“እንደምን አደሩ አቶ መለስ?… ተልባ እየዘራሁ ነው”
ከደረጀ ሀብተወልድ-ሆላንድ
አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን ለፓርላማቸው የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ከብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ከአቶ ግርማ ሰይፉ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን “መልሶች” አዳመጥኩ።አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ፤በብዙዎቹ ነጥቦች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ግርማን ሊያገኟቸው አልቻሉም።
አቶ ግርማ ፦”ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደምን አደሩ?” ሲሏቸው፤ አቶ መለስ፦”ተልባ እየዘራሁ ነው” ሲሉ ነው የተስተዋሉት።ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ፦”ክቡርነትዎ! ከፍየልና ከበግ ስጋ የማንኛቸው ይጣፍጣል?” ሲሏቸው፤አቶ መለስ፦ “የዓሳ ስጋ ያሙለጨልጫል” ሲሉ ነው የተደመጡት።” ሊቁ “ጠቅላይ ሚኒስትራችን፦ላም ባልዋለበት ነው፤ኩበት ሲለቅሙ የዋሉት።
የተወሰኑ ነጥቦችን ብቻ በማንሳት በአጭሩ ላሳይ፦
-ከአቶ ግርማ ጥያቄዎች አንዱ፤ ከኦጋዴ ነፃ አውጭ ግንባር ተዋጊዎች ጋር በተያዙት የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የ 11 ዓመት እስር ሲበየን፤ በ ኢሜይል ሀሳብ ሲለዋወጡ ተይዘዋል በተባሉት ኢትዮጵያውያን ላይ የ 14 እና የ 19 ዓመት እስራት መበየኑን እንዴት ያዩታል?”የሚል ነው።
አቶ መለስ ለዚህ መልስ ሲሰጡ፦” የኢትዮጵያዎቹ ብዙ ዓመት ተፈርዶባቸው ፤የስዊድን ጋዜጠኞች እንዴት 11 ዓመት ብቻ ይፈረድባቸዋል?” የሚል ቅሬታ ሲቀርብልን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ። እስከዛሬ ድረስ ስዊድናውያኑ ጠቅላላ መታሰር የለባቸውም የሚል ተቃውሞ ነበር የሚቀርብብን፤ ዛሬ ግን ፍርዱ ያንሳቸዋል የሚል አዲስ ነገር ነው የሰማነው፤…”በማለት ነው የጀመሩት።
አቶ መለስ ይህን ሲሉ ወዲያው በአዕምሮዬ የመጣብኝ፤ በምርጫ 97 ዋዜማ በአንድ የፓርቲዎች የክርክር መድረክ ላይ በኢህአዴግና በቅንጅት መካከል የተደረገ ክርክር ነው። በመድረኩ ኢህአዴግን በመወከል ለክርክር የቀረቡት አቶ በረከትና አቶ ጁነዲን ሲሆኑ፤በቅንጅት በኩል ደግሞ ዶክተር ብርሀኑ ነጋና ዶክተር ሙሉ ዓለም ታረቀኝ ናቸው።…በክርክሩ መሀል አቶ ጁነዲን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሆኑት ፓርቲዎች በህዝብ ፍላጎትና ምርጫ የቆሙ እንጂ፤ አንዳንዶች እንደሚሉት ህወሀት ተለጣፊ አድርጎ የፈጠራቸው እንዳልሆኑ በኩራት ሲናገሩ፤ ዶክተር ብርሀኑ ፦” ጁነዲን! በእርግጥ ከልብህ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ይወክላል ብለህ ታምናለህ?” በማለት በአግራሞት ጠየቋቸው። በዚህ ጊዜ አቶ በረከት ቱግ ብለው፦”ዶክተር ብርሀኑ! እንዴት የጁነዲንን ኦሮሞነት ጥያቄ ውስጥ ትከተዋለህ?ጁነዲንን እንዴት ኦሮሞ ነህ ወይ?ብለህ ትጠይቀዋለህ?”አሉ። ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ ወኪል አይደለም ብሎ ማመን-እንዴት ሆኖ “ጂነዲን ኦሮሞ አይደለም” ማለት እንደሚሆን እናንተው ፍረዱት።አቶ በረከት ግን በግልጽ፣ በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ክርክር ላይ እንደዛ ሲሉ፤ቢያንስ ክርክሩን የሚከታተለው ህዝብ ምን ይለኛል?አላሉም።ለካ የአቶ መለስ ደቀ-መዝሙር ኖረዋልና።
“እንትናዬ፤ እገሌን ባየሁት ቁጥር ሁሌ አንተ ትዝ ትለኛለህ”
“ይህን ያህል እኔና እሱ እንመሣሰላለን?”
“እሱም እንዳንተ መቶ ብር ተበድሮኝ አልመለሰልኝም”
በቅን ዓይን ካየነው፦“በስዊድናውያን ጋዜጠኞች ላይ 11 ዓመት ተፈርዶ፤በኢትዮጵያውያኑ ላይ ከፍ ያለ መፈረዱን እንዴት ያዩታል? ማለት’ በስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የተፈረደው ለምን ከፍ አላለም? ማለት አይደለም። ጥያቄው ሳይጨመርበት፤ሳይቀነስበት የፍትህ ጥያቄ ነው።”ሁሉም ፈፅመዋል ከተባሉት ጥፋት አኳያ፤ የተሰጠው ፍርድ ፍትሀዊ ነው ብለው ያምናሉ ወይ?” ነው ጥያቄው። ይህን ጥያቄ አጠጋግተን መተርጎም ካለብን፤ ሊሆን የሚችለው ከኦብነግ ተዋጊዎች ጋር በተያዙትና ያለ ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ በገቡት ላይ፤ የ 11 ዓመት ፍርድ ከተላለፈ፤ ሀሳባቸውን በኢንተርኔት በተለዋወጡት ላይ ከዛ ያነሰ ፍርድ መሰጠት ነበረበት የሚል ነው። ጥያቄው መተርጎም ካለበት ሊጠጋጋ የሚችለው ወደዚህ ነው። ይህን ያልኩት፤ እኔም እንደ አቶ መለስ ወደፈለግኩት በመሳብ አይደለም-ይልቁንም አቶ ግርማ ጠቅላላ ተከሳሾቹ መፈታት አለባቸው የሚል አቋም እንዳላቸው ስለማውቅ እንጂ።
አቶ መለስ ግን ጥያቄውን ወደራሳቸው ሀሳብ ስበው በማስገባት፤ በግልባጩ መለሱ።
ታዲያ በሸንጎ መሀል የተወራውን እዚያው እየጠመዘዙ ሌላ መልክ በማስያዝ የሚተረጉሙ ሰዎች፤በእልፍኝ ውስጥ ስለ ቀዶ ህክምና “ኦፕሬሽን” የተወራውን፤ ወደ ትግል “ኦፕሬሽን” በመቀየር፦- ህገ-መንግስት በመናድ፣በሽብርተኝነት፣በአገር ክህደት…እያሉ የክስ ናዳ ቢያዥጎደጉዱ ምን ይገርማል?
አቶ ግርማ፦”እንደምን አደሩ አቶ መለስ?”
አቶ መለስ፦”ተልባ እየዘራሁ ነው”
– ሁለተኛው የአቶ ግርማ ጥያቄ በአዲሱ የ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ የክዋሜ ንክሩማ ሐውልት ሲቆም፤የአፄ ሀይለሥላሴ ሀውልት አለመቆሙ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል።የውስጥ አለመግባባታችን በአህጉር ደረጃ መገለጫ እሰከመሆን እንደደረሰ የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው የሚል ነው።
ልብ በሉ! የአቶ ግርማ ጥያቄ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ትኩረት ያደረገው በአፍሪካ ህብረት ዙሪያ ነው። በቻይና መንግስት አዳራሽ የተሠራውም፤ ለአፍሪካ ህብረት ነው።የክዋሜ ንክሩማ ሐውልት የቆመውም ፤ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ነው። ጥያቄው ለአፍሪካ ህብረት፤ ከ ዓፄ ሀይለሥላሴና ከክዋሜ ንክሩማ ማን ይቀርባል?” የሚል ነው። ጥያቄው ዓፄ ሀይለሥላሴ የአፍሪካ ህብረት መስራችና አባት ሆነው ሳለ፤ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሲያሰራ እንዴት ተዘነጉ?”የሚል ነው።አራት ነጥብ።ለዚህ ጥያቄ፦”ለፓን አፍሪካኒዝም እንደ ክዋሜ ንክሩህማ የታገለ የለም” ማለት፤ ምን የሚሉት ምላሽ ነው።
(ደግሞም ፤ባቀፈቻቸው 54 አገሮቿ ውስጥ ከ 800 በላይ ጎሳዎች ባሏትና በጎሳዎቿ ቁጥር ልክ በግጭት በምትታመሰው አፍሪካ ፤የፓን አፍሪካኒዝም መፈክር ያተረፈው ነገር ቢኖር፤”ላም አለኝ በሰማይ…” የሚልን ተረት ብቻ ነው። ከዚህ አኳያ…የየራሳቸውን አገር ሰላምና አንድነት ማስጠበቅ ተስኗቸው በስጋትና በቋፍ ላይ ያሉ መሪዎች፤ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ፊት የምስክር ሐውልት ለማቆም የፈለግነው ፤ለዋነኛው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ነው ቢሉ፤ግብዝነት ይባል ካልሆነ በስተቀር ራዕይን የሚያመለክት አይደለም)
አቶ መለስ በዚህ ነጥብ ዙሪያ እያጠጋጉ የዘለሉት፤ ከአፍሪካ ህብረት ፦ወደ ፓን-አፍሪካኒዝም ብቻ አይደለም- ለማብራራት እንዲመቻቸው ከሀይለ-ሥላሴ ፦ወደ መንግስቱም ዘልለዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት አቶ ግርማ የጠየቁት፦”ለምን የዓፄ ሀይለሥላሴ ሐውልት አልተሰራም?” የሚል ነው።ስለ መንግስቱ ፈፅሞ ያሉት ነገር የለም። አቶ መለስ ግን ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ ፤ሀይለሥላሴም፣መንግስቱም ለአፍሪካ ህብረት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው የሚካድ እንዳልሆነ በማውሳት፤”ሆኖም መንግስቱ በአገር ውስጥ የፈፀመውን ጭፍጨፋና፤የሠራውን ወንጀል እናውቀዋለን፤ እንኳን ሐውልት ተጨምሮበት ራሱ ተራራ ነው”የሚመስል ነገር ተናገሩ። ለመንግስቱ ሐውልት ይሠራለት ብሎ የጠየቀ ሳይሆን፤ለመጠየቅ ያሰብ በሌለበት ነው አቶ መለስ እንዲህ ያሉት። አጠጋግተው ወደሚመቻቸው ዘለሉ ያልኩት ለዚህ ነው።
ጥያቄ ፦በአፍሪካ ህብረት- የህብረቱ መስራች ለሆኑት ሐውልት ያልቆመው ለምንድነው?
መልስ፦እንደ ንዋሜ ክሩህማን ለፓን አፍሪካኒዝም የታገለ የለም።
ጥያቄ ፦ የዓፄ ሀይለስላሴ ሐውልት ለምን በህብረቱ አዳራሽ አልታነፀም?
መልስ፦”መንግስቱ የሰራው ወንጀል፤እንኳን ሐውልት ተጨምሮበት፤ራሱ ተራራ ነው”
-ከዚሁ ጋር የተያያዘው የአቶ ግርማ ሌላው ጥያቄ፤የአፍሪካ ህብረት ዓለም በቃኝ እስር ቤት የነበረበት ቦታ ላይ መገንባቱን አስመልክተው አቶ መለስ በህብረቱ ስብሰባ ያሰሙትን ንግግር የተመለከተ ነው።”መንግስትዎ ዜጎችን በሆነ ባልሆነው ማሰር ባላቆመበት ሰዓት፤ የአፍሪካ ህብረትን- ዓለም በቃኝ የሚባል እስር ቤት በነበረበት ቦታ ላይ ሠራነው ማለቱ ፤የስም ካልሆነ በቀር የተግባር ለውጥ የለውም” እያሉ ለሚተቹዎት ምን መልስ አለዎት?”የሚል ።
አቶ መለስ በሰጡት መልስ ግን፦” አቶ ግርማ ፤እስር ቤት ለምን ይኖራል? ጠቅላላ መኖር የለበትም!” እያሉ ከሆነ፤እስር ቤት የሌለው መንግስት ስለመኖሩ በታሪክ ሰምተን አናውቅም። መንግስት እስካለ ድረስ፤ እስር ቤት ሊኖር ግድ ነው…” እያሉ ነው መዝለል የጀመሩት።
የአቶ ግርማ ጥያቄ ጭብጥ ፦” መንግስትዎ ዜጎችን በፈጠራ ክስ በገፍ እያሠረ ባለበት ሰዓት፤ በዓለም በቃኝ እስር ቤት ላይ የ አፍሪካ ህብረትን ሠራንበት ማለትዎ፤ መመፃደቅ ካልሆነ በቀር፤ምን ትርጉም ይሰጣል ?” የሚል ነው።የአቶ መለስ መልስ ደግሞ፦”መንግስት ባለበት አገር እስር ቤት ሊኖር ግድ ስለመሆኑ፤ስለ ዲሞክራሲያዊና አምባገነናዊ ስርዓት እስር ቤቶች…ወዘተ ዙሪያ ጥምጥም የሄደ ነው።
በነገራችን ላይ የዚህ ዓይነት ከንቱ መመፃደቅ የአምባገነኖች መለያ ባህርይ ነው። ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ አገዘዝ ስር በነበረችበት በአንደኛው ዓመት በጠቅላላ አገሪቱ ውስጥ፤ ከ5ሺህ በላይ ጥቁሮች ታስረው ነበር። በዚህም ምከንያት ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች፦”እንዴት 5ሺህ ጥቁሮች፤ በነጮች ይታሠራሉ ?”በሚል ስሜት ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተደምጠዋል። በጣም የሚገርመው ታዲያ እነዚያ የአፍሪካ መሪዎች በነጮች ለታሰሩት 5ሺህ ጥቁሮች ሺጮኹ የነበሩት ፤ በዚያኑ ዓመት በየአገሮቻቸው በትንሹ በደቡብ አፍሪካ ከታሰሩት ሶስትና አራት እጥፍ የሚያህሉ ዜጎቻቸውን በወህኒ አጉረው ነው።ይህ ነው ግብዝነት ማለት- በራስ ዓይን ላይ የተጋደመን ምሰሶ ሳያነሱ፤ ወደ ሌሎች ጉድፍ መጠቆም።
አቶ መለስም ያደረጉት ይህንኑ ነው።አዎ!ትንሹን ትልቁን፤ሴቱን ወንዱን፤ጋዜጠኛውን፤ተቃዋሚውን በፈጠራ ክስ በጅምላ እያሰሩ፤ ስለ ደርግ አሳሪነት ማውራት ግብዝነት ነው።በምርጫ 97 ጊዜ የተገደሉትን ዜጎች አስከሬናቸውን ወስደው ለመቅበር ቤተሰቦቻቸው 50 ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ገና ሳንረሳው፤ ደርግ ከገደለ በሁዋላ ስለሚያስከፍለው 11 ብር እያወሱ “ፃድቅ”ለመምሰል መሞከር፤ፈሪሳዊነት ነው።ለዚህም ነው አቶ መለስ፦”የአፍሪካ ህብረት በዓለም በቃኝ ላይ ተሠራ”ካሉት ይልቅ፤ ፕሮፌሰር መስፍን፦”አፍሪካ ህብረት፤ዓለም በቃኝ ገባ” ያሉት የተስማማን።
-የአቶ ግርማ ሌላው ጥያቄ የፀረ-ሽብር ህጉ በመሰረታዊ ነፃነቶች ላይ የተቃጣ እንደሆነ የጠቆመ ፤በአፈፃፀም ደረጃም ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት ሊፈፀም እንደሚችል የዛሬ ዓመት አንስተውት የነበረው ስጋት በተጨባጭ እየታየ መሆኑን የሚያመለክት ነው።
አቶ መለስ ለዚህ ሲመልሱ፤ህጉ በዲሞክራሲ ከዳበሩት አገሮች “ኮማ”እንኳ ሳይቀር ተለቅሞ የተቀዳ መሆኑን፤ እንደውም በአንዳንድ ነጥቦች ካደጉት አገሮች የተሻለ አድርገው እንደቀረፁት ተናገሩ። “በጄ” እያልኩ ካደጉት አገሮች ለመሻሉም እንደሚከተለው አንድ ማሳያ ጠቀሱ፦
“ለምሳሌ በአሜሪካ አንድ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ሽብርተኛ ተብሎ የሚወሰነው በሥራ አስፈፃሚው ደረጃ ሲሆን፤ እኛ ግን ይህ ጉዳይ ሰፋ ተደርጎ መታየት አለበት በማለት በ”ፓርላማ” ደረጃ ነው እንዲወሰን ያደረግነው። እንደነሱ አላጠበብነውም”
ቂቂቂቂቂ…..ቂቂቂቂቂ….. “ሲሉ ሰምታ ለስሟ መጠሪያ ቁና አሰፋች”አሉ መምሬ አከለ?
እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር መለስ ይህን ሲሉ፤ ስለ ሌላ አገር ፓርላማ የሚያወሩ መምሰላቸው ነው።
የኢትየጵያ ፓርላማ ከዋሽንግተን አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ፤ በኢህአዴግ አሻንጉሊቶች የተሞላው ፓርላማ-ከኦባማ ካቢኔ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ውሳኔ ያሳልፋል ነው ያሉት። በአደባባይ እንዲህ ማለት ማበድን፤አለያም መጃጀትን ካልሆነ በስተቀር፤ ብልጠትን አያመለክትም።
በእርግጥም ከዚሁ ጋር ተያይዞ አቶ ግርማ፤ ድርጅታቸው ስብሰባ ሲያካሂድ የሚቀረፁት ቪዲዮዎች ፤ በመንግስት ሰዎች በኤዲቲንግ እየተቆራረጡና ሌላ ትርጉም እየተሰጣቸው ንፁሀንን ለመክሰሻ እየዋሉ እንደሆነ ላነሱት ቅሬታ አቶ መለስ የሰጡትን ምላሽ ሳዳምጥ፤ “መለስ እየጃጁ ይሆን?”የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሮብኛል።
በአጭሩ ያሉት፦”አዲስ አበባ ውስጥ በየቀኑ እጅግ ብዙ የሰርግ ቪዲዮዎች ሲቀረፁ ነው የሚውሉት።ቪዲዮ የምትቀርፁት እናንተ ብቻ አይደላችሁም። .. ቪዲዮ መቅረፅ ተቸግረናል የሚለው ስህተት ነው..”የሚል ነው።
የአቶ ግርማ ጥያቄ፦” በፖለቲካዊ ድርጅት ውስጥ የሚደረግን ስብሰባ በነፃነት ለመቅረጽ የተቸገርንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” የሚል ሲሆን፤አቶ መለስ የሰጡት መልስ፦” የሰርግ ቪዲዮ መቅረፅ ይቻላል”የሚል ነው። በዚህ ጊዜ ነው ፦”አቶ መለስ ይህን ያሉት፤ ሆነ ብለው በተዘዋዋሪ መንገድ በነፃነት መሰብሰብ አትችሉም፤ፖለቲካችሁን አቁማችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ እያሏቸው ይሆን? ወይስ ጃጅተው ይሆን ?”የሚል ጥርጥሬ የተፈጠረብኝ።
ከዚህም በላይ ብዙ ነጥቦችን በማንሳት መተቸት የሚቻል ቢሆንም፤እንዳላሰለቻችሁ በዚሁ ላቁም።
በእርግጥ አቶ መለስ ስላልተጠየቋቸው ጥያቄዎች ሲያብራሩ የዋሉት፤ መርሳት ጀምረው ይሆን እንዴ?
ዶክተር፦”ምንዎን ነው ያመመዎት?”
ህመምተኛ፦”አልዛይመር(የመርሳት በሽታ ነው የያዘኝ)
ዶክተር፦”መቼ ነው የጀመረዎት?”
ህመምተኛ፦”ምኑ?” (እዛው ረሱት)
–