የጥቃት ኢላማ የሆነው የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ከሳሙኤል ሽፈራው)

ይህ ፌደሬሽን በሂውስተንና በዳላስ ሁለት ቡድኖች ተመሰረተ። በቀጣዩ አመት ዳላስ ጨዋታው ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳ በመሄድ የታደምሁ ነኝ። ይህ ፌደሬሽን ሲመሰረት ሁሉም እንደሚያስታውሰው ከቀይሽብር አምልጠውና ተርፈው የመጡ ስደተኞችና ትቂት በዚሁ በዳላስና ሄውስተን አካባቢ ለትምህርት መጠው የቀሩ ወገኖች የጀመሩት ነበር። በቀጣይ አመታት ከተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ከተሞች የተመሰረቱ ቲሞች ወደፌደሬሽኑ በመቀላቀል እድገት እንዲያገኝ አርገውታል። በየአመቱ በአሜሪካ የነጻነት ቀን ሰንበት የሚካሄደው የፌደሬሽኑ የእስፖርት በአል ላለፉት 28 አመታት ለኢትዮጵያውያን ልዩ የሆነ የአመት በአል በመሆኑ፤ ሳምንቱን ብዙ ወገኖች በጉጉት ይጠብቁታል። በ1980 ወቹ አመታት አገራችን በደርግ ስርአት ስር ስለነበረች፤ በጊዜው የነበረው አንባገነን ይህን ፌደሬሽን በክፉ ይመለከተው እንደነበርም የሚዘከር ነው።

 

ወጣም ወረደ ወደስደት የወጣው ወገን የመሰረተው ይህ የስፖርት በአል፤ በምሳሌነቱ ተቀናቃኞች ሳይቀሩ የመሰከሩለት በመሆኑ፤ የወያኔ አስተዳደር አገራችንን ከተቆጣጠረ በኋላ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን አንድነት በከፍተኛ አሰባስቦ ያሳየ ከዚህ ድርጅት በላይ አልነበረም። አንዳንድ ዘረኞች ምንም እንኳን ባይሳካላቸውም እሱን የመሰለ ለመፍጥር ሞክረዋል። ከነዚህ የዘረኛ ቡድኖች መካከል የሐረሪ የስፖርት ፌደረሽን በሰሜን አሜሪካ፡ የኢርትራ የስፖርት ፌደሬሽን የሚጠቀሱ ናቸው። ሆኖም በኤርትራውያን ያኔ የትግራይ ወገኖቻችንን ነጥሎ ለማካሄድ የተሞከረው ከመጀመሪያው ሳይሳካ በመቅረቱ ኤርትራውያኑ ለብቻቸው መቀጠሉን በመወሰን አሁንም በየአመቱ ቢካሄድም የዚህን አንጋፋ ማህበር ያክል ሊደምቅ አልቻለም።

 

እንደግለሰብ እኔ የዚህ ቀን አክባሪና ተጠቃሚ በመሆኔ፤ ሳምንቱን በጉጉት እጠብቃለሁ። እዚህ የተወለዱ ልጆቼ የዚህን አመታዊ ሳምንት በጉጉት ይጠብቁታል። በየግዜውም አመቱን ለማክበር የሚያስችላቸውን ወጭ በአመቱ ውስጥ ከሚያገኙት የስጦታም ሆነ ሌላ ገቢ ሰባስበው የመጓጓዣቸውን የሸፈኑባቸው ጊዚያት ብዙ ናቸው። የዚህ አይነቱ ተግባር በሁሉም ቤተሰብ እንዳለ ከቅርብ ወዳጆቸ ለማወቅ ችያለሁ።

 

የሰሜን አሜሪካ የስፖርት በአል ሌላው አቢይ ተግባር ወገኖች ለዚህ ሳምንት ተቀጣጥረው የሚገናኙበት በመሆኑ። ለአመታት ተለያይተው የኖሩ የትምህርትቤት ጓደኞች፤ የመንደር ልጆችና ዘመዳሞችን የሚያሰባስብ ወቅት ነው። ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህ የአመትበአል ተገናኝተው ፍቅር የመሰረቱ ወልደው ከብደውም የሚኖሩም እጅግ ብዙ ናቸው። የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰበአዊ መብትና፣የሙያ ማህበራት ስብሰባወችና፣የጓደኛሞች ጌት ቱጌዘሮች ሁሉ የሚከናወኑት ይህን አመታዊ በአል ጠብቀው ነው።

 

“ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” እንዲሉ ወያኔም ቢሆን ይህንን የአመት በአል አልተጠቀምበትም ማለት እንዴት ይቻላል። ግን ፖለቲከኞችና ፖለቲካ ነው ያበላሸው ለማለት ይከጅላል። መቸም ሁሉን ማፍረስ መቆጣጠርና በራሱ ስር ማዋል ይሁነኝ ብሎ የያዘው የመጋኛ ፖለቲካ መሆኑን እሱ ቢያለባብሰው ሌላው የሚስተው አይሆንም። ነውና፤ ለሦስት አስርት አመታት የዘለቀን ማህበር በቱጃር አላሙዲን አሽከሮችና ከየአካባቢው አጋጣሚውን ተጠቅመው መተያያ አገኘን ባይ አፋሽ አጎንባሾች ሊያፈርስ ብሎም በራሱ መልክ ሊሰራው ቢነሳ የሚያስገርም ሊሆን አይችልም። ይህ አይን ያወጣ የማናህሎኝነት ተግባር የዚህን ስርአት ምንነት ለማወቅ ጊዜም ሆነ ፍላጎቱ ያልነበራቸውን ስለሰበአዊመብትም ሆነ አገርና ወገን በደል ጊዜ ሰጠው ላልተከታተሉ በራቸውን ያንኳኳ በመሆኑ አዲስ ምእራፍ ከፋች ሆነ ብል የምሰሳት አይመስለኝም።

 

ላለፉት አያሌ አመታት በኢትዮጵያውያን ስብስቦች ሁሉ በአይነትና በይዘት ተሳክቶለት የቀጠለ ድርጅት; ዘር፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት፣ ጾታና እድሜ ልዩነትን ሳያደርግ፤ መላ ኢትዮጵያውያንን በአንድ መንፈስ (በኢትዮጵያዊነት) ያስቀጠለ። በዚሁ አመታዊ የእስፖርት በአል ለአመታት የተረሱ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ያኮሩና ያስመሰገኑ ወገኖችን ወደ መድረክ በማምጣት የሰራ። ይህን ተግባራዊ ክንዋኔ በመመልከት በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋና፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች ያላሰለሰ ተአማኒነት የለገሱት ኢትዮጵያዊ የሙያ ስብስብ ቢኖር ይህ የስፖርት ፌደሬን ብቻ ነው። ታዲያ ይህን ያየውና በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በነጻነት የሚኖር፣ የሚደራጅ በመሆኑ። በቅናት አይኑ የጦዘው ዘረኛ ቡድን የውጭ ደጋፊወቹን አሰማርቶ ለማፈራረስ ሞከረ።

 

የከሸፈው ጥቃት

እዚህ በምኖርበት ዳላስ ሁለት የእግርኳስ ቡድኖች አሉ። እንደእውነቱ ከሆነ የሁለቱንም ቲሞች ደጋፊ ነኝ። በየጊዜው የገንዘብም ሆነ የሞራል ድጋፌ እንዲሁም በየአመቱ ሜዳ ድረስ በመሄድ የቲፎዘነት ድጋፌን ሰጥቻለሁ። አስቡት ይህ ላለፉት 28 አመታት መሆኑ ነው። ታዲያ ፌደሬሽኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት ትልቁ ጥንካሬው ዘር፣ ሐይማኖት፣ ወይንም ጾታና እድሜ ልዩነትን ያላካተተ ትውልደ እትዮጵያውያንን ሁሉ የጨመረ መሆኑ ነው። በመሆኑም ልጆቸ እግር ከተከሉ ጀምሮ የኔነት ይሰማቸዋል። በየአመቱ የሚሄዱትና በየሜዳው አብረው በአሉን የሚያከብሩት የኔ ብለው ስለሚያምኑ ነው። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እውነተኛ ስሜት ነው። በተለይ በቴክሳስ ለምንኖርና በዚያን ግዜ ለነበርን ትልቅ ኩራታችን እንደሆነ በድፍረት ሁላችንም እንናገራለን። የፌደሬሽኑን ህልውናም እንደኛው እንመለከታለን። ደግሞ ይህ ፌደሬሽን ሲጀመር በአንድ ቲም ሆኖ ከሔውስተን አትላንታና ዲሲ ቲሞች ጋር ጀማሪው ቲም፤ በ፳ ወቹ አመታት በስደት ወደአሜሪካ በመጡ የዚያን ጊዜ ስደተኞች የተጀመረ እንደነበር ከላይ ጠቅሻለሁ። ታዲያ ሁለቱም ቲሞቻችን ላለፉት አያሌ አመታት መንፈስ ሳይቀይሩ እስከአለንበት ደርሰዋል። ለነዚህ ቲሞችም ሆነ ለመላ ለፌደሬሽኑ መፈጥርና መጎልበት አስተዋጸኦ ያደረጉ ወገኖች በነዚህ ቲሞች መስራችና አሁንም አባል ናቸው። አቶ ታደሰ ፈረደ፤ አቶ እያዩ ዘነበ፤ አቶ ደሳለኝ በፈቃዱ፣ አቶ ሲራክ ደበበና ለረጅም አመታት የፌደሬሽኑ አመራር ኮሚቴ አባል ሆኖ ያገለገለው አቶ ዘውገ ቃኘው በግንባር የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ያደረጉት አስተዋጸኦ ለዚህ ለዳላስ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ለፌደሬሽኑ መፈጠርና መጎልበት አይነታ አስተዋጸኦ አለው። እዚህ ቴክሳስ ሲጀመር ከሔውስተን አቶ ሐይሌ ተፈራ፣ ዶክተር አካሉ ወ/ሚካኤል (ነፍሳቸውን ይማር)፣ አቶ ብርሐኑ ወ/ማሪያም የሚረሱ አይደሉም።

 

ለዚህ የስደተኛ ፌደሬሽን ማደግ ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን ካወጡት በዚህ ጽሁፍ ካልተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ባሻገር፤ መላ ስደተኛው ጠቃሚነቱን በመረዳትና በመተባበሩ ለመሆኑ ተግባሮቹ ይናገራሉ። ከመጀመሪያው አመት ጀምሮ ወገንን ከአጥናፍ አጥናፍ እዚህ ሰሜን አሜሪካ በማሰባሰቡ በቅናት የተዋጡ የተለያዩ ስብስቦች ተፈጥረው ለመወዳደር ብሎም ለማዳከም ሞክረዋል። ሙከራቸው ግን አልተሳካም። ይህን ፌደሬሽን ሊያስንቅ አልቻለም። አንዱና ትልቁ ጉልበቱ ሁሉንም ዜጋ ያለምንም ልዩነት በማካተቱና በአንድ ማገናኘቱ በመሆኑ የአደሬ ፌደሬሽን ወይንም የሌላ ዘር ብለው ቢፈጥሩት ይህን ፌደሬሽን ሊያስንቅ የሚችል አልተፈጠረም።

 

በሰሞኑ ፌደሬሽኑን ለመንጠቅ በተነሳው ግርግር ከላይ የጠቀስኳቸው ግለሰቦች በተለየም አቶ ደሳለኝ በፈቃዱና አቶ ዘውገ ቃኘውና እንዲሁም አቶ አብይ ኑርልኝ የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዜዳንትን ጨምሮ ላደረጉት አስተዋጸኦ ከልብ ክበሬታ ሰጥቻለሁ (በዳላስ ማለቴ ነው)። በአንጻሩ ሦስት የሚሆኑ ግለሰቦች መጀመሪያ አንዱን ቲም ከመሰረተው ፌደሬሽን ነጥቀው ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ ከላይ በዘረዘርኋቸው ግለሰቦችና በመላ የቲሞቹ አባላት ሲከሽፍ፤ በአቶ ኤሊያስ ደብሩ ግንባር ቀደምነት ለአመታት ከነበሩበት ፌደሬሽንም ሆነ ቲም ወጠው ለመሄድ መወሰናቸውን ስሰማ ከልብ አዝኛለሁ። ለሐዘኔ ምክንያቱ ግለሰቦቹ፤ አንድም ፌደሬሽኑ የወሰነውን ውሳኔ ያልተቀበሉትና የጨዋታው አመታዊ በአል በዳላስ እንዳይደረግ የተቃወሙት፤ በማህበራዊ ኑሮም ሆነ በመልካም ባህርይ ከሕዝብ ያልተለዩ፣ ለቲሞቻችን ግርማሞገስና ድምቀት ሰጭ ሆነው የቆዩ ወገኖች በመሆናቸው፤ ይህን አሁን የያዙትን አቋም ለሰማ ሁሉ ማመን ይቸገራል። አሁንም ቢሆን ስህተታቸውን አርመው እንደሚመለሱ ተስፋ አለን። ሆኖም አቋማቸውን ከቀጠሉበትና በሽማግሌም ተጠይቀው እንቢታን በማሳየት አሁንም ካፈርሁ አይመልሰኝ ካሉ ለአመታት ያደረጉትን ውብ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መልካም አስተዋጸኦ ማፍረስ እንደሚሆንባቸው ላሳስብ እወዳለሁ። ፌደሬሽኑ የሕዝብ ነው። ይቀጥላል። ሕዝብን በገንዘብ መግዛት ማንም አይችልም። ግለሰቦች ይሆናል ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል። እንደሚባለው፤ አንዳንድ ግለሰቦች በነዋይ ተደልለው ከሆነ ችግራቸው ከቤት ይጀምረል። ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው የሚቀበሉት አይደለምና። ከላይ እንዳልሁት ፌደሬሽኑ የሁላችንም ነው። ይህንን ለ፪፰ አመታት ባሳየው ተግባር የተዋሀደን እንጅ እንኩ ተብለን የተቀበልነው አይደለም።

 

የኢትዮጵያ እስፖርት ፌደሬሽን ሰሜን አሜሪካ ያለፉ ፈተናወች

በ፳ወቹ በዚህ በሰሜን አሜሪካ የነበራችሁ ኢትዮጵያውያን ልታስታውሱ ትችላላችሁ። ፌደሬሽኑ ገና ለጋ ጀማሪ በነበረበት አመታት በአገራችን የደርግ አስተዳደር የነበረበትና ወደዚህ ወደሰሜን አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ከሶማሊያ፤ ጅቡቲና፤ ሱዳን በስደት የሚመጣበት ወቅት ነበር። በዚያን ግዜ በዚህ በሰሜን አሜሪካ ይኖር የነበረው የሕወሐት ተወካይ ብርሐነ ገ/ክርስቶስ ይባላል። ይህ ሰው አሁን የሕወሐት ፖሊት ቢሮና የውጭ ጉዳይ ዋና ሰው ነው። ግለሰቡ ይህ ፌደሬሽንን አጥብቀው ከሚጠሉት ውስጥ ነው። ምክንያቱም ዘርን፤ ሐይማኖትን፤ ጾታን፤ ቋንቋን የማይለይ በመሆኑና የሕወሐትንም ሆነ መላ የዘር ፖለቲካን ይሁነን ብለው የያዙ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን አላማ ፉርሽ ያደረገ፤ ኢትዮጵያውያን ከየትም ተሰባስበው በአንድ ውለው አድረው ሰንብተውና እንደ ብሔራዊ በአል ክብር አድርሰው የሚለያዩበት አሰባሳቢ ወርና ሳምንት በመፍጠሩ ነው። አቶ ብርሐነ ለዚህ ለሰሞኑ የትቂት ግለሰቦች ግርግርም እጁን እንዳስገባ ይነገራል። በእርግጥ አላማው ነው። ይህ ፌደሬሽንም እሱ በዋሽንግተን በነበረበት አመታት ተወልዶ ያደገ በመሆኑና በጊዜው ተመሳሳይ ፌደሬሽን ከሻብያ ደጋፊወች ጋር ለመፍጠር ሞክሮ ስላልተሳካለትም ነው። ብዙ የኤርትራ ተወላጅ ወንድሞቻችን ፌደሬሽኑ ሲመሰረት አብረው መስራች ነበሩ። ለምሳሌ እዚህ ዳላስ አቶ መንግስት አብ ኢትዮጵያን ወክሎ በብዙ የአፍሪካ ዋኝጫ ውድድሮች ተጫዋች የነበር ግለሰብ በመጀመሪያው አካባቢ አብሮ ይጫወት እንደነበር አስታውሳለሁ። በኋላ ግን ተለይተው እንደወጡና የኔ የሚሉት እንደመሰረቱ ነው።

 

ይህ የስፖርት ፌደሬሽን ሦስት አስርት አመታት ሲዘልቅ ብዙ ተመሳሳይ የሆኑ ፈተናወች ነበሩበት። ሁሉም ከአንድ አቅጣጫ የተወረወሩ ናቸው። ለተቀናቃኝ መፈጠርም ምክንያቱ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነው። ይህ የዛሬው ሙከራ የራሱን የፌደሬሽኑን ስም ይዞ ቢወጣም ካለፉት አመታት ካየናቸው የሚለየው ግልጽ የሆነ የነዋይ ድጎማ እስከ ተጫዋቾች ዘልቆ መለገሱ በቀር ምንም አዲስ ሁኔታ አላየነም። ውጤቱም አንድ ይሆናል:: ይህን አንጋፋ ድርጅት ትተው ዲሲ ወደተዘጋጀው ሊጓዙ የተነሳሱ ቲሞች ካሉ ሊያስቡበት ይገባል። እንደሰማነው የመጓጓዣና ሆቴለ እንደሚከፈላቸው ነው። ይህ ግን በፈቃድ እራስን ለባርነት እንደመሸጥ ይቆጠራል። ያሰባችሁ ቲሞች አካሔዳችሁ የተሰሳተ ነው በግዜ ማረሙ ይበጃል ይላል ብዙሀኑ ሕዝቡ።

[email protected]