በወያኔ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የናረው የምግብ ሽያጭ ተመን አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱ ተዘገበ
በወያኔ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ተብሎ የወጣው የምግብ ሽያጭ ተመን አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱ ተዘገበ።
የገና በአልን አስመልክቶ የጎጠኛው ቡድን መሪ መለስ ዜናዊ የነግድ ማህበረሰቡን ሰብስቦ ያደረገው ንግግርና ያነን ተከትሎ የወጣው የዋጋ ተመን ሰሞኑን የህዝብ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ መሰንበቱን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ከላከልን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል።
የወያኔው አምባገነን አገዛዝ ሰሞኑን ያለወትሮው የህዝቡን ችግር በቁጥጥሩ ስር በሚገኘው የቴሌቪን ጣቢያ አማካኝነት ሲዘግብ የቆየ ሲሆን በድንገት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ስብሰባ የተቀመጠው የአገዛዙ መሪ መለስ ዜናዊ ባልተጠበቀ ሁኔታ ነጋዴዎች የኑሮ ውድነት መንስዔ መሆናቸንና ይህንንም ለማሻሻል በሰላም ከመደራደር እጃቸውን እስከመቁረጥ የሚደርስ እርምጃ የሚወስድ መሁኑን በትእቢት መደንፋቱን ዘጋቢያችን ከስፍራው ከላከልን ሪፖርት ለማወቅ ተችሎአል ። ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው አንዳንድ የአድስ አበባ ነዋሪዎች የመለስ ዜናዊ ስድብና ድንፋታ በንግድ ማህበረሰቡ ላይ ሽብርንና ተስፋ መቁረጥን የፈጠር እንደሆነና ይህም በተቀረው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ የመነጋገያ ርእስ ሆኖ መሰንበቱን ለማወቅ ተችሎአል።
በከተማዋ ለረዥም አመታት በንግድ ስራ ላይ የሚተዳደሩትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ባለሃብት በሁኔታው እጅግ ግራ መጋባታቸውን ገልጸው ‘ችግሩ ሁሉ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ በሚቆጣጠራቸው ቱባ ቱባ በሚያክሉ የንግድ ድርጅቶች የተፈጠረ መሆኑን እየታወቀ እኛን ምን አድርጉ ይሉናል….እኛ ምን እንሁን’ በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል። ከውጭ አገር በመግባት ዘይት በማምረት ስራ ላይ የተሰማሩት አንድ ባለሃብት ደግሞ የዘይት እህሉን በጅምላ የሚያከፋፍሉት የወያኔ ድርጅቶች ራሳቸው እህሉን በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡልን ተመርቶ የሚወጣውን ዘይት አገዛዙ በተመነበት ዝቅተኛ ዋጋ መሸጥ በድርጅታቸው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያመጣባቸው መሆኑን ገልጸዋል። እኝሁ ባለሃብት አያይዘውም መለስ ዜናዊ ባለፈው ሳምንት ከነጋደው ህብረተሰብ ጋር ባደረገው ስብሰባ ወቅት እንደዛተው የአገሪቱ ዜጎች ተሰማርተውበት የሚገኙበትን ይህንን የንግድ ሥራ እንደሌላው የ እርሻና እንዱስትሪ መስክ ሰበብ ፈጥሮ ለቻይናና ለአረብ ባለሃብቶች አሳልፎ በመስጠት በሙስና ተጨማሪ ሃብት ለማከማቸት የታሰበ ወንጀል ከመሆን እንደማያልፍ ያላቸውን ጥርጣሬና ስጋት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ ያስገረማቸው አንድ አዛውንት ለዘጋቢያችን እንደገለጹት ወያኔ ሰሞኑን በቴለቪዥን ጣቢያው ሲያሳያቸው የቆየው ነገር ያስገረማቸው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ችግሩ ወያኔዎቹ ራሳቸው የፈጠሩት እና የደረሰበትንም ያአስከፊነት ደረጃ ጠንቅቀው የሚያውቁት መሆኑን ጠቁዋሚ እንደሆነ ተናግረዋል። አዛውንቱ እንዳሉት የወያኔው አገዛዝ ቁንጮዎች ከዚህ በፊት ተሃድሶ ብለው የሚፈልጉትን ሰው ሊመቱ በፈለጉ ጊዜ እንዲህ አይነት ዘዴ የተጠቀሙ መሆኑን አስታውሰው ይህ የሰሞኑም ዘገባ ከጀርባ አንድ ተንኮል እንዳለው ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።
ይህንኑ ጎዳይ እንዲያብራሩልን ዘጋቢያችን ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት ሙሁር ወያኔ ከዚህ በፊት የውጭ ምንዛሪ ሲቸግራቸውና የሚሰርቁት ብር ሲደርቅባቸው በብዙ ሺህ ሄክታር የሚቆጠር ለም መሬት ያለምንም ጥናት ለውጭ ባለሃብቶች መቸብቸባቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህም በውጭም ሆነ በአገርቤት ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳስነሳባቸው ጠቁመው ከዛ ስህተት በመማር በሚመስል መልኩ ትንንሸ የሚሉዋቸውን ሀገር በቀል ነጋዴዎችን በህዝቡ ዘንድ የችግሩ ሁሉ ምክንያት አድርጎ በማቅረብ ከህዝቡ ጋር ካጣሉዋቸው በሁዋል ትልልቅ የውጭ ባለሃብቶችን በማስገባት እና ከራሳቸው ድርጅቶች ጋር በጋራ እንዲሰሩ ለማድረግ የታቀደ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህም ከፍተኛ ሃብት ለመዝረፍ ሊያመቻቸው የሚችል መሆኑን ጠቁመው ሀገሪቱን ግን እጅግ ወደከፋ የችግር አረንቁዋ የሚዘፍቃት እንደሚሆን አያይዘውም ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት የአምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ነጋዴዎች የሚሸጡአቸውን ሸቀጦች ዋጋ ዝርዝር ጽፈው በየሱቆቻቸው እንዲለጥፉ መመሪያ ካስተላለፈ ወዲህ ሰበብ አስባብ እየተፈለገ ነጋዴዎቹን የማስፈራራትና አንዳንድ ሱቆችንም የማሸግ ስራ መጀመሩን የግንቦት ሰባት ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከልን ዘገባ ለማወቅ ተችሎአል።
እንደ ዘጋቢያቺን ሪፖርት በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የንግድ ድርጂቶች የወያኔው አምባገነን አገዛዝ እያደረሰባቸው ባለው ማዋከብ እና አጋጣሚውንም በመጠቀም ካድረዎች በወሰዱት እርምጃ ለረጅም ጊዜ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩትና ከአገዛዙ ምንም ጥበቃ የማያገኙ የንግዱ ህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ውስጥ ወድቀዋል። በተለይም የ ዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሲሉ በአንስተኛ የቺርቻሮ ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ አነስተኛ ነጋዴዎች ቀደም ሲል በውድ ዋጋ ከአከፋፋዮች ገዝተዋቸው የነበሩትን ሸቀጦች በኪሳራ ለመሸጥ መገደዳቸውንና በዚህም ምክንያት የመፈናቀል አደጋ እያንዣበበባቸው መሆኑን ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ በርካታ ሱቆች ለምን የሸቀጦችን ዋጋ ዝርዝር አልለጠፋቺሁም በሚል ሽፋን ሱቆቻቸው እየታሸጉባቸው መሆኑን ዘጋቢያቺን ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ገልጸውላታል፣ ፣
በአሁኑ ሰአት በከፍተኛ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ከወደቁት ነጋዴዎች አንዳንዶቹን ተዙዋዝሮ ያነጋገረው ዘጋቢያችን፣ ህብረተሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ ሸቀጦችን መግዛት የሚችልበትን ዕድል መፍጠር መልካም ቢሆንም ከአቅርቦት ጋር ያልተመጣጠነ የዋጋ ቅነሳ ለፖለቲካ ፍጆታ አጭርና ጊዜያዊ መፍትሄ ያስገኝ እንደሆን እንጂ ለዘለቀታው መፍተሄ አይሆንም ማለታቸውን ገልጾአል። አገዛዙ እውነተኛ የዋጋ መረጋጋትን ለመፍጠር ከልቡ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ በህወሃት ሥር የሚተዳደሩ ግዙፎቹ የንግድ ድርጅቶች ቀረጥ ያልተከፈለባቸውን ዕቃዎች ከመነገድ እንዲታቀቡና ለሚሠሩት የንግድ ሥራ ግብር እንደማንኛውም እንዲከፍሉ ማድረግ በተቻለ ነበር ብለዋል ። ግዙፎቹ የወያኔ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት እንዳሻቸው እንዲሠሩና በነጋዴው ህብረተሰብ ጫንቃ ላይ አንዲጨፍሩ እየተለቀቀ ከአገዛዙ ጋር የጥቅም ወይም የዘር ንክኪ የሌለንን ምን አድርጉ እንደሚሉን መገመት ከምንችለው በላይ እየሆነብን መጥቶአል በማለት ነጋዴዎች እያማረሩ ነው።