የኬንያ ፖሊስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ሁለት ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስሬያለሁ አለ

የኬንያ ፖሊስ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከጀመረ አንስቶ እስከ አርብ ድረስ ብቻ ሁለት ሺህ ህገ-ወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ማሰሩ ተዘገበ።

ደይሊ ኔሽን የተባለው የኬንያ የዜና አውታር እንደዘገበው፥ ድህነትን ሽሽት ወደ ኬንያ የሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቁጥር በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫናን እያደረገ ነው። የታሰሩ፣ የተከሰሱ እና በጅምላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረጉ ኢትዮጵያውያን ወሬ በሞያሌ አካባቢ የተለመደ እንደሆነም አውታሩ ጠቅሷል። ወጣቶቹ ወደ ኬንያ የሚገቡት ስራ ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቋረጥ ነው ያለው ደይሊ ኔሽን፤ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ንብረት እየሸጡ ለአመላላሽ ደላላዎች እንደሚከፍሉም ዘግቧል።

በዘረኛውና አምባገነናዊው መለስ ዜናዊ የሚመራው የትግራይ ገዢ ጉጅሌ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት አስገኝቻለሁ እያለ በሚፎክርበት፤ በየአመቱ በአስርተ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እናት አገራቸውን እየጣሉ እንደሚሄዱ ይታወቃል። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ብቻ ከ42 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገራት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል። ይህ ቁጥር ግን ህገ-ወጥ የኢኮኖሚ ስደተኞችን እንደማያካትት ከዚህ ቀደም  ጠቅሰናል።

ስደተኞቹ ስራ ፍለጋ ወደሚሄዱባቸው አገራት ለመድረስ ከፍተኛ አደጋን የሚጋፈጡ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን መንገድ ላይ ይሞታሉ፤ በርካቶችም በእስር ላይ ይገኛሉ። ታዋቂው የዜና አውታር ሲ.ኤን.ኤን. ባለፈው ሰኞ እንደዘገበው፣ ስደተኞችን የጫኑ ሁለት ጀልባዎች በየመን ድንበር ላይ ከሰጠሙ በኋላ ከ80 በላይ የሚሆኑ ተሳፋሪዎቻቸው ሞተዋል ተብሎ እንደሚገመት እና ከነዚህም ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ጠቅሷል።