ኃይሉ ሻዉል ቢሮ ተቆልፎባቸው በበረንዳ በመሰብሰብ ሹመት ሰጡ

የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ፣ ትልቅ ቀዉስ ዉስት እንደገባ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመልክታል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ሻዉል ከሃላፊነታቸዉ እንደሚነሱ በተደጋጋሚ ካሳወቁ በኋላ እንደገና ሊቀመንበር ሆነዉ በቅርብ መመረጣቸዉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በድርጅቱ አመራር አባላት ዉስጥ ከፍተኛ ዉዝግቦችና አለመግባባቶች እንደተፈጠሩ የደረሰን ዘገባ ሲያክል፣ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለሶስት መከፈሉንም ለማረጋገጥ ችለናል።

ኢንጂነር ኃይሉ ሻዉል፣ በቅርቡ ድርጅቱን የተቀላቀሉት ዶር ያእቆብ ሌኬ እንዲተኳቸዉ ይፈልጉ የነበረ ሲሆን ዶር ያእቆብ፣ በአብዛኛዉ የመኢአድ አባላት ሊመረጡ እንደማይችሉ በተረዱ ጊዜ ፣ «እለቃለሁ» ያሉትን ሃሳብ ቀይረዉ እንደገና የድርጅቱ ሊቀመንበር መሆናቸዉ፣ ሌሎች የአመራር አባላትን ማስቆጣቱና ማሳዘኑን የሚገልጸዉ የደረሰን ዘገባ፣ አቶ ኃይሉ በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ የከረረ አለመስማማቶች እንደተፈጠሩ አክሎ ያትታል።

አቶ ኃይሉ በዛሬው ቀን በመኢአድ ጽ/ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ ሲመጡ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ማሙሸት አማረ ከሌሎች የአመራር አባላት ማለትም ዶ/ር ታዲዎስ ታኑና ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ጽ/ቤቱን ቆልፈዉ የሄዱ ሲሆን ኢንጂነር ኃይሉ ከጥቂት አጋሮቻቸዉ ጋር በጽ/ቤቱ ደጃፍ፣ በዉጭ ፣ አጭር ስብሰባ አድርገዉ የድርጅቱን ዋና ጸሃፊ የሆኑትን አቶ ማሙሸት አማረ ምትክና ፣ እንዲሁም ዶር ታዴዎስ ታንቱ እና ዶር በዛብህ ደምሴን ምትክ ከደጀን እና ከትግራይ የመጡ በቅርብ የሚያወቋቸዉን ግለሰቦች የደርጅት ጉዳይ ሃላፊና ዋና ጸሃፊ አድርገዉ መሾማቸዉንም ለማረጋገጥ ችለናል።

በመኪና ዉስጥ ዶር ያእቆብ ሌኬ እና ነባር የመኢአድ አንጋፋ አመራር አባል፣ አቶ ወልደጻድቅ መህከል ባለፈው ሳምንት አለመስማማታቸዉ ከሮ፣ አካላዊ ግብግብ መፍጠራቸዉንም የደረሰን ዘገባ ያትታል።

በአቶ ማሙሸት አማረ፣ ዶር ታዴዎስ ታንቱ፣ አቶ ወልደጻድቅ እና ዶር በዛብህ ደምሴ የሚገኙበት በርካታ የአመራር አባላትን ያቀፈዉ ቡድን፣ ከዚህ በኋላ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ገና ያልታወቀ ሲሆን አቋሙን በቅርብ ያስታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የአቶ ኃይሉ ሻዉልም ሆነ የዶር ታዴዎስ ቡድኖች ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጋር አብሮ ለመስራት ብሎም ለመዋሃድ ፍላጎት ያላቸዉ ሲሆን ሰሞኑን የተፈጠረዉ የከረረ አለመስማማት መኢአድ ከአንድነት ጋር የሚያደርገዉ ዉህደት የበለጠ ያወሳሰነዋል ተብሎም ይገመታል።

«አቶ ሃይሉ ሻዉል እለቃለሁ እንዳሉ ቢለቁ ኖሮ ይሄ ሁሉ ችግር አይመጣም ነበር። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ድርጅቱ የሚመራዉን መርጦ መቀጠል ይችል ነበር» ያሉን ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ኢንጂነር ኃይሉ አንጋፋ የደርጅቱ አመራር አባላትን አግለዉና አባራዉ ምንም አይነት የረባ ነገር ሊሰሩ እንደማይችሉም ይናገራሉ። «በዚህ እድሚያቸዉ እንደ አባት፣ እንደ መሪ፣ ሁሉን አስማምተዉ፣ አቀራረበዉ መልቀቅ ሲገባቸዉ፣ ጭራሹና በርሳቸዉ ምክንያት መኢአድ እንደዚህ መታመሱ አሳዛኝና አሳፋሪ ነዉ» ሲሉም አስተያየታቸዉን ይቋጫሉ።

በተያያዘ ዜና ከአመታት በፊት ከድርጅቱ የተባረሩት የቀድሞ የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ የነበሩት ወ/ሮ መሰበ ወርቅ በመኢአድ ዉስጥ የተፈጠረዉ አለመግባባት በመታዘብ ከጥቂት ወደጆቻቸዉ ጋር «የመኢአድ መፍትሄ አስፈላጊ» ኮሚቴ በሚል ስም መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ለማወቅ ችለናል። ይህ ወ/ሮ መሰበ ወርቅ የሚመሩት ቡድን፣ ከዉጭ የነበረና ላለፉት ሁለት ሶስት አመታት የት እንደነበረ የማይታወቅ ቡድን ሲሆን፣ ለሁለት የተከፈለ የሚለዉን አሁን ያለዉን የመኢአድ አመራር «ድርጅቱን እያደማ» ያሉ ሲልም መክሰሱን ከስፍራዉ የደረሰን ዜና ያመለክታል።

ይህ ቡድን ለሕዝብ በበተነዉ አምስት ገጽ ወረቀት በተለይም አቶ ኃይሉ ሻዉል «አምባገነን» እና «ዲሞክራሲን የገድሉ» ፣ መኢአድን የገዥዉ ፓርቲ አጫፋሪና ደካማ እንዲሆን ያደረጉ ሲልም ይከሳል።

መኢአድ ከመድረክ ጋር አብሮ መሥራት የለብትም የሚል አቋም ያለዉ ይህ ቡድን የመኢአድ አሁን ያሉት አመራር አባላትን ፣ ሃብትንና ንብረት ለሌሎች በተለይም በብሄር ለተደራጁ አሳልፎ መስጠት እንደማይገባ አጥብቆ ያሳስባል።