመናገር ተከልክሎ እያጉረመረመ ነበር። ፓሊሱና ጆሮ ጠቢው የአገሬውን ሰው አገር አሳጣው። የቤን ዓሊ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማዳከሙ ህዝባዊው ትግል መሪ ያጣ መስሎ ነበር። ሆኖምቅራኔዎች በስለው ሰበብ ብቻ ነበር የሚፈልጉት። ሰበቡ ባልታሰበ መንገድ ተገኘ። ባለፈው ወር ቅራኔው ፈነዳ። በዚህ ሳምንት ቱኒዝያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። ሁኔታዎች ወደየት እያመሩ እንደሆነ በግልጽ መናገር ባይቻልም የእያንዳንዱ እለት ውሎ የሃገሪቱን መፃዒ እድል የሚወስን እየመሰለ ነው። ታሪክ ሰሪዎቹ ከቤተመንግሥትም ሆነ ከጫካ ሳይሆን ከየጎዳናው እየወጡ ነው።
መሃመድ ቦዛዚ የሃያ አራት ዓመት የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ቢሆንም ቋሚ ሥራ ግን አልነበረውም። ከቱኒዝ 150 ኪሜ ርቃ በምትገኝ ሲዲ ባውዚድ በምትባል ከተማ አትክልትና ፍራፍሬ እየሸጠ ይተዳደር ነበር። የከተማው ፓሊሶች “ንግድ ፈቃድ የለህም” በሚል በተደጋጋሚ እቃውን ዘረፉት፣ ሰደቡት፣ ደበደቡት። ወጣቱ መሃመድ ቦዛዚ በከተማው ማዘጋጃ ቤት በራፍ በገዛ ራሱ ላይ እሳት ለኮሰ፤ ከሁለት ቀናት በኋላም ህይወቱ አረፈች። ዜናው በፍጥነት ተሰራጨ። ይህ ከሆነ ከሁለት ቀናት በኋላ የሃያ ስድስት ዓመቱ ሁሴን ናዲ ፈልሂ “በቃኝ !!!! መረረኝ!!!” እያለ 30 000 ሜጋ ዋት የሚያሰራጭ የኤሌክትሪክ ሽቦ ጨብጦ ሞተ። ሁሴን የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ቢሆንም የቤን ዓሊ ዘመድ ባለመሆኑ ሥራ አጥ ነበር።
የሁለቱ ወጣቶች ምሬት የወለደው እርምጃ መላዋን ቱኒዝያ ናጣት። ተማሪዎች በቁጣ ወደጎዳና ወጡ፤ ሠራተኞች ተከተሏቸው። አስተማሪዎች፣ ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ ነጋዴዎች፣ የቤት እመቤቶች የሥራ ልብሶቻቸውን እንደለበሱ ተማሪዎችን ተቀላቀሉ። ሁሉም ሰው፤ በሁሉም ቦታ፤ በአንድነት “መረረን!!! በቃን!!!” አለ። ቤን ዓሊ ዓልሞ ተኳሽ ወታደሮቹን አሰማራ፤ እነሱም ታንክ እየነዱ ከተማ ውስጥ ገቡ። እስካሁኗ ሰዓትም ከ100 በላይ ሰዎችን ገደሉ። ሆኖም ግን ታንኩ፣ ጥይቱ፣ የፓሊሶቹ አስለቃሽ ጋዝ የህዝቡን ቁጣ ማብረድ አልቻለም። የህዝቡ ጠንክሮ መቆም ወታደሮቹም በጭንቅላቶቻቸው እንዲያስቡ አደረጋቸው፤ እናም ቢን ዓሊ በተመኘው መጠን በህዝባቸው ላይ አልጨከኑም።
ቢን ዓሊ ድሮ ኢዲ አሚን ወደ ሸሸባት ሳዉዲ ዓረቢያ ፈረጠጠ። በአሁኑ ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት ጊዜዓዊ መንግሥት አቋቁሞ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ መንግሥት መመስረት እንዲችል ህዝቡ እንዲረጋጋለት በመለማመጥ ላይ ነው። ተገፍተው አገር ለቀው የነበሩ የፓለቲካ መሪዎችም እየተመለሱ ነው። አሁን መንግሥት ለማኝ፤ ህዝብ ተለማኝ ሆኗል። ቱኒዚያ ግን ገና አልተረጋጋችም።
ተሸናፊውን ቢን ዓሊን በማውገዝ አሜሪካንን የቀደመ የለም። አሜሪካ “ምንጊዜም ከቱኒዝያ ህዝብ ጎን እንደምትቆም” በመጀመሪያ ሂላሪ ክሊንተን ቀጥሎ ባራክ ኦባማ አረጋገጡ። ቀጥላ የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ የቱኒዚያ ህዝብ “አጋርነትዋን” በተግባር ለማረጋገጥ ለአንድ ለሊት ለመኝታ ብቻ አምስት መቶ ኢውሮ በሚከፈልበት ልዩ ሆቴል በመዝናናት ላይ የነበረችው የቢን ዓሊ ልጅ – ነስሪን – ፈረንሳይን ለቃ እንድትወጣ አደርጋለሁ ስትል ዛተች። ቤን ዓሊ ወደ ፈረንሳይ ለመሸሽ ቢያስብም የመግቢያ ፈቃድ ከለከለችው። የቱኒዝያ ጉዳይ በእንግሊዝ ፓርላማም ተነስቶ ሥልጣን ላይ ያሉትም የሌሉትም የፓርላማ አባላት በአንድ ድምጽ ቤን ዓሊን በማውገዝ “ከቱኒዝያ ህዝብ ጎን” ቆሙ።
ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች በቱኒዚያ እየሆነ ያለውን ነገር ለመዘገብ ብቻ ሳይሆን፤ የቢን ዓሊንና የሚስቱን የለይላን ጥፋቶች ለመዘርዘር ሰዓታት የፈጁ ፕሮግራሞችን ሰርተው ዓየር ላይ ለቀቁ። ሚዲያዎቹ ለይላን ሶስት ሺህ ጥንድ ጫማዎች ከነበሯት ከፊሊፒንሷ ሞልቃቃ ኤሜልዳ ማርቆስ ጋር እያነፃፀሩ በስግብግነቷ ተሳለቁባት።
የቱኒዝያ ህዝብ ትግል ቀጥሏል። ይህ ትግል ወደየት እንደሚያመራ መገመት ለጊዜው ከባድ ነው።
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እስካሁን ባየነው እንኳን ቢሆን ከቱኒዚያው ህዝባዊ ትግል የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ ብሎ ያምናል፤ ለጊዜው ግን በሚከተሉት ሶስት ዓበይት ነገሮች ላይ እናተኩራለን።
- አምባገነን ሥርዓቶች አስከፊ ውድቀት ይወድቃሉ። አምባገነኖች ከታሪክ መማር የማይችሉ በመሆናቸው ውድቀታቸውን ማሳመር አይችሉም። ወታደርና ሃብት ከውድቀት አያድኑም።
- ህዝብ ከፍርሃት ቆፈን ከተላቀቀ መሳሪያ አይገታውም። ከፍርሃት የተላቀቀ ህዝብ ራሱን ለማደራጀትና መሪዎችን ለመምረጥ ጊዜ አይወስድበትም። ቀደም ባሉ ዓመታት በዩክሬንና በጆርጂያ የታዩ ህዝባዊ የጎዳና ላይ አመፆች በአፍሪካ ምድርም የሚቻሉ መሆኑን ቱኒዚያዊያን በተግባር አስመስክረዋል።
- የኃያላን መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘት የህዝባዊ ንቅናቄው በዓላማና በሞራል ከአምባገነኖቹ በልጦ መገኘት በቂ አይደለም። የኃያላኑን ድጋፍ ለማግኘት አንባነኑን ማንበርከክ የሚችል ኃይል ሆኖ ጠንክሮ መታየት ግድ ነው።
ቢን ዓሊ ቱኒዝያ ውስጥ የገነባው ሥርዓት መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከለው አገዛዝ በብዙ እጥፍ የተሻለ ነበር። መለስ የቢን ዓሊን ጥፋቶችን በብዙ እጥፍ ከመስራቱ በተጨማሪ በሌላ ማንኛውም አገር የሌለ ትልቅ ክፋት እኛ ላይ እየፈፀመብን ነው። ይህ የክፋቶች ሁሉ ቁንጮ – መዋቅራዊ ዘረኝነት ነው። መለስ ዜናዌ ዘረኝነት የአገዛዙ መሠረት አድርጎታል። እናም ቱኒስ የተነሳው ነፋስ አዲስ አበባ ሲደርስ እንደምን ያለ አውሎ ነፋስ እንደሚወጣው መገመት ከባድ ነው። በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የተደራጀ አካል የመኖሩ አስፈላጊነት የጎላ የሚያደርገውም በእንዲህ ዓይነት ወቅት ዘረኝነት ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ተከላክሎ ንቅናቄው ግቡን እንዲመታ ማድረግ ስለሚገባ ነው። ሁላችንም ለዚህ ዝግጁ እንሁን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!