ቋሚ የችርቻሮ ዋጋ ተመን ይፋ ተደረገ

የንግድ ሚኒስቴር ከታህሣስ 28 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚኾን ቋሚ የችርቻሮ ዋጋ ተመን ይፋ አደረገ፡፡ በመላው አገሪቷ የሚገኙ የችርቻሮ መደብሮች በአጠቃላይ አዲሱን የዋጋ ተመን ዝርዝር እንዲለጥፉ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ዛሬ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ከንግዱ ማኀበረሰብ ጋር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ባደረገው ውይይት እንደገለፀው መሠረታዊ በሚባሉ ዋና ዋና የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ሸቀጦች የዋጋ ተመን ወጥቶላቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በምግብ ዘይት፣ በዳቦ፣ በፓስታና መኮረኒ፣ በሥጋ፣ በስኳር፣ በብርቱካንና ሙዝ፣ በሳሙና፣ በቆርቆሮ፣ በብረታ ብረት፣በመድኃኒትና በሌሎች 18 ዓይነት ምርቶች ላይ የችርቻሮ ዋጋ ተሰልቷል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ስኳር በኪሎ 14 ብር፣ ሩዝ በኪሎ  12 ብር ከ40 ሳንቲም ፣  የልብስ ሳሙና ባለ 200 ግራም  አምስት ብር እንዲሁም ስጋ አንድ ኪሎ 52 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል።

ይህ እርምጃ መንግስት ለ19 ዓመታት ሲናገርለትን የነበረውን “አፍአዊ” የነጻ ገበያ ትርክት አፈር ማልበሱን ያወጀበት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማታዊ መንግስት ወግ መነገር ከጀመረበት ወቅት ወዲህ ደግሞ የኢሕአዴግ የገበያ ሥርዓት ለውጥ ትልቁ እርምጃ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት የችርቻሮ መደብሮች የዋጋ ተመኖችን ዝርዝር እንዲለጥፉ መንግስት ማስገደዱ የሚታወስ ቢኾንም የዋጋ ተመን ላይ ተሳትፎ አልነበረውም፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚነገረው የነጋዴዎች ያልተገባ የንግድ ጠባይ ለኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት ቢኾንም ኢኮኖሚው ከማህበረሰቡ የሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ አቅርቦት አለመፍጠሩ ዋነኛ ችግር ነው፡፡ ኢኮኖሚው በተገቢው የእድገት ምእራፍ ላይ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ  የሚናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት ላለፉት አምስት አመታት ያለሟቋረጥ የሚያሰግረውን የዋጋ ግሽበት መግታት ወይም ባለበት ማቆም አልቻሉም፡፡ ይህም የማኀበረሰቡን ጥሪት ከማሟጠጡም ባሻገር አገሪቷ ተገቢውን የቁጠባ አቅም እንዳታዳብር ምክንያት ኾኗል፡፡