አቡጊዳ – በየትም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማንም አደራዳሪና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መስማማት እንደሚፈልጉ አቶ መለስ ገለጹ

አቶ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠሩት ፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አቀረቡ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የኤርትራ ህዝብ ወንድማማች ሕዝቦች እንደሆኑ የገለጹት አቶ መለስ ያላቸው ጠብ በስልጣን ላይ ካለዉ ቡድን ጋር እንደሆነም አስረድተዋል።

የኤርትራ መንግስት አካባቢዉን የማተራመስ ሥራ እየሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ መለስ፣ እንደዚያም ሆነ ግን ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በማንኛዉም ቦታ፣ በማንኛዉ ጊዜ፣ በማኝኛዉም ሁኔታ በማንም አደርዳሪ ፣ ከተፈለገም ያለ አደራዳሪ ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ በግልጽ አስታወቀዋል።

በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማህበር ያወጣዉን መግለጫ በተመለከተ ባቀረብነዉ ዘገባ ፣ ማህበሩ የመለስ አገዛዝ በሻእቢያ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቁን፣ እንደዚያም ሆኖ ግን በወቅቱ ያነጋገርናቸዉን የፖለቲካ ተንታኝ በመጥቀስ፣ ከበርካታ የቀድሞ የሕወሃት አባላትና የትግራይ ተወላጆች ፍላጎት ጥያቄ ዉጭ፣ በምንም ሁኔታ ሻእቢያ ላይ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ፣ ጥቃት እንደማያዙ፣ በድብቅ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል መዘገባችን ይታወሳል።

በኤርትራ ጉዳይ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ የመለሱትን እንደሚከተለዉ አቅርበናል፡

========================================================

በቅርቡ የአገር ሽማግሌዎች ቢሞክሩስ በሚል የተነሳዉን ጥያቄ የበተመለከተ …. አንደኛ ማለት የምፈልገዉ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ጠብ የለንም። ጠባችን በስልጣን ላይ ካለዉ ቡድን ጋር ነዉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ የኤርትራን ሕዝብ እንደ ወንድሙ አይቶ የሚያስተናገድ ነዉ። አሁን ብዙ ስደተኞች ነዉ እየመጡ ያሉት ከኤርትራ። ስደተኛዉ ሲመጣ ባእድ አገር ዉስጥ እንደገባ ሆኖ አይሰማዉም። ሕዝቡም የሆነ ባእድ እንደመጣ አድርጎ አይደለም የሚያየዉ። በሕዝቦች መካከል ያለዉ ወንድማማችነት እንደተጠበቀ ነዉ። እንደተጠበቀ እንዲቀጥልም ይሄ መንግስት አበርትቶ ይሰራል። መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም በጠቅላላ በተመሳሳይ ሁኔታ ይሰራል።

ከመንግስቱ ጋር ያለዉ ልዩነት ግን አስቸጋሪ ነዉ። ከኤርትራ መንግስትም ጋር ቢሆን የመጀመሪያዉ ምርጫችን ፣ ሁለተኛ ምርጫችን፣ ሶስተኛ ምርጫችን በሰላም መፍታት ነዉ። ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነዉ።

ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንፈልጋለን የሚል አጠቃላይ አነጋገር ብቻ በቂ አይደለም። ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ምን መስራት ያስፈልጋል ፣ «ምን መስራት ይገባል» ብለን አስበን ከስንት አመታት በፊት የሰላም አማራጭ አቅርበናል። ባለ አምስት ነጥብ የስላም መፍትሄ። «በዚህ በዚህ መልኩ ሰላም ለማግኘት እንችላለን። ከእናንተ ጋር፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር በሰላም ለመኖር እንፈልጋለን። ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመንግስቱ ጋር ያለንን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንፈልጋለን» ብለን ባለ አምሰት ነጥብ የሰላም ሃሳብ ካቀረብን ሰንብተናል።

ሃሳብ ማቅረብ ብቻ አይደለም። ሃሳቡን በተግባር ለማሸጋገር ከኤርትራ መንግስት ጋር በማንኛዉም ወቅት ፣ በማንኛዉም ቦታ ፣ በማንኛዉም አኳሃን ለመወያየት ለመደራደር ዝግጁ ነን ብለናል። አደራዳሪ መምረጥ ሃላፊነት የኛ አይደለም። ማንኛዉንም አደራዳሪ ለመቀበል ዝግጁ ነን። «የአገር ሽምግሌዎች ይሞክሩት» የተባለዉም ከዚህ በፊትም ተሞክሯል። የሃይማኖት አባቶች፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች፣ በሁለቱ መንግስታት መካከል እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።በወቅቱ ይሄን ጥረት እኛ ደግፈናል።የኤርትራ መንግስት ግን ስላልፈለገ አቆመዉ።

እኛ ማንኛውም አደራዳሪ ቢመጣ ችግር የለብንም። ያለ አደራዳሪ እንነጋገር ከተባለም ችግር የለብንም። ያለ አደራዳሪ እንነጋገር ካሉም ችግር የለብንም። የአገር ሽምግሌዎች ያደራድሩን ካሉም ችግር የለብንም።

ነገር ግን ሰላም እስኪገኝ ድረስ፣ የኤርትራ መንግስት የሚያደርገዉን የማተራመስ ስትራቴጂ ለማስቆም ሶስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ይዘን እየሄድን ነዉ።
አንደኛ በአለም አቀፍ ሕግ መሰረት የአለም አቀፍ ሕብረተሰብ በኤርትራ መንግስት ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር ማድረግ ነዉ። በዚህ መስክ ጥሩ ሥራ ተሰርቷል የሚል እምነት አለኝ።

ሁለተኛ ለማተራመስ የሚጠቀምባቸዉን ተላላኪዎቹን ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብ ነዉ። እዚህም ላይ ጥሩ ሥራ ተሰርቷል ብለን እናስባለን። በሚስጠር የሚያሰማራቸው አሸባሪዎች ሻእቢያ እንዳሰቡት ሊሰሩለት ስላልቻለ ፣ መነሻቸዉን ኤርትራ ያደረጉ ሽብርተኞችን አሰማርተዉ፣ እኛ ጋር ደርሰው ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ማድረግ ፣ እንደ አማራጭ እንዲወስዱ ያስገደደዉ፣ አሸባሪዎቹን ለመቆጣጠር የሻእቢያ ተላላኪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማስደረግ ያካሄድነዉ ሥራ ዉጤታም እየሆነ ስለመጣ ነዉ።

ሶስተኛ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነዉ፣ ለመጠቀም እንድንችል፣ ወታደራዊ ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ ስናካሂድ ቆይተናል። ይሄ ዝግጅት ለወደፊቱም የሚቀጥል ይሆናል። በዝግጅቱ ጋር በተያያዘ ተመጣጣኝ የመከላከል እርምጃ ለመዉሰድ አስፈላጊና ጠቃሚ ነዉ ተብሎ በታመነበት ወቅት ተመጣጣኝ የመከላከል እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። እነዚህን ሶስት ስታራቴጂዎች አጣምረን እራሳችንን እንከላከላን። ይሄን እያደረግን ደግሞ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አብረን እንሰራለን።