የኢትዮጵያ ህዝብ የዘረኛውን አገዛዝ ዘረፋ እየተቃወመ ነው

ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ለመጪዎቹ አምስት አመታት በእድገት ስም ላወጣው እቅድ እርዳታ መሰብሰብ በሚል ሰበብ ህዝብ ለመዝረፍ የጠነሰሰው አላማ የህዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ከአዲስ አበባ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፥ ገንዘብ እንዲያዋጡ በአገዛዙ ካድሬዎች ማስፈራራት እየተደረገባቸው ያሉት የመዲናይቱ ነዋሪዎች እምቢታቸውን በድፍረት እየገለጹ ነው። በወያኔው ሎሌ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የከተማይቱ መስተዳደር ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ከህዝብ ለመዝረፍ እቅድ አውጥቶ መነሳቱን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። ባለፉት በርካታ ሳምንታት ለዘጋቢያችን አመለካከታቸውን የገለጹ ነዋሪዎች እንኳን ለሚጠሉት አገዛዝ የገንዘብ ስጦታ ሊያደርጉ ይቅርና ምግብ መግዣም እንደሌላቸው በመናገር ሲያማርሩ ቆይተዋል።

አዲስ ነገር ኦንላይን የተባለው የዜና ድረ-ገጽም የመስተዳደሩን የዘረፋ ሙከራ መውደቅ አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፣ ካድሬዎች ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ በነዋሪዎች ላይ ተመን ሲጥሉ እና የተነገራቸውን መጠን ለመክፈል ፈቃደኞች ያልሆኑትን ሲያስፈራሩ እንደሰነበቱ ገልጿል። በዘገባው የተጠቀሰ አንድ ጸጉር አስተካካይም የተጠየቀውን ገንዘብ ካልከፈለ ስሙን በጥቁር መዝገብ ላይ እንደሚያስገቡ በመንገር ያስፈራሩትን ካድሬዎች ከቁብ ሳይቆጥር እምቢታውን አስታውቋል።

ዘረኛው እና አምባገነናዊው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍ እና ዘረፋ ከመብዛቱ የተነሳ የኢትዮጵያውያን እሮሮ የሚፈነዳበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይታወቃል። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ህዝቡ ወደ አመጽ ለመግባት የሚፈልገው ትንሽ ምክንያት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢዎች በተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ያናገሯቸው ዜጎች በተጠሩ ጊዜ ለማመጽ ዝግጁ መሆናቸውን እንደገለጹ በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።