የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአሜሪካ ጉብኝታቸውና የቅዱሳን መጻሕፍት ስጦታዎቻቸው (ቤተ ጳውሎስ)
የሚበዙት ነገሥቶቻችን በታሪክ ረገድ የተፃፈላቸው የጦርነትና የግዛት ማስፋፋት ታሪካቸው እንጂ ለእውቀትና ለጥበብ ሥራዎች እንዲሁም ለስነ ጹሁፍ ያላቸውን ልዩ ዝንባሌና ትኩረት የታሪክ ጸሐፍቶቻችን እምብዛም ትኩረት የሰጡት አይመስሉም፤ እኛም በዚህ ረገድ ለማወቅም ሆነ ለማጥናት ያለን ፍላጎት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህም በዚህ ጹሁፍ የኢትዮጵያውያንን ነገሥታት ከስነ ጹሁፍ ጋር የነበራቸውን ትውውቅ፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ለመመርመር የነበራቸውን ብርቱ ፍላጎትና ጥረት በተመለከተ አንዳንድ ነገስታቶቻችንን እያነሳን ያለፉት ነገስታቶቻችን ለስነ ጹሑፍና የሕይወት ብርሃን ለሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የነበራቸውን ፍቅርና ክብር የሚያሳይ የሕይወታቸውን ታሪክ ክፍል ለማየት እንሞክራለን፡፡
ለዛሬ ኢትዮጵያን ከ40 ዓመት በላይ በንግስና ስለገዙትና እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ የሀገራችን ንጉሥ የነበሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለቅዱሳን መጻሕፍት ያነበራቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ቅዱሳት መጻህፍትን ለመመርመርና ሌሎችም እንዲያውቁት በማድረግ ከሀገር ውስጥ አልፈው በውጭ ሀገራት ጉብኝታቸው ጭምር ያደረጉትን አስተዋዕፆ በአጭሩ ልናስቃኛችሁ ወደድን፣ ቆይታችሁን ከእኛ ጋር ይሁን፡፡ መልካም ንባብ!
በእርግጥ በታሪካችን እንደምናውቀው የሚበዙት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከቤተክህነት ጋር ካላቸው የላቀ ግንኙነት የተነሳ በማንበብና በመጻፍ ረገድ የሚታሙ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ነገሥታቶቻችንም የተለያዩ የሃይማኖት፣ የጥበብ እና የፍልስፍና ድርስቶችን በማበርከት ለቤተክርስቲያናችንና በአጠቃላይም ለሀገራችን ሥነ ጹሁፍ የላቀ አስተዋዕፆ እንዳደረጉ የታሪክ ድርሳናት እና እስከዛሬም ከብዙ ትውልድ በኋላ በእጆቻችን የሚገኙት መጻህፍቶቻቸው ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ የስነ ጹሁፍ፣ የእውቀት እና የጥበብ ትሩፋት ወደታችኛው ሕብረተሰብ ወርዶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገበትን ሁናቴ ስንመለከት አፋችንን ሞልተን የምንናገርለት አይደለም፡፡
በተለይም ደግሞ የሚበዙት የሃይማኖት ድርሰቶቻችንና ሌሎች የምክር፣ የተግሳጽና የጥበብ መጻህፍቶቻችን የተፃፉት የግዕዝ ቋንቋ ስለነበር፣ የአማርኛ ቋንቋ የቤተ መንግስት ቋንቋ ከሆነ በኋላ የሚበዛው የህብረተሰባችን ክፍል እነዚህን መጻህፍት ሊረዳ ቀርቶ እስከ ደርግ ዘመነ መንግስት መባቻ ድረስ የሚበዛው የኢትዮጵያ ህዝብ በመሃይምነት ጨለማ ውስጥ የሚማቅቅ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል የህዝባቸው መሃይምነነትና ድንቁርና ያሳሰባቸው አፄ ቴዎድሮስ ህዝቡ ቅዱሳንን መጻህፍትን በሚረዳው ቋንቋ ማንበብ ይችል ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለቤተክርስቲያን እንዲሰጥና ካህናቱም ኅብረተሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ሲሉ እንግሊዛውያኑን ሚስዮናውያንና አማካሪዎቻቸውን በመወትወት አፄ ቴዎድሮስ ብዙ ጥረት አድርገው እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ከእሳቸውም በኋላ የነገሱት አፄ ዮሐንስም ለተዋህዶ ሃይማኖት ከነበራቸው ፍቅርና ቅናት የተነሳ ካህናቶቻቸውና ህዝባቸው በመንፈሳዊ እውቀት የበረቱ እንዲሆኑ ብዙ ጥረት ከማድረግ አልፈው ሀገራቸውንና ሃይማኖታቸውን ላለማሰደፈር ክቡር ሕይወታቸውን ጭምር ለመሰዋት ወደኋላ ያሉ ንጉሥ እንዳልነበሩ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡
ከአፄ ዮሐንስም በኋላ ለዘመናት ህዝቡን በማስተማር ታላቁን ሚና የተጫወተቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ትልቅ ኃላፊነት በመጋራት ከቤተክህነቱ ባህላዊ ትምህርት በሻገር ዘመናዊ ትምህርት በአገሪቱ እንዲስፋፋ ትልቁን ሚና በመጫወት ረገድ አፄ ምኒልክ በዋናነት የሚጠቀሱ ንጉስ ናቸው፡፡ ከእሳቸውም በኋላ ኢትዮጵያን ለረጅም ዘመን በንግሥና በመምራት የቆዩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ይሄን ጅምር ወደላቀ እድገት ደረጃ በማድረስ ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ህዝቡ በሚግባባበት በአማርኛ ቋንቋ በየቤቱ እንዲዳረስና ሀገራቸው ኢትዮጵያም የዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር አባል እንድትሆን በማድረግ እንዲሁም ዛሬ በብዙዎቻችን እጅ የሚገኘውና የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎም በማድረግ ትልቅ ባለውለታም ናቸው፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከነበራቸው ትልቅ ተቀባይነትና ክብር የተነሳ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ስልጣኔና አኩሪ ታሪክ ያላት ቀደምት የክርስቲያን ሀገር መሆኗን በውጩ ዓለማት ዘንድ በማሳወቅ ረገድ የተሳካለቸው ታላቅ ዲፕሎማት ሰው እንደነበሩ ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታሪክ ጸሐፊዎች ይስማሙበታል፡፡ እኚህ ንጉስ በሚሄዱበት ሁሉ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በእጅ የተፃፈ የብራና መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ለዓለማችን ታላላቅ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የታወቁ ሰዎች፣ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ማዕከላት በስጦታ መልኩ ያበረክቱ እንደነበር የታሪክ ጸሐፍት ይናገራሉ፡፡
የአፄ ኃይለ ሥላሴን ዓለም አቀፍ ስብእና፣ የተዋጣላቸው ዲፕሎማትና ከውጭ ሀገራት ጋር የነበራቸውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በተለይም ደግሞ ከሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነትና ጉብኝታቸውን በሚጥም ቋንቋ ‹‹The Lion of Judah in the New World›› በሚል ርዕስ ይህን ድንቅዬ መጽሐፍ ስለንጉሱ በርካታ መረጃዎችን አቅርበውልናል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ቲዮደር ኤም ቬስታል በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር፣ የኦክላህማ ስቴት ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሳይንስ ኤምሬት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት አሜሪካውያን የሰላም ጓዶችን በማስተባበር በሀገራችን በቆዩበት ወቅት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ታሪክና የንጉሱን ፖለቲካዊ ሰብእና እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት በቅርብ ለመረዳት እድሉን አግኝተው ነበር፡፡ ይህ መጽሐፋቸውም የዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታቸው አንዱ ገጸ-በረከት ነው፡፡
እኚህ ምሁር ኃይለ ሥላሴ በተለያዩ ጊዜያት በአሜሪካ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች በተመለከተ በዚሁ መጽሀፋቸው ብዙ ነገር ይነግሩናል፡፡ ፕሮፌሰር ቬስታል እንደሚነግሩን የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም በፕሬዝዳንት አይዘንሀወር ጋባዥነት የአሜሪካ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ሴኔት በሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጣቸው ጊዜ ለዚህ ክብር ያጯቸውን ዩኒቨርስቲውና የዩኒቨርስቲውን ማህበረሰብ ካመሰገኑ በኋላ ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በእጅ የተፃፈ የብራና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በታላቅ አክብሮት ማበርከታቸውን ፕሮፌሰር ቬስታል በዚሁ መጽሐፋቸው ይነግሩናል፡፡
በተጨማሪም ንጉሱ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም በሦስተኛው የአሜሪካ ጉብኝታቸው የካሊፎረኒያ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ፍራንክሊን ዲ መርፊ አራት ሺ የሚሆኑ ዩኒቨርስቲው ማኅበረስብና ታዋቂ ሰዎችና እንግዶች በተገኙበት ለንጉስ አፄ ኃይለ ሥላሴ በሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጧቸው ጊዜ ለዚህ ክብር ለዩኒቨርስቲው ቤተ መጻህፍት በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ቅዱሳት መጻህፍትንና በብራና የተፃፉ የአዲስ ኪዳን መጻህፍትን አበርክተዋል፡፡
በሴሜቲክ ቋንቋ ጥናት የተከበሩ ፕሮፌሰር የነበሩትና እንግሊዘኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ያበረከቱልን እውቁ የአማርኛና ግዕዝ ቋንቋ ምሁር ፕሮፌሰር ዎልፍ ልስላው በዚሁ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሰቲ መምህርና የሴሜቲክ ቋንቋ ተመራማሪ በነበሩበት ዓመታት እነዚህን የንጉሱን ስጦታ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጻሕፍትን ለጥናትና ለምርምር እንደተጠቀሙባቸው በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል እጅግ ተወዳጅ የነበሩትና በሰው እጅ ሕይወታቸው ያለፈው በጆኔፍ ኬኔዲ ጋባዥነት እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም አሜሪካን የጎበኙት አፄ ኃይለ ሥላሴ በፕሬዝዳንት ጆኔፍ ኬኔዲ በነጩ ሳሎን በተደረገላቸው የክብር ግብዣና የስጦታ ልውውጥ ወቅት እጅግ ያከብሯቸው ለነበሩት ለጆኔፍ ኬኔዲ ካበረከቱላቸው ስጦታዎች መካከል ሁለት መቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈ የብራና መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት እንደሚገኙበት ፕሮፌሰር ቬስታል በዚሁ መጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡
በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜ Man of the Year የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት የለንዶኑ ታይምስ መጽሔት የመረጣቸው አፄ ኃይለ ስላሴ ከፍ ያለ ሰብእና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቅ መሪና አባት የሚታዩ የተዋጣለቸው ዲፕሎማቲክ፣ እንዲሁም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ንጉስ እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እኚህ ንጉስ በሄዱበት ሁሉ ቅዱሳት መጻህፍትን ከእጃቸው የማይለዩና ልዩ ፍቅርና ከበሬታ ለሚሰጧቸው ወዳጆቻቸው ከሚያበረክቷቸው መጻህፍት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ ዋንኛው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አዎን መጽሐፍ ቅዱስ ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ስጦታ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለማችን ነገሥታትና መሪዎች ህዝባቸውን የሚያስተዳድሩበትን መልካም ጥበብንና ማስተዋልን የሚለግስ ዘመን የማይሽረው ድንቅዬ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ ልዩ ቅዱስ መጽሐፍ በዘመናት ሁሉ እጅግ ተከብሮና ተወዶ የኖረ፣ የብዙዎችንም ልብና ኅሊና በመግዛት ወደር ያልተገኘለት መጽሐፍ ነው፡፡
በዚህ ዘመን ለወዳጆቻችን፣ ለትዳር አጋሮቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ ለምናፈቅራቸውና ለምናከብራቸው ሁሉ የምንሰጠው ክቡርና ወድ ስጦታ ምን ይሆን? የመጻሕፍት ስጦታ ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ስጦታ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ደግሞ ከሁሉም ስጦታዎች በላይ የሚልቅ የሕይወት ብርሃንና የእውነተኛ ፍቅር ማሳያ ስጦታ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ መጽሐፍ የሕይወት መመሪያ መጽሐፍ ነው፤ ስለሆነም ዘወትር በጸሎት ሊነበብና ሊጠና የሚገባው የእውቀትና የጥበብ ምንጭ የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ የአሜሪካ 16ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብን አስመልክተው የተናገሩትን ታላቅ ቁምነገር በመጥቀስ የዛሬውን ጹሁፍ በዚሁ እንቋጭ፡-
‹‹መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቤ ብዙ አትርፌአለሁ፡፡ እስቲ አንተም በመንፈስና በእምነት ተሞልተህ አንብበው፡፡ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ የተሻለ ሰው ሆነህ ትኖራለህ፡፡ እንደተከበርክም ታልፋለህ፡፡››
ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመመርመር እንትጋ!