የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪዎች በጨረፍታ
ተመስገን ደሳለኝ (አዲስ አበባ)
(ፍትህ ጋዜጣ) ከዚህ ቀደም የፖለቲካ መዘውሩን ከያዙት መሪዎቻችን ጀምሮ እስከ ድርጅቶቻቸው ድረስ ‹‹እከሌን በጨረፍታ፣ እከሌን በጨረፍታ…›› እያልኩ መዳሰሴን ያስተዋለው ወዳጄ አቤ ቶኪቻው ከእለታት በአንዱ ቀን እንዲህ አለኝ፡፡
‹‹ዛሬ የፃፍከውን አነበብኩት››
‹‹እናሳ! እንዴት አየኸው?›› ጠየኩት፡፡ ሳያቅማማም እንዲህ ሲል መለሰልኝ ‹‹በርግጥ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሰዎች ጨርፈህ ጨርፈህ ጨረስካቸው››፡፡ ዛሬ አቤ ሀገር ቤት የለም፡፡ ወዶ ግን አይደለም፣ ተገዶ እንጂ፡፡ ደረጀ ደስታ እንዲህ ከእኛ ከነፃ ጋዜጠኞች እንደአንዱ ከመሆኑ በፊት ፋና ዲሞክራሲ በሚያሳትመው ተከታታይ እፍታ መጽሐፍ ላይ ‹‹ስብሃት ወዶ አይደለም›› የምትል አሪፍ ግጥም ጽፎ ነበር፡፡ ዛሬ ደረጀ ደስታ ግጥም አይፅፍም፡፡ በዋሽንግተን አካባቢ እንደ መስቀል ወፍ ከስንት አንዴ ብቅ የምትል የራሱ ጋዜጣ አለችው፤ አልፎ አልፎ ወደ ድህረ ገፆችም ብቅ ይላል፡፡ነገር ግን በግጥም አይደለም፡፡ በፖለቲካ ኮመንተሪ እንጂ፡፡
በርግጥ ምድቡን የለቀቀው ደረጀ ብቻ አይደለም፤ ተስፋዬ ገ/አብም ከለቃቂዎቹ አንዱ ነው፡፡ ሌሎችም አሉ፣ ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡ በግልባጩ ደግሞ ከኛ ከተራው ወይም ከተገዥዎች ወይም መገዛት ከማይሰለቻቸው ምድብ ወደ ¬¬‹‹አውራው›› ምድብ የተቀላቀሉ አሉ፡፡ ሬድዋን ሁሴን ምድብ ከቀየሩት አንዱ ናቸው፤ ሽመልስ ከማልም ሌላኛው ናቸው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን እንደ ቅርጫ ስጋ ‹‹የእኛ›› እና ‹‹የእነሱ›› ብለን እንዘርዝር ካልን ማለቂያ ስለማይኖረው ወደ አጀንዳዬ ባልፍ የተሻለ ነው፡፡
አጀንዳዬም ይህ ነው፡፡ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪዎች አንድ ሶስቱን ጨርፎ ማየት፡፡ አዎ! ሁልጊዜ መለስን ብቻ ከምናይ፣ ከጀርባ ሆነው ጣራችንን የሚያበዙብንንም ብናያቸው ምን ይለናል? ምንም፡፡ ኧረ እንዲያውም ከነተረቱ ‹‹ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ›› አይደል እንዴ የሚባለው፡፡ በርግጥ ይሄ ለግለሰብ ሲሆን ነው፤ ‹‹ጓደኛህን…››፡፡ ለመሪዎች ግን ‹‹አማካሪህን ንገረኝ›› ነው፡፡ ምክንያቱም ጓደኞቻቸውን ማወቅ ማንነታቸውን ማወቅ አይደለምና !
እሺ! ጤና ይስጥልኝ ‹‹…አማካሪ ፋሲል ናሆም፣ አማካሪ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ፣ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፡፡››
እንደመንደርደሪያ…
መጀመሪያ ቃል ነበር! ቃልም… ነገሩም እንዲህ ነው፡፡ በመጀመሪያ አፍሪካ በቀኝ ገዥዎች ስር ነበረች፡፡ ከኢትዮጵያ በቀር፡፡ ኢትዮጵያም ሌሎች አፍሪካውያን ነፃ ይወጡ ዘንድ ከስንቅ እስከ ትጥቅ አቀበለች፡፡ እነሆም አብዛኛው አፍሪካውያን ነፃ ወጡ፡፡ ሆኖም ከአድማስ ባሻገር አተኩረው ቢያዩ እሩቅና ባድማ ሆነባቸው፡፡ ጭው ያለ በረሃ፣ ሁሉም ነገር ጭልጥ ያለ ምድረበዳ ላይ ያሉም ሆኖ ተሰማቸው፡፡ ይህን ጊዜም ነው ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የተባሉ ንጉሰ ነገስት ሰበስበው ያደራጇቸው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም በዚህ ሁኔታ ተመሰረተ፡፡ የድርጅቱም መቀመጫ ኢትዮጵያ፣ የመጀመሪያው ሊቀመንበርም አፄ ኃይለ ሥላሴ ሆኑ፡፡ …ይሄ ከሆነ ከ50 አመት፣ ንጉሰ ነገስቱ ከሞቱ ከ37 አመት በኋላ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት አስተዋጽኦ ያደረጉት የኢትዮጵያው ፊውዳል ሳይሆኑ፣ ኮሚኒስቱ ክዋሚ ንኩሩማ ነው በሚል በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ሀውልት ቆመለት፡፡ የናቡከደነፆር አይነት ሀውልት-የሀሰት አምልኮም ይሉሀል ይህ ነው፡፡
በእርግጥ ለዚህ ተጠያቂው በጅምላ ታሪክን የካዱት የመላው አፍሪካ መሪዎች ሲሆኑ፣ በተናጠል ደግሞ የሁልጊዜው ተጠያቂ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ናቸው፡፡
…እርግጥ ነው መለስ የአፄውን አገዛዝ አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበር ማንም አይስተው፡፡ ከእድሜ እና ከትምህርት አቻዎቻቸው ጋር በመሆንም ‹‹የአፄ ኃይለ ሥላሴ የፊውዳል መንግስት ለአፍሪካ ሶሻሊስት አብዮት ጠንቅ ነው›› ሲሉ አምርረው ተቃውመዋል፡፡ ይሄ አንድ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ፊውዳሊዝም ብቻ ሳይሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲም እንኳን ለኢትዮጵያ ለአፍሪካም ጠንቅ መሆኑን እኔም እናገራለሁ፡፡
አፄው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከማንም አፍሪካዊ መሪ በተሻለ መልኩ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ደግሞ ሌላኛው እውነት ነው፡፡ ለዚህም ነው የንክሩማን ሀውልት መታሰቢያ ሳይሆን- የአምባገነኖች ጣኦት መስሎ የታየኝ፡፡ (ምንአልባት ሀውልቱ እንዲሰራ ሀሳብ ያቀረቡት ጋዳፊ ይሆኑ እንዴ?)
የሆነ ሆኖ የሀውልቱ ምረቃ እለት ሀውልቱ የተሸፈነበት ጨርቅን መሪዎቹ በጋራ ሲገልጡ መለስ ‹‹በየለሁበትም›› አይነት ስነ-ስርአቱን ከመካፈል ይልቅ በቀጥታ ወደ አዳራሹ በመሄዳቸው በቦታው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ‹‹መለስ የአፄ ኃ/ስላሴ ሀውልት ባለመሰራቱ ተናደዋል››ማለት ነው ሲሉ አሰቡ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ከትላንት በስቲያ በፓርላማው ተገኝተው ‹‹ለአፄው አይገባቸውም፤ የሚገባው ለንክሩማ ነው›› ብለው ሲከራከሩ አየን፡፡ የመከራከሪያ ነጥባቸው ግን ፍፁም ደካማ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የመለስ መከራከሪያ ‹‹ንክሩማን የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ በመሆኑ ይገባዋል›› የሚል ነው፡፡ ትልቁ ማደናገር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሌላ፣ ፓን አፍሪካኒዝም ሌላ ናቸውና፡፡ የእነንክሩማን ፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና የሚያወራው ‹‹አፍሪካን አንድ ስለማድረግ ነው››፤ የዚህ ሁሉ ሀሳብ አመንጪም የጋናው ንክሩማ ሳይሆን፣ የካሪቢያኑ ማርክስ ጋርቬ ነው፡፡ የመጀመሪያው የፓን አፍሪካኒዝም ጎባኤም የተካሄደው በ1900 እ.እ.አ ለንደን ላይ ነው፡፡ እናም ፓን አፍሪካኒዝም በንክሩማን ልብ ውስጥ የሰረፀው በ1945እ.እ.አ ማንችስታር ላይ በተካሄደው ሁለተኛው የፓን አፍሪካኒዝም ጎባኤ ላይ ከጆሞ ኬንያታ ጋር ተጋብዞ ከተገኘ በኋላ ነው፡፡
በቃ የፓን አፍሪካኒዝም መዳረሻ ነጥብ አፍሪካ ውስጥ ያሉት ጥቁሮች ብቻ ሳይሆኑ በየትኛውም የምድራችን ዳርቻ ያሉ ጥቁሮች በሙሉ አፍሪካውያን ናቸው የሚል እና አንድ አፍሪካን መፍጠር ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንኳን ያኔ ዛሬም አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ንክሩማን እና አፄው ከሞቱ በኋላ አፍሪካ አንድ ልትሆን ቀርቶ በርካታ ሀገሮች ተገንጥለው ወጥተዋል፤ ራሳቸውንም ችለው አዲስ ሀገር ሆነዋል፡፡ (አሁን በቅርቡ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳንን ማየት ይቻላል) ከዚህ አኳያ ካየነው የነንክሩማን ሃሳብ የትም አልደረሰም፡፡ አሁን አለማችን ባለችበት ሁኔታ ደግሞ የፓን አፍሪካኒዝም አስተምህሮት ወንዝ አያሻግርም፡፡ የአፄው ግን ‹‹የጋራ ደህንነት ማስከበር››ን (collective security) መሰረት ያደረገ በመሆኑ ዛሬ ያለውን ‹‹የአፍሪካ ህብረት›› ይወክላል፡፡ ለዚህም ነው ከንክሩማን ይልቅ የሚገባቸው አፄው ናቸው የሚለው ክርክር ሚዛን የደፋው፡፡ እናም የአቶ መለስን ንግግር ስሰማ የኢትዮጵያ ሳይሆን የጋና ጠ/ሚንስትር መስለው ነበር የታዩኝ፡፡ ብቻ ምን ያደርጋል? ባይሆን ‹‹መለስ ሆይ! እባክዎት ከኢትዮጵያ ታሪክ እና ከኢትዮጵያ ጋራ መላተሞትን ያቁሙ፡፡ ኢትዮጵያን ማንም አያሸንፍምና!›› ብሎ ማለፉ ይሻላል፡፡ የአፍሪካ ህብረትም የኃይለ ሥላሴን ውለታ መዘንጋቱ ያሳዝናል፡፡ የአፍሪካ መሪዎችም እስከ መቼ ድረስ እንዲህ ምርጫ እና ታሪክ እያጭበረበሩ እንደሚቀጥሉ እግዜር ይወቀው፡፡ …አሁን ወደተነሳንበት ነጥብ እንመለስ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪዎች በጨረፍታ ወደማየቱ፡፡ ፋሲል ናሆም፣ እንድርያስ እሸቴ እና ሬድዋን ሁሴን…
ዶ/ር ፋሲል ናሆም
በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ በህግ የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ አላቸው፤ ፋሲል ናሆም፡፡ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ የተከታተሉት እኚህ ሰው በአባታቸው አይሁድ ሲሆኑ፣ ወላጅ እናታቸው ደግሞ ኤርትራዊ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
እናም ፋሲል ናሆም ማን ናቸው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ለነገሩ ጥያቄው ቢነሳም አይገርምም፡፡ ሰውየው የዋናው ‹‹ሰውዬ›› አማካሪ ከመሆነቸው አኳያ ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ የህግ እውቀታቸው ላይ ብዙም ጥርጣሬ ያለው የለም፡፡ ሁለቱን የኢትዮጵያ ህገ መንግስቶች የመዳፋቸውን ያህል አብጠርጥረው ያውቋቸዋል፡፡ የደርግን እና የኢህአዴግን፡፡
አዎ! የኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም አስተዳደር የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ (ኢህዴሪን) ከመሰረተ በኋላ ህገ-መንግስት አዘጋጅቶ አፅድቋል፡፡ የዚህ ህገ መንግስት አርቃቂ ደግሞ የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፋሲል ናሆም ናቸው፡፡
የኢህአዴግ ህገ መንግስት ሲረቅም ፋሲል ናሆም የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባል ባይሆኑም ኤክስፐርት ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከዛም አልፎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህግ አማካሪ ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ እየሰሩ ነው፡፡ አሁን አንዳንድ ተቃርኖዎችን እንይ፡-
የመንግስቱ ኃ/ማርያም አስተዳደር አሀዳዊ ሲሆን፤ የመለስ ደግሞ ፌደራላዊ ነው፤ የኢህዲሪ ህገ መንግስት ለመንግስቱ በቀጥታ ስልጣን ሲሰጥ፤ የኢፌዴሪ ደግሞ ለይስሙላም ቢሆን ስልጣን ለክልሎች ይሰጣል፤ መንግስቱ ኃ/ማርያም ለሚወስዱት የአፈና እርምጃዎችም ሆነ ግድያዎች ምንም አይነት የህግ ከለላ አይጠቀሙም (ህግ ቢጠቀስ ባይጠቀስ ደንታ አይሰጣቸውም) መለስ ዜናዊ ደግሞ ለእያንዳንዱ እርምጃቸው ህግ ይጠቅሳሉ፣ የሚጠቀስ ቢያጡ እንኳ እድሜ ለእነ ፋሲል በአንድ ምሽት ህግ አስወጥተው ያድራሉ፤ የኢህዴሪ ህገ መንግስት ኤርትራን ጨምሮ አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ ሲል፣ የኢፌዴሪ ደግሞ ኤርትራ ቀርቶ ሌሎች ክልሎችም የመገንጠል (ኢትዮጵያዊ አይደለንም የማለት) መብት እንዳላቸው በግልፅ ይደነግጋል፡፡… እንዲህ እንዲህ እያልን መንግስቱ ኃ/ማርያም እና መለስ ዜናዊ በውጤት ካልሆነ በቀር በአካሄድ በፍፁም የማይመሳሰሉ ስለመሆናቸው ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይሄ በቂ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ፋሲል ናሆም ሁለት በፍፁም ሊገናኙ የማይችሉ ሰዎችን እና የተጠፋፉ ስርአቶችን እንዴት ለማማከር እንደቻሉ እና ምን አይነት አማካሪ እንደሆኑ ማየት እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡
እግዲህ ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር ፋሲል እስከተከፈላቸው ድረስ እውነት፣ መርህ፣ ህሊና፣ ሞራል… የመሳሰሉት ብዙም የሚያሳስባቸው አይመስለኝም፡፡ መቼም የመንግስቱ ኃ/ማርያምም የመለስ ዜናዊም አማካሪ አንድ ሰው ነው ቢባል ማን ያምናል? እንግዲህ በደርግ መንግስት ትልቁ ችግር የህግ የበላይነት አለመኖር እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በይስሙላ ህግ (Pseudo Law) እና በይስሙላ ዲሞክራሲ (Pseudo Democracy) የሚስተካከለው የለም፡፡ የሁለቱም የህግ ሊቅ ደግሞ ፋሲል ናሆም ናቸው፡፡ እግዜር ያሳያችሁ! በደርግ መንግስት ‹‹መገንጠል›› እንደማይቻል የሚያብራራ ህገ-መንግሥት ያረቀቀ ሰው፣ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሲተካ ደግሞ ‹‹መገንጠል›› እንዴት ቀላል እንደሆነ የሚያብራራ ህገ-መንግሥት ሲያረቅ? መቼም ከኤርትራ ገንጣዮች ጋር ያን ያህል አመት የፈጀ ጦርነት የተደረገው ህገ-መንግሥቱ መገንጠልን ስለማይፈቅድ መሰለኝ፤ ተሳሳትኩ እንዴ የተከበሩ አማካሪ? እዚህ ላይ ሊሰመር የሚገባው የሀገር መሪን የማማከር ስራ ከሀገር ፍቅር ስሜት (Sense of National feeling) ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት ነው፡፡ …ማን ያውቃል ምን አልባትምየጠላት ሀገር አማካሪ እያስደበደበን ቢሆንስ?
የሆነ ሆኖ መለስ ህግ እንዳልተማሩ ይታወቃል፡፡ የግድ መማርም አይጠበቅባቸውም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ያለ መሪ እንዲህ አይነት ክፍተቱን የሚሞላው በአማካሪዎቹ ነውና፡፡ ችግር ያለው የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የመያዶች፣ የፕሬስ፣ የሊዝ አዋጅን የመሳሰሉ አወዛጋቢ እና ተቃውሞ የገጠማቸው ህጎች ሲወጡ አማካሪው ማን ነው? የሚለው ስር ነቀል ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡ ይሄኔ ነው ከአማካሪው ጀርባ ያሉ ነገሮች የሚፈለፈሉት፡፡ እናም ምንአልባት አማካሪው ፓስፖርቱ ሳይሆን ደሙ ከወዴት ነው? ሊባል ይችላል፡፡ ከኤርትራ? ወይስ ከእስራኤል?… ማን ነበር አንቺ ምን አለብሽ ሁለት አባት አለሽ ያለው?…ሶስት ሆነ መሰለኝ?
አማካሪ ፋሲል ናሆም ጥር 15 እና ጥር 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ በዛ ቃለ መጠይቅ ላይም የነካኳቸው ጉዳዮች ቀልብ ይስባሉ፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ እቅዴ የሚሳካው 40 እና 50 አመት በስልጣን ላይ ስቆይ ነው ሲል ይከራከራል፡፡ አማካሪውም ይህን ያበረታታሉ፡፡ በቀጥታ አይደለም፤ በተዘዋዋሪ እንጂ፡፡ አዲስ ዘመን ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት እያሉ የሚጠይቁ ሰዎች እንዳሉ የሚጠቅስ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ እሳቸውም መለሱ ‹‹…ህገ መንግስታችን በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ አንፃር ሁለት አስርት ዓመታት ያልሞላው ለጋ ህገ መንግስት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የሚያልመው ራዕይ በጣም ጥልቅና ሰፊ በመሆኑ በእነዚህ ጥቂት አመታት ሊገኝ የተቻለው ውጤት አበረታች ቢሆንም አሁንም ገና ነው፡፡ …በ20 እና በ30 ዓመታት ጊዜ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ትልሟን ትቀጥልበታለች፡፡›› ጥሩ ምክር ነው ክቡር አማካሪ፡፡
ኧረ ለመሆኑ ሕገ-መንግስቱ ገና ለጋ ነው ማለት ምን ማለት ነው? 20 አመት የቆየ መንግስት እንዴት ገና ለጋ ነኝ ይላል? እንደው በእርስዎ እይታ ሕገ-መንግሥቱ በሰለ (አረጀ) የሚባለው ስንት ሺህ አመት ሲሞላው ይሆን? አማካሪ ምናአልባት ‹‹ሳንፈልጋቸው ሃያ አመታቸው›› የሚል መዝሙር በታላቁ ሩጫ ላይ አልሰሙ ይሆን?
እሺ! ተደጋጋሚ ጊዜ ኢህአዴግ ‹‹ስልጣን ከለቀኩ ሀገሪቱ ትበታተናለች›› የሚል ንግርት ሲናገር ይሰማል፤ ወይም ያስነግራል፡፡ በርግጥ ንግርቱ የነቢያት አይደለም የፖለቲከኞች እንጂ፡፡ የንግርቱ አንጓ ‹‹ስራ አጣው፣ ተራብኩ፣ የራሴ የምለው ነገር የለኝም…›› ለሚሉ ህዝባዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት አርባ እና ሀምሳ አመት ታገስ የሚል ነው፡፡ እናም በዚህ ንግርት እያስፈራሩ 40፣ 50፣ 60… እያሉ መቀጠል ነው፡፡ ይህ ንግርት ለተወሰነ ጊዜ የሰራ ወይም ያደናገረ ይመስለኛል፡፡ አሁን ግን የንግርቱ አዋጭነት እያለፈበት ነው፡፡ ፋሲል ግን እንዲያልፍበት የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ እናም ንግርቱን ‹‹ህገ መንግስት›› የሚባል የዳቦ ስም ሰጥተው እንደገና ለገበያ የማቅረብ ፍላጎታቸውን እንዲህ ሲሉ ይገልፁታል፡-
‹‹ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚባለው ሕገ-መንግስቱ ሲረቀቅ በህዝቦቿ የእኩልነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ሲሰነዝሩ የነበሩትን አንዳንድ ትችቶችን እንደገና ለማንሳት ከሆነ የተጣለውን ጽኑ መሰረት ማነቃነቅ ይሆናል፡፡ ይህንን መሞከር የህዝቦቿን መሰረታዊ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥቅም የሚፃረር በመሆኑ ጥያቄው ከመነሻው ውድቅ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል፡፡›› እንዴት ነው ነገሩ? ሕግ-መንግሥቱ ራሱ እርሳቸው የጠቀሷቸው ቅሬታዎችን የሚንተራሱ አንቀፆች እንዴት ሊቀየሩ እንደሚችሉ ለስሙ ያህል ህጋዊ ማዕቀፎችን አመቻችቶ ሳለ፣ ይህ የአማካሪው ሃሳብ ከምን እንደመጣ ለማዋቅ ያስቸግራል፡፡ ኧረ ጠንቋይ መሆንም የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡
እርሳቸው በቀዳሚነት ያረቀቁትን የደርግ ሕገ-መንግስት አልቀበልም ብሎ በኢህአዴጎች አነጋገር ‹‹የደርጉን ሕገ-መንግሥታዊ ስርዕት›› በኃይል ንዶ የመጣን ስርዕት እያማከሩ ባሉበት በዚህ ወቅት ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንዲሉ እርሳቸው ያነቆለጳጰሱትን ‹‹ሕግ-መንግስታዊ ስርዕት›› በጠመንጃ እናፈርሳለን የሚሉ ፖለቲከኞች በአንዳንድ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች መንገድ እንደጀመሩ እየሰማን ነው፡፡ ይህን መሰሉን ነገር ስናስተውል የሰውየውን ጀርባ ከሀገራችን ሰላም እጦት ጋር አያይዘን ብንጠረጥር ወንዝ ባንሻገር እንኳ ምንጭ እንሻገራለን፡፡
አሁን ደግሞ ወደ አማካሪው ምላሽ እንመለስ፡፡ በጣም ጥሩ፣ አማካሪ! ቀጥሉ ቀጥሉ እየሰማንዎ ነው ‹‹ዛሬ በፈጣን ለውጥ እያለፍን ባለንበት ወቅት ሕገ መንግስቱ ሊሻሻል ይገባል የሚል አመለካከት ካለም ይህንን ፈጣን ለውጥ ያመጣው ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ይህንን በጥልቀት ማየት ተገቢ ነው፡፡ ….በአገር አቀፍ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስላልቀናቸው ህገ መንግስቱ ሊሻሻል ይገባል የሚል አመለካከት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው ህዝቡ የሚበጀውን የሚመርጠው፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህዝቡን የልብ ትርታ የማዳመጥ ይህንን ለመፈፀምም በቁርጠኝነትና አቅምን በማዳበር መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡ በእኔ አመለካከት ዋና ትኩረታችን መሆን የሚገባው በሚሻሻል ላይ ሳይሆን ህገ-መንግስታችንን በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በየፊናችን መሯሯጥ ላይ ነው፡፡›› …ኦኦኦ እፁብ ድንቅ፡- አማካሪ!
ግን ስንቱን ህገ-መንግስት ለማስፈፀም ይሯሯጣሉ? ኢህዴሪና ኮለኔል መንግስቱን በስንት ትግል፣ በስንት መስዋዕትነት ባናወርዳቸው ኖሮ ዛሬ የሚመክሩን ሌላ ነበር፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር፣ ወያኔ ወንበዴ ነው፣ አስገንጣይ ነው…›› ወዘተርፈ፤ ብቻ በደርግ ጊዜ የምንሰማቸውን እንሰማ ነበር፡፡ ሆኖም ደርግን ብንገላገል፣ አማካሪ ፋሲል ደግሞ የደርግን ሰማያዊ ካኪ ቀይረው ኢህአዴግን እና መለስን ‹‹በፍፁም ልብህ ውደድ›› ሲሉ ይመክሩናል፡፡ ነገ ደግሞ ሌላው ቢመጣ አማካሪ ምን ተዳቸው! ኮራ፣ ዘና ብለው ምክራቸውን ማካፈል ነው፡፡ ….ማኪያቬሊ ሆይ፡- ‹‹በሰው ቁስል…›› ያልከው አንተ ትሆን እንዴ?
በርግጥ ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር መለስ ተጠያቂ ለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ አማካሪውም የድርሻቸውን መውሰዳቸውም እንዲሁ አይቀሬ ነው፡፡
…አንድ ታሪክ አለ፡፡ በአባቱ እግር የተተካ ንጉስ ታሪክ፡፡ ንጉሱ ህዝቡ ለጠየቀው ጥያቄ በሀገሩ ያሉ አስተዋይ እና መልካም መካሪዎች የመከሩትን መልካም ምክር በመተው ጓደኞቹን ያማክራል፡፡ ጓደኞቹም ‹‹ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ…›› ብለህ መልስላቸው ሲሉ ይመክሩታል (የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መሰለኝ) የሆነ ሆኖ አዲሱ ንጉሥ መካሪዎቹ የመከሩትን ለህዝቡ መለሰ፡፡ ህዝቡም ሆ ብሎ አመፀ፣ ስልጣኑንም በአንድ ቀን አጣ፡፡
የሳምንት ሰው ይበለን፣ ቀጣዩን ሳምንት እመለስበታለሁ