የጠፋው ትውልድ [አንድ ለቅዳሜ]
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ከትውልድ ጋራ አያይዘው ለመረዳትና ለመፍታት የሚሞክሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። እርግጥ አንድ ትውልድ የአገርን ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶችና የታሪክ አጋጣሚዎች ሊፈታ ወይም ሊያባብስ ይችላል። ሆኖም የኢትዮጵያን ችግሮችም ይሁን መፍትሔዎች በአንድ ትውልድ ሥራዎች ውስጥ መፈለግ/መጠበቅ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊያደርስ ይችላል። በተጨማሪም ሐሳብን ለማደራጀት በትውልድ ቀመር እንነጋገራለን እንጂ ማንኛውም ማኅበረሰብ ሕይወትን የሚመራው በተለያዩ ትውልዶች ተሳትፎ ነው። በአንድ ትውልድ አባላት ብቻ የሚመራና የሚኖር የሕይወት አካል የለም።
የአገራችንን ፖለቲካ በትውልድ ለመረዳት ሲሞከር የውይይቱ ማዕከል የሚሆነው ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ያለው የአብዮቱ አንቀሳቃሽ ትውልድ ነው። የ “ያ ትውልድ” ብዙዎቹ አባላት አሁን ዕድሜያቸው በአማካይ ከ50-75 ነው። “ያ ትውልድ” ከ1960ዎቹ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ፖለቲካውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል። በእርግጥ ለአንድ ትውልድ 40 ዓመት ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ሆኖ መቆየት እጅግ ብዙ ሊባል የሚችል አይደለም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትውልድ አከፋፈል ላይ የተሠራ ጥናት አለነበብኩም፤ ባገኝ እጅግ እወድ ነበር። ለዚህ ጽሑፍ ያህል “ያ ትውልድ”ን መነሻ አደርጌ ሦስት ዘመኖችን አስቀምጫለሁ። ይህን ሳደርግ ግን ወደ ፖለቲካ ትውልድ አከፋፈል ዝርዝር ሐልዮቶች (ቲዎሪዎች) መግባቱ አስፈላጊ አልመሰለኝም። የትውልዱን መለያ “ስም”፣ የትውልዱን አማካይ የትውልድ ዘመን (ልደት)፣ ፍላጎቱ ገኖ የወጣበትን የፖለቲካ ዘመኑን (ፖለቲካ)፣ እንዲሁም የትውልዱ አባላት አሁን የደረሱበትን ዕድሜ (ዕድሜ)በቅደም ተከተል አስቀምጫጨዋለሁ።
- “ያ ትውልድ”፤ ልደት 1925-1950፤ ፖለቲካ 1960-1997፤ ዕድሜ 53-78
- “የጠፋው ትውልድ”፤ ልደት 1951-80፤ ፖለቲካ 1995- ፤ ዕድሜ 23-52
- “አዲሱ ትውልድ”፤ ልደት 1981-1990፤ ፖለቲካ፣ አልደረሰም፤ ዕድሜ 20-
ዛሬ ላነሳ የፈለኩት (ነገር ፍለጋ በሚመስል መልኩ) “የጠፋው ትውልድ” ስላልኩት የራሴ ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ በመሠረቱ ስለ አገርም ይሁን ስለ ፖለቲካ ያለው አመለካከት በቅድሚያ የተቃኘው “እናት አገር” ወይም “ኢትዮጵያ” በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ነው። የ“እናት አገር” ገናና ታሪክ፣ ሉአላዊነት እና አንድነት የፖለቲካው እንብርት ነበር። ስለ እናት አገር ለተከታዩ “አዲሱ ትውልድ” የሚተርፍ አክብሮትና ፍቅር ያደረበትም ለዚህ ነው። የአክብሮቱና የፍቅሩ መገለጫ ሁሉ “ትክክል” መሆኑን ግን እጠራጠራለሁ። አብዛኛው በተለይም ከተማ ቀመሱ በ”እናት አገር” ርዕዮተ ዓለማዊና ባህላዊ መሠረት ቢቀረጽም፣ በሒደት “በብሔረሰብ መብት” አስተምህሮ መማረክ የጀመሩ ቁጥራቸው የማይናቅ የትውልዱ አባላት አሉ።
የዘመኑ ፖለቲካ ለ“ለጠፋው ትውልድ” ስለ ነጻነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት ወዘተ ይህ ነው የሚባል ሐልዮታዊም ሆነ ተግባራዊ ቁም ነገር የሚያስጨብጠው አልነበረም። በተቀራዊው የፖለቲካን አስከፊ ገጽታ “እያደነቀ” ለማደግና ለመኖር የተገደደ ነበር። በማንኛውም መመዘኛ ነጻነቱን እና መብቱን የተነጠቀ፣ ተስፋውን በቅርብ የማይመለከት፣ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በተግባር የኖረ ነው። በመሠረታዊ ተፈጥሯቸው ጨቋኝ የሆኑት ብዙዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች (ደርግ፣ ህወሓት፣ ኦነግ፣ ሻእቢያ…) ለደም ግብር የጠሩትም እርሱኑ ነው። “ወይ በባሌ ወይ በቦሌ” ያለውም ይኸው የእኔ ትውልድ ነው።
በዘመነ ደርግ ትውልዱ ስለ ነጻነትና ስለዴሞክራሲ ከመስማትና ግፋ ቢል ከማሰብ ያለፈ ዕድል አልነበረውም። እርሱም ቀርቶበት ሁሉንም የሕይወቱን ገጽታዎች ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ስርአቱ በማንም እንዲተካለት ከመመኘት አድርሶታል። ህወሓት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ጠንካራና የተደራጀ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያልገጠመውም በዋናነት በዚህ ምክንያት ነው። ምናልባት ይህ የሆነው የትውልዱ አባላት በአብዛኛው ህወሓት/ኢሕአዴግን “እንደ ነጻ አውጪ ተቀብሎት” የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። ሲጀመር ህወሓት/ኢሕአዴግ “የእናት አገር” አስተምህሮ ለመናድ እንደሚሰራ ሲናገር የቆየ ነው፤ በተጨማሪም አብዛኛው ሕዝብ ስለ “ነጻ አውጪዎቹ” ያለው መረጃ የወቅቱ መንግሥት የሚሰጠው ብቻ ነበር። ይህን ሐሳብ ያነሳሁት “የጠፋው ትውልድ” ለወሰደው አንድ መሠረታዊ ምርጫ መነሻ ምክንያት ስለሆነ ነው። ይህም ብዙ የትውልድ አቻዎቼ ለኢሕአዴግ እና በአጠቃላይም ለብሔር ፖለቲካ አራማጆች ዕድል መስጠት፣ ማዳመጥ እና ለመረዳት መሞከር እንደሚገባ ማመኑ ይመስለኛል። ከብዙ መሰሎቼ ጋራ የአገራችንን ታሪክ በብሔር መብት ጥያቄዎች አንጻር እንደገና የመገምገም፣ አዳዲስ እይታዎችን የማስተናገድ፣ የብሔር ጥያቄን በተለያየ ጥልቀትና አቅጣጫም ቢሆን የማሰላሰል (appreciate) ፖለቲካው ፈቃደኝነትም ድፍረትም አላጣንም። ቢያንስ በግሌ የብሔር ጥያቄን ከሚያነሱ ጋር እንደ ጥያቄው የምጋራቸው ብዙ ነገሮች አግኝቻለሁ፤ በአጀንዳው አቀራረጽና አቀራረብ፣ እንዲሁም በመፍትሔው ላይ ግን ልዩነቶች አሉኝ። ይህ ተሞክሮ ትውልዴን ይወክላል ብዬ መናገር ግን አልችልም። ዛሬ በብሔረሰብ በተደራቹ የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ/እናት አገር ቀና አመለካከት ያለቸው ሰዎች በአብዛኛው የዚህ ትውልድ አባላት ሆነው ቢገኙ አይገርምም። በተቃራኒውም የብሔረሰብ መብት ጥያቄ በታሪካዊዋ ኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ሊስተናገድ የሚችል ነው የሚሉም እንዲሁ።
ነካ ነካ ፖለቲካ
የጠፋው ትውልድ በዘመነ ደርግ ፖለቲካ የሚጠቀስ ተሳትፎ አልነበረውም። “ተሰብሰብ” ሲባል ይሰበሰባል፤ “ንቃ” ሲባል ይነቃል፤ “ዝመት” ሲባል ይዘምታል አለዚያም ታፍሶ ይዘምታል፤ “ጫካ ግባ” ሲባል ይገባል አለዚያም ተገዶ ይወርዳል…። ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የዚህ ትውልድ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና እምቅ አቅም ምን ሊሆን እንደሚችል የገመተ አይመስለኝም። “የብሔር ፖለቲካ” ጨዋታው ለሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሆን ሳያምኑም አልቀሩም። እነርሱ “ዴሞክራሲ” ሲሉና እኛ (የእኔ ትውልድ) ዴሞክራሲ ስንል ፈጽሞ ስለተለያዩ ነገሮች እናስብ እንደነበር የገባን ግን እየቆየ ሆነ፤ ለሁለታችንም። ለዚህም ነው ኢሕአዴግ እና ሌሎቹም ብሔር ተኮር ድርጅቶች በብሔረሰብ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ የሚያምኑ የትውልዱን አባላት እንኳን ማርካት ያልቻሉት። ምክንያቱም እነርሱ “የብሔረሰብ መብት” ሲሉ የምራቸውን ለዴሞክራሲ ይጠቅማል ብለው ነው፤ ኢሕአዴግና መሰሎቹ ደግሞ ገና እዚያ ገጽ ላይ አልደረሱም። በኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ በመሳተፍ የመጀመሪያ ቅሬታ የደረሰባቸውም እነዚሁ የትውልዴ አባለት ነበሩ።
በሌላ በኩል የተቃውሞ ፖለቲካውን ጎራ የተቀላቀሉም የመረረ እውነታ ገጣሟቸዋል። እነዚህ ወገኖች በአንድ በኩል የኢሕአዴግ ዴሞክራሲ እነርሱ ከሚሉት የተለየ መሆኑን ቢያውቁም የአፈናው አይነትና መጠን ግን ከሚያስቡት ፈጽሞ የተለየ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶቹም “ደርግ ሌላ ምን አደረገ?” ሲሉ መደመም ጀምረዋል። በሌላ በኩል በየፓርቲያቸው ውስጥ ያለው ድርጅታዊ ሕይወትም ቢሆን ሌላ የትግል ሜዳ ሆኖ ጠብቃቸዋል። ፖለቲካን እንዲሸሽ፣ ከቀረበም በጥንቸል ንቃት እንዲንቀሳቀስ በሚያሳምን ድባብ ውስጥ ያደገው ይህ ትውልድ የዘመነ ኢሕአዴግን ፖለቲካ ለመሸሽ ብዙ ጊዜም ማስጃም አያስፈልገውም ነበር። እንደለመደውም የፖለቲካ ጫማውን አውልቆ በቅርብ ተመልካችነት ተሰለፈ። ትኩረቱንም ወደ ሌሎች ዘርፎች አደረገ፤ ትምህርት፣ ንግድ፣ ቤተሰብ፣ ሃይማኖት፣ ስደት…። በዚህ ወቅት በፖለቲካዊ አቋሙ በማመናቸው ብቻ ኢሕአዴግን የተቀላቀሉ የዚህ ትውልድ አባላት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።
“የጠፋው ትውልድ” በወሳኝ የሕይወቱ ጊዜ ከፖለቲካው መጽሐፍ ከመጥፋት የተረፈው በመርጫ 97 ዋዜማ ሆነ። ቀደም ሲል እንዳልኩት የአንድ ትውልድ አባላት ሚና የጎላ እንጂ ብቸኛ ሊሆን የሚችልበት ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ ሊኖር አይችልም። በዚሁ እይታ ምርጫ 97ን ከሞላ ጎደል የዚህ ትውልድ አዲስ “አብዮት” አድርጎ መውሰድ ስሕተት አይመስለኝም። ይህ ማለት ከ“ያ ትውልድ”ም ይሁን ከ“አዲሱ ትውልድ” ለዚህ አዲስ የፖለቲካ ጅማሮ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ አልነበሩም ማለት አይደለም። የምርጫ 97ን ወሳኝ መልእክቶች እና ሥራዎች በመሠረቱ የቀረጹት የዚህ “የጠፋው ትውልድ” ፖለቲካዊ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ናቸው። የ“አዲሱ ትውልድ” የመጀመሪያ አባላትም ቢሆኑ የዚሁ መንፈስ ተቋዳሾች ሆነዋል። ይህን መልእክት በሚገባ ማንጸባረቅ የቻሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ጎልተው ወጥተዋል።
ምናልባት ይህ ታሪክ ሲነሳ ብዙ ጊዜ ቀድሞ የሚታወሰው “ቅንጅት” ነው። ሆኖም በብሔረሰብ ቢደራጁም “ጥያቄው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በመቀራረብ መፈታት ይችላል” የሚሉት ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታቸው መረሳት የለበትም። ይህ ደግሞ በመሠረቱ ብዙዎች “ቅንጅት”ን ለመደገፍ ያበቃቸው ምክንያት ሌላ ገጽታ እንጂ ፍጹም ተቃራኒ አይደለም። ቅንጅት ውስጥም ይሁን ከደጋፊዎቹ መካከል “የብሔረሰብን ጥያቄ” የማይቀበሉ ወይም እውቅና የማይሰጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ አብዛኛው የዚህ ትውልድ አባል ግን የኢትዮጵያን አንድነትና የብሔር ጥያቄን ፈጽሞ የማይታረቁ ጉዳዮች አድርጎ አይመለከትም። በዚህ መነሻነት የሚቀርቡት መፍትሄዎች ሊለያዩ ይችላሉ፤ ቁም ነገሩ ግን ብዙው ሰው አጀንዳዎቹን የተረዳበት መንገድ ነው። በመፍትሔ አማራጮች ላይ መለያየቱ የዴሞክራሲን አስፈላጊነትና ተቀባይነት ማግኘት የሚያሳይ ይሆናል። “ቅንጅት”ን የብሔረሰቦችን ጥያቄ እውቅና የማይሰጥ አድርገው የሚያቀርቡት ኢህአዴግን የመሰሉ ጠባብ ድርጅቶች እና አንዳንድ የራሱ የቅንጅት ጭፍን አባላት ብቻ ይመስሉኛል። ከዚያ ውጭ በሕዝቡ ውስጥ የነበረው “የቅንጅት መንፈስ” የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የነጻነት፣ የመቻቻል እና የመተማመን እንጂ የመጠራጠር፣ የጥላቻና የመናናቅ አልነበረም። እንዲዚያ ባይሆን ኖሮ የራሱ የህወሓት/ኦህዴድ/ብአዴን… አባላት ሳይቀሩ ለ“ቅንጅት” ድምጻቸውን ባለሰጡ ነበር።
ይህንን እውነታ “የጠፋው ትውልድ” ከደረሰበት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ደረጃ አንጻርም ማየት ወደ ተመሳሳይ መደምደሚያ ሊያደርሰን ይችላል። የትውልዱ አባላት በትምህርትና በእውቀት፣ በሥራ/ገቢ እና በማኅበራዊ ኑሮ ወሳኝ የሚባል ተሰሚነት ለመፍጠር ጊዜ አግኝተዋል። ይህ ተጽእኖ በወላጆቻቸውም ሆነ በልጆቻቸው/ታናናሾቻቸው ላይ መንጸባረቁ የማይቀር ነው። የትውልዱ ፖለቲካው ምልከታ በቀኝም ይሁን በግራ የተሰለፉትን የፖለቲካ ጎራዎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማስተናገድ የሚሞክር በመሆኑ በቀላሉ ለማጣጣል የሚመች አልነበረም። አሁን አሁን ሳየው ግን በቅንጅት ውስጥ ሳይቀር ይህ መንፈስ ዘልቆ ያልገባቸው “ትልልቅ”ም “ትንንሽ”ም ሰዎች ነበሩ። የ“ቅንጅት መንፈስ” ግን የዚህ ትውልድ አንድ ሁነኛ የፖለቲካ ፍላጎት ነጸብራቅ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል እገምታለሁ፤ ግምት ነው።
ያስተሰርያል
ምናልባት “የጠፋውን ትውልድ” ፖለቲካዊ ምኞት የሚወክል አንድ ነገር ጥቀስ ብባል መጀመሪያ ከሚመጡልኝ ነገሮች አንዱ የቴዲ አፍሮ “ያስተሰርያል” ነው። የዚህ ዘፈን ልቀት ግጥሙ ወይም ዜማው አይመስለኝም፤ መልእክቱ ነው። አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ! በነገራችን ላይ ቴዲም የዚሁ “የጠፋው ትውልድ” አባል ነው። የምርጫ 97 መንፈስ ቀደም ሲል እንዳልኩት በመሆኑ ይፈልግ የነበረው “ስርየትን” ነበር፤ ደም የማይፈስበት ስርየት። አለመታደል ሆኖ መሣሪያውን የታጠቀው የፖለቲካ ቡድን ስርየትን ያለደም ማሰብ የማይችል ድንጉጥ አማኝ ነው፤ ስለዚህም ደም ፈሰሰ፣ ለዚያውም “ስርየት” ላያመጣ።
የነጻነትን እና የዴሞክራሲን “ስርየት” ያለ ደም መፍሰስ ማግኘት እንዳልቻለ የተመለከተው “የጠፋው ትውልድ” በምርጫው ማግስት ብዙ ዋጋ ከፈለ። ይህን ተከትሎም እንደገና ወደ ጥንቸል ስጋቱ ተመለሰ። ኢሕአዴግም አገዘው፤ በአንድ በኩል ከጥቅማ ጥቅም ጋራ የተያያዘ የምልመላ ስትራቴጂ አምጥቷል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚነት ቀርቶ ብዙዎችን ሊያደራጅ በሚችል መልኩ የተለየ አስተያየት መያዝ የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል። በቤተሰብ፣ በንግድ፣ በትምህርት ወዘተ ሐላፊነቶች የተያዘው “የጠፋ ትውልድ” ፖለቲካን በጥንቸላዊ ጥንቃቄ ወደማየቱ መመለሱ ወደ ቀደመ ቤቱ እንደመመለስ ነው። ነገር ግን የአሁኑ ዘመን የተለየ ነው፤ አፈናውን ማቅለልና ማለፍ የሚችልባቸው አማራጮች አሉ። ስለዚህም እንደ ደርግ ዘመን መንግሥት የሚለውን ብቻ የመስማት ግዴታ የለበትም፤ ፖለቲካዊ ተሳትፎውንም በተለያየ መልኩ “ስሙን ሳይገልጽ፣ ድሙጹን ሳያሰማ” በለሆሳስ መቀጠል ችሏል።
የኢሕአዴግ አያያዝ “ያለደም ስርየት የለም” የሚለውን የብሉይ ሕግ የሚያጸና ሆኗል። ለታይታና ለዲፕሎማሲያዊ ፍጆታ ከሚሆነው በቀር እውነተኛ የዴሞክራሲ እና የመቻቻል ምልክቶች ጨርሰው ሊጠፉ የቀራቸው እጅግ ጥቂት ነው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ያለ ደም ማምጣት ይቻላል ወይስ አይቻልም?” የሚለውን ክርክር በድጋሚ የፖለቲካችን ቁልፍ አጀንዳ እያደረገው ያለውም ራሱ ኢሕአዴግ ነው። “የጠፋው ትውልድ” ተስፋውን አልጣለም፤ ከደርግ ጊዜ በተለየ ፖለቲካዊ ሐሳቡን በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማረመድ ስለመቻል አለመቻሉ ግን እርግጠኛ አይደለም። ስለዚህም በክርክሩ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል። በፖለቲካው ተስፋ ቆርጦ ሌላ ሕይወቱን ስለማሸነፍ ብቻ ለማሰብ የወሰነ አለ፤ ፖለቲካውን እንደ ትግል በማየት ተሳትፎውን የቀጠለ ጥቂት አለ፤ የሚከፍለውን ዋጋ በሚቀንስ መንገድ በዴሞክራሲ ግንባታ መሳተፍ የሚመኝ ነገር ግን መንገዱ ጠፍቶት ግራ የተጋባ አለ፤ ራሱን ኢሕአዴግን በመቀላቀል ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ በዚያውም ከውስጥ ለውጥን መጀመር ይቻል እንደሆነ ብሎ የሚያስብም አይጠፋም…። የኢሕአዴግን አመራር እያደነቀ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል የዚሁ ትውልድ አባል የማያውቅ ሰው ካለ አንዱን ድረ ገጽ ይጎብኝ።
“የጠፋው ትውልድ” የሽግግር ዘመኖች ትውልድ ነው፤ ለዚያውም የከሸፉ ሽግግሮች። ይህ ጠቃሚ ጎኖች ቢኖሩትም ጉዳቶችም አሉት። አንዱ ጉዳቱ ትውልዱ በፖለቲካው ውስጥ አሻራውን የሚተውበት እድልና ጊዜ ማጣቱ ነው። ሆኖም ይህ ትውልድ ደርግ እና ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መኖር ያልነበረባቸው፣ ድጋሚም መምጣት የሌለባቸው የፖለቲካ ስርአቶችና አመራሮች መሆናቸውን ኖሮ አይቷቸዋል። ይህ ትውልድ ሁሉንም ፖለቲካዊ ጽንፎች በአያቶላዎቹ ሲተነተኑ ሰምቷል፤ በፊት አውራሪዎቹ ሲተገበሩ አይቷል፣ ኖሯቸዋልም። ይህ ትውልድ የፖለቲካ ሐላፊነቱን ካልተወጣ አገራችን አዳዲስ ደርጎች እና አዳዲስ ኢህአዴጎችን ማስተናገዷ እንደማይቀር እሰጋለሁ። ያን ጊዜ ብዙ መንግሥቱዎች ወይም ብዙ መለሶች ይወሩናል፤ አያርግብንና! “የጠፋው ትውልድ” ከዚህ ልምድ የሚቀስመው ትምህርት አገሪቱን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያሸጋገር ቀመር እና ፖለቲከኞች እንዲያፈራ ይረዳው ይሆን? እስከዚያ ድረስ “እንደ ጠፋ” ትውልድ እንቆጥረዋለን፤ ልክ በጣም አልፎ አልፎ እንደምናገኘው ሰው፤ “ምነው ጠፋህ?” እንደማለት! አይዞን!