አቡጊዳ – ቢሊዮን ብሮች ተሰብሶብ የአባይ ግድብ ጉዳይ እንደገና በግብጽ እጅ ሊወድቅ ነው!

ግሪን ፕሮፌት የተሰኘዉ የግብጽን አቋም በስፋት የሚያንጸባርቀዉ ድህረ ገጽ፣ የአባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ዘገበ።

የኮሚቴው አባላት ሁለት ከሱዳን፣ ሁለት ከግብጽ እና ሁለት ከኢትዮጵያ ሲሆኑ፣ አራት በሶስቱም አገሮች ተቀባይነት ያላቸው ባለሞያዎች እንደሚካተቱበት ድህረ ገጹ ያትታል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ስድስት የአባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር በመሆን ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል። በቅርቡም ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ የራሷን መንግስት መመስረቷ የ2011 ዓ.ም ትልቁ ዜና ነበር።

ይህ ሆኖ እያለ የመለስ አገዛዝ፣ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አገሮች በመተዉ፣ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ብቻ በአባይ ጉዳይ ለመነጋገር መቀመጡ፣ ከአስር አመታት በላይ የፈጀዉን የአባይ ስምምነት ማጣጣል ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቀርበት ያላቸው ይናገራሉ።

በአባይ ግንባታ ስም፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች፣ በውዴታም ሆነ በጉልበት በቢሊይኖች የሚቆጠር ብር እየሰበሰበ ያለዉ የመለስ አገዛዝ ፣ በአባይ ጉዳይ ላይ ኮሚቴ ማቋቋሙ ለብዙዎች ዱብ እዳ ሆኗል። ምናልባት የተሰበሰበዉን ገንዘብ በካዛናዉ በማስገባት፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ሽጦ ከአባይ ግድብ ግንባታ፣ አገዛዙ ፈቀቅ ሊል እንደሚችልም የሚጠረጥሩ አሉ።

ሱዳን እና ግብጽ ሁልጊዜ አብረዉ የሚያብሩ እንደመሆናቸዉ ፣ በአብላጫ ድምጽ በኮሚቴዉ የሚወሰኑት ዉሳኔዎች የኢትዮጵያን ሳይሆን የግብጽን እና የሱዳን ጥቅም የበለጠ የሚያስከበር፣ በቀላሉም በአለም አቀፍ ማህበረሰብ በኩል ኢትዮጵያን የሚያስጠቃ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ የፖለቲካ ተንታኝ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ማዋጣት ብቻ ሳይሆን ቆም ብሎ መጠየቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

«በአባይ ጉዳይ ላይ የሚያገባቸው ፣ ከኢትዮጵያም ጋር የሚስማሙ፣ እንደ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ .ያሉ በርካታ አገሮች አሉ። እነርሱን አስወጥቶ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚ እንዳትሆን ከሚፈልጉ ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር መቀመጥ ትልቅ ስህተት ነዉ» ሲሉ ያስረዱት እኝሁ ተንታኝ፣ በአገር ዉስጥ ሆነ ከአገር ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ የተቃዋሚ ድርጅቶችም ሁሉ የአቶ መለስ አገዛዝ የሚያደርጋቸዉን ስምምነቶች ሁሉ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኮሚቴዉ የመግባቢያ ሰነድም ሆነ አላማ ምን እንደሆነ፣ እንዲሁም የኮሚቴዉ ዉሳኔ ምን ያህል አሳሪ ሊሆን እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም።