አይ ሀገሬ ! ዘለቀ ጀምበሩ (ከቶሮንቶ)
በአራዊተ መንጋ ተወርሮ ቤታችን
ጀምረን ጥገና ዘሞ ምሰሶአችን
አንዱ እስባለሁ ሲል ሌላኛው ጎትቶ
ፈረሰ ቤታችን “መሀንዲሱ” በዝቶ ::
ፍርስራሹን ቤቴን፣ … ዕድሌ እንዳየብኝ
እንግልተ ጎርፉን፣ … ቢያጥለቀልቅብኝ
ሀሩር፣ … እና ቁሩ ሲፈራረቁብኝ
ከበረሀ አድሬ ጠኔ በረታብኝ ::
ጠኔ ያጠነነው ክዶኝ ሰውነቴ
እንቅልፌም ሸፍቶ ጠፍቶብኝ ዕረፍቴ፤
እኔ እንደምን ልረፍ እንቅልፌ መንኖ
አልጋው ካልተመቼ እንኳን ትኋን ብቻ ሆኖ ::
ስደት “ዕጣ” ሆኖ ካወጣኝ ከአገሬ
አይነገር የለም፣ አይሰማ ወሬ፤
ዓይኔ አያየው የለ፣ አይሄድበት እግሬ
ያንችስ ሄዶ ሄዶ የት ጣለሽ ሀገሬ?
ተነሳሁ ቆርጨ አሻፈረኝ ብየ፤
እንዴት ለጃርት አውሬ; ሰው ይለቃል ቀየ?
ይገነባል ቤቴ ፣ … ያከትማል ስቃየ፤
እንካችሁ እስከዚያው ወርቅ ነው ቋንቋየ ::
ዘለቀ ጀምበሩ (ከቶሮንቶ)
ጥር – 2003 ዓ.ም.