ፍኖት ጋዜጣ – ፈረዱባቸዉ – በብዙዋየሁ ወንድሙ
“እኔ ወንጀል አልፈፀምኩም፡፡ ጥፋተኛም አይደለሁም፡፡ ታሪክ ነፃ ያወጣኛል” አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሄር
“ማስረጃ ባልቀረበበት ክስ ፈርዳችሁብኛል” ጋዜጠኛ ውብሼት ታዬ
“ይህ የሰው ፍርድ እንጂ የእግዚሐብሄር ፍርድ አይደለም” ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ
ባለፉት 20 ዓመት አገራችን በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ በተለይ በፍ/ቤት ዙሪያ ብዙ አሳዛኝም፤ አስገራሚም የሚባሉ ነገሮች ተፈጽመዋል፡፡ በወቅቱ አንድ ግዙፍና ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ በመመስረት፣ በህክምና ሞያቸውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው እንዲሁም በግል ስብዕናቸው ስመጥርና አንቱ የተባሉት የፕ/ር አስራት ወልደየስ የፍርድ ሂደት ዘላለም ይታወሳል፡፡
እሳቸው ፍ/ቤት በሚቀርቡበት ወቅት ፍ/ቤት የሚሰበሰበው ህዝብ አስገራሚ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ በፍ/ቤት ዙሪያ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ የጅምላ አፈሳ ተደርጐ ለሦስት ወር ኮልፌ ፖሊስ ካምፕ ታስረው ነበር፡፡
ተይዘው ሲታሰሩ ትልቅ የለ ትንሽ ፀጉራቸውን በጠቅላላ እንዲላጩ ተደረጉ፡፡ አዛውንቷ አምባሳደር ዮዲት እምሩም አንኳ ሰለባ ነበሩ፡፡ ፕ/ር አስራት በተከሰሱበት ወንጀል ለጊዜው ለመከራከር ቢሞክሩም የዳኝነቱ ሂደት እምነት አሳጥቷቸው ነበር፡፡ “ፍትሐዊ ዳኝነት በሌለበት አልከራከርም” ብለው ጠበቆቻቸውን ማሰናበታቸው ይታወሳል፡፡
ተፈረደባቸውና እስር ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም የሆነው ሁሉ ሆነ፤ ሞቱ፡፡ ተቀበሩ፡፡ ከመሞታቸው በፊት ግን
አንድ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ “ሻማውን ለኩሰነዋል፡፡ ከእንግዲህ ማንም አያጠፋውም፡፡” ነበር ያሉት፤
ፕ/ር አስራት ወልደየስ፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት ተከሰሱና ፍ/ቤት ቀረቡ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ አመጽ ለመቀስቀስ ፓርቲ እንዳቋቋመ፤ ጦር እንዳደራጁ፤ ተመሰከረባቸውና ተፈረዳባቸው፡፡ የፍርዱ ዕለት በጉጉት ተጠብቆ ነበርና በርካታ ታዳሚዮች ችሎቱን ሞልተው ይከታተሉ ነበር፡፡ “15 ዓመት እንዲታሰሩ ተወስኖበዎታል፤ በፍርዱ ቅሬታ ካልዎት ይግባኝ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡” ተባሉ፡፡ ዶ/ር ታዬ “ከእንግዲህ እናንተ 15 ዓመት የምትቆዩ ከሆነ ውጪ ከምሆን እስር ቤቱ ይሻለኛል፡፡” ብለው ተናግረው እስር ቤት ገቡ፡፡ ፓርቲያቸውንም ጦራቸውንም ማንም ሳያውቀው በወረቀት ላይ ቀረ፡፡ ቀን ፈታቸውና ተፈቱ፡፡ እና ተሰደዱ፡፡
ሌሎች በርካታ ገጠመኞችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በቅርቡ የወጣው የፀረ-ሽብር አዋጅ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ አዋጁ ገና ከረቂቁ ጀምሮ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ አዋጅ ሆኖ እንዳይወጣ ከአገር ውስጥም፣ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብም፤ ጥረት ተደርጐ ነበር፡፡
ረቂቅ አዋጁን አጥብቀው ካወገዙት ድርጅቶች ውስጥ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍተህ ፓርቲ/አንድነት/ ይገኝበታል፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም “የፀረ-ሽብርተኝነት ረቂቅ አዋጅ በዜጐች ላይ ሽብር ፈጣሪ ነው!!” በማለት መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በፓርላማው ውስጥ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አጥብቀው አውግዘውታል፡፡
ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ረቂቁ እንዳይፀድቅ አሳስበዋል፡፡ “አዋጁ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት የታለመ ነው” በማለት ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ “አዋጁ አገርንና ህዝብን ለመጠበቅ
ታስቦ የተዘጋጀ ሳይሆን ኢህአዴግን በሥልጣን ላይ ለማቆየትና ኢህአዴግ እየፈፀመ ላለው አፈናና
ወንጀል ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የታሰበ ነው” ሲሉ አብጠልጥለውታል፡፡
ፓርላማው በረቂቅ አዋጁ ላይ ሲወያይ በወቅቱ የፓርላማው አባል የነበሩት አቶ ወንድሙ ኢብሳ “ረቂቅ አዋጁ በራሱ ሽብር ነው” ሲሉ ረቂቅ አዋጁን አጣጥለውት ነበር፡፡ ሁሉም ቢያወግዘውም፣ ቢፈራውና ቢጠለውም አዋጁ አዋጅ ሆኖ ወጣ፡፡ በዚህ ክስ የተመዘገቡት የኢትዮጵያ ሪቪው ድህረ ገጽ ባለቤት አቶ ኤልያስ ክፍሌ በሌሉበት ክሳቸው ታይቶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
2ኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ /ኢብአፓ/ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሔር ናቸው፡፡ ከመክሰሳቸው በፊት አቶ ዘሪሁንና ፓርቲያቸውን እስቲ በጥቂቱ እንመልከት፡፡ ይህ ፓርቲ 2002 ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ከነበሩ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጠንካራ የተቃውሞ አቋሞችን ይወስድ የነበረ ቢሆንም ብዙ የሚዲያ ሽፋን ባለ ማግኘቱ በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት ይታወቃል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ፓርቲው የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ሲፀድቅ በቅድሚያ ያወገዘና ራሱን ያገለለ ፓርቲ ነው፡፡ የምርጫ ሥነ ምግባሩን ካልፈረሙት ጥቂት ፓርቲዎች ውስጥም አንዱ ነው፡፡ በምርጫውም ላይ ከ60 በላይ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና በመቶዎች የሚቆጠሩ ለክልል ም/ቤት እጩዎችን አስመዝግቦ
ተወዳድሮአል፡፡ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም፤ብሎ መግለጫ ካወጡት ፓርቲዎች ውስጥም አንዱ ነው፡፡
ከምርጫው በኃላ ፓርቲውን ወክለው የተወዳደሩ ከሥራ ተባረሩብኝ፣ ታሰሩብኝ፣ እርዳታ ተከለከሉ፣ ተሰወሩብኝም፣ በማለት በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ ግንቦት 20 ቀንን በማውገዝ ህዝባዊ ሰለማዊ ሠልፍ ለማድረግ ባለፈው ዓመት ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ፍቃድ ጠይቀው ተከልክለዋል፡፡ በዚሁ የተነሳ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያና ዛቻ እንደተፈፀመባቸው ክትትል ይደረግባቸው እንደነበረም ለፍ/ቤቱ ሲያስረዱ ተደምጧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም “በሽብርተኝነት ተጠርጥረሃል” ተብለው ታሰሩ፡፡ አቶ ዘሪሁን ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በወረዱበት ወቅት ለዝግጅት ክፍላችን አንድ ደብዳቤ ልከው ነበር፡፡ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ ስለሆነ በወቅቱ አላወጣነውም ነበር፡፡ በዚህ ደብዳቤ ላይ እንደገለፁት እና ፍ/ቤት ሲያስረዱ እንደተደመጠው “በታሰርኩ በማግስቱ ምርመራ ቢሮ ተጠራሁ፡፡ ከዚያም መቼም አንተ የአራዳ ልጅ ነህ፡፡ እንደ ገጠር ልጅ አትገግምም፡፡ እኛ በምንነግርህ መሠረት የመድረክ መሪዎች፣ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ በኤልያስ ክፍሌ ላይ ትመሰክራለህ፡፡ ከዚያም ትለቀቃለህ አሉኝ፡፡
ምንድነው የምመሰክረው ብዬ ስጠይቃቸው ሽብርተኞች ናቸው፡፡ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ይህን ይህን አድርገዋል፡፡ እኔንም እንዲህ እንዲህ አድርግ ብለውኛል ብለህ አሉኝ፡፡ በእርግጥ መርካቶ ተወልጄ አድጌአለሁ፡፡ የአራዳ ልጅ ወይም የመርካቶ ልጅ አብሮ ይሰራል፡፡ አብሮ ተሸምቶና ተቀማምቶ ይበላል፡፡ ለጓደኛውና ለእውነት ይሞታል እንጂ በማያውቀው ነገር የሐሰት ምስክር አይሆንም፡፡ የአራዳ ልጅ በእምነቱ ይሞታል እንጂ ግብዝ አይሆንም፡፡ እየሰማሁ ያደኩት ይህንን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔ በሐሰት አልመሰክርም፡፡ የያዛችሁኝ ማስረጃ አለን ብላችሁ ነው፡፡ ከያዛችሁኝ በኋላ እንዴት እንዲህ ትሉኛላችሁ? አልኳቸው፡፡
ፍ/ቤቱን የምናዘው እኛ ነን፡፡ እንቢ ካልክ የ20 ዓመት እስር ይጠብቅሀል፡፡ የሚደርስብህን ሁሉ ታያለህ አሉኝ፡፡ የፈለጋችሁትን አምጡ እንጂ በሐሰት ምስክር ሆኜ አልቀርብም አልኳቸው፡፡” ይላል፡፡ ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት ደግሞ “መርማሪው ፖሊስ ጠርቶ ምከሩት፡፡ ለሰው ብሎ ራሱንና ቤተሰቡን እየጐዳ ነው፡፡ እሱ እንዴት የቤተሰብ ኃላፊነት አይሰማውም? እኛ እሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን እሱ ግን እንቢ እያለ ነው፡፡ ቀላሉን ጉዳይ ከባድ እያደረገው ነው፡፡ ብትመክሩት ይሻላል
አለን፡፡ እኛም በየዋህነት ሄደን መርማሪው ፖሊስ እንዳለው መርማሪው ባለበት ለምን የሚሉህን እሺ አትላቸውም? ይኽው መርማሪው ፖሊስ ምከሩት እያለን ነው፡፡ መፈታት አትፈልግም ወይ ለእኛስ ለምን አታስብልንም በማለት ነገር ነው፡፡ እዚያው መርማሪ ፖሊስ ባለበት ተናዶ ምኑን ነው እሺ የምለው? ብሎ ንዴቱን መቆጣጠር አቅቶት ባለቤቱን ሊያንቃት ሲይዛት ልጁ አባብላ አስለቀቀቺው፡፡ እኛ እሱ ስለአለን ነው፡፡ የምናውቀው ሚስጥር የለም፡፡ ሁሉንም የምታውቀው አንተ ነህ፡፡ አንተን እንደመሰለህ ብለን ትተነው ሄድን፡፡ ከዚያ በኋላ አንስተንበትም አናውቅም” ይላሉ፡፡
አቶ ዘሪሁን በመቀጠል “ለሁለት ወር ጨለማ ቤት አስገብተው ለብቻዬ አሰሩኝ፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ ሰቅለው
ሲቀጠቅጡኝ ውለው አደሩ፡፡ ጠባሳውን አሁንም ማሳየት እችላለሁ፡፡ ህክምናም እንዳላገኝ ተከለከልኩ”
በማለት አቶ ዘሪሁን በጊዜ ቀጠሮ ይመላለሱ ለነበሩት ፍ/ቤት ገልው ነበር፡፡ \
አቶ ዘሪሁን ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሲወርዱ ለዝግጅት ክፍላችን የላኩትን ደብዳቤ ሙሉ ጽሑፉን በሚቀጥለው ሳምንት ለአንባቢያን እናቀርበዋለን፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዚህ አዋጅ በርካታ ሰዎች ተከሰው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መዝገቦች ውስጥ በቅርቡ የፍርድ ውሳኔ የተሰጠበትን የእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብን እንመልከት፡፡
ጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም በ8፡30 የተሰየመው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች እንዳሻው አዳነ፣ ሙሉ ጌታ ኪዳኔ፣ በሪሁን አራጋው ተሰየሙ፡፡ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እና አንተነህ ጌታቸው፣ ተከላካይ ጠበቆች የ2ኛ፣ የ3ኛና የ4ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ደርበው ተመስጌን፣ የ5ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ሞላ ዘገየ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡
መዝገቡ የተቀጠረው የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ነበር፡፡ ይህንን ያሉት አቶ ዘሪሁን በ2ኛ ተከሳሽነት ተከሰሱና “በቃ” የሚል ጽሑፍ ማጻፋቸው ተረጋገጠ ተባለ፡፡ በሽብር ወንጀል አስተባባሪነትና ፈጻሚነት በተከሰሱበት ሦስት ክሶች “ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው 17 ዓመት እስራትና 50 ሺ ብር” ተፈረደባቸው፡፡
ከፍርድ በኋላ ወደ ዳኞች ጣታቸውን ቀስረው “እኔ ወንጀል አልፈፀምኩም፡፡ ጥፋተኛም አይደለሁም፡፡ ታሪክ ነፃ ያወጣኛል፡፡”በማለት ችሎቱን ለቀው ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሄዱ፡፡
ከተፈረደባቸው አምስት ቀን በኋላ አቶ ዘሪሁንን ማረሚያ ቤት ሄጄ አነጋግሬአቸው ነበር፡፡ በተፈረደባቸው ጉዳይ ምን ተሰማዎት? አልኳቸው፡፡ ፍርድ ቤት በፍርዱ ዕለት የተናገሩትን በመድገም ጀመሩልኝ፡፡ “እኔ ወንጀል አልሠራሁም፡፡ ጥፋተኛም አይደለሁም፡፡ ፍቃድ ያወጣነው ለመቃወም እንጂ ሽንኩርት ልንቸረችርበት አይደለም፡፡ የአቶ መለስ አገዛዝ መቀየር አለበት ብለን ስላመንን “መለስ በቃ” እያልን ነው፡፡ “መለስ በቃ” ማለት ሽብርተኝነት አይደለም፡፡ ሥርዓቱ በዘረኝነት፣ በሙስና፣
በሰብአዊ መብት ጥሰትና በዴሞክራሲያዊ መብት አፈና ይታወቃል፡፡ የሥርዓቱ ፖለቲካ ከሰሯል፡፡ የሚያራምዱት የከሰረ ፖለቲካ ነው፡፡ የእኛን የክስ ሂደትና ፍርድ ስትመለከትም የከሰረ ፖለቲካ ውጤት መሆኑን ያሳያል፡፡ የፍርድ ሥርዓቱ በህግ አስፈጻሚው ሥር ወድቋል፡፡ ህግ አውጪውም በህግ አስፈጻሚው ሥር ነው፡፡ ህግ አስፈጻሚው በአምባገነንነት በትዕዛዝ ያሻውን ሲያስወስንና ሲያስፈጽም ይታያል፡፡ የምንታገለው የምናወግዘው ይህንን ነው፡፡ በቃ ያልነውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ራሳቸውም ያወጡት ህገ መንግስት ይፈቅዳል፡፡ ላወጡት ህገ መንግስትም አይገዙም፡፡ ፀረ- ህገመንግስት የሆነ አዋጅ አውጥተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ምንም የሠራሁት ወንጀል የለም፡፡ ፍርዱ ፍርደገምድል ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የፍትህ ሥርዓቱ በህግ አስፈጻሚው ሥር ወደቋል ብለዋል፡፡ ይግባኝ አትጠይቁም ማለት ነው? በማለት ጥያቄ
አቅርቤላቸው ነበር፡፡ “ስለይግባኙ እያሰብንበት ነው፡፡ ከጠበቆቻችንና ከቤተሰብ እንዲሁም ከትግል አጋሮቼ ጋር ተመካክሬ እወስናለሁ፡፡ የፍትህ ሥርዓቱ ያለበትን ደረጃ ማሳየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ውሳኔው ምንም ይሁን ምን ሥርዓቱን ለትውልድ ማሳየት ያስፈለጋል፡፡” በማለት መልስ ሰጥተውኛል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የጋዜጠኛ ውብሼት ታዬን እና መምህርት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን የፍርድ ሂደት እንዲሁም ከፍርዱ በኋላ ጠበቆች ቤተሰብና የህግ ባለሞያዎችን አስተያየት እንዳስሳለን፡፡
የፍኖት ጋዜጣ የአንድነት ፓርቲ ልሳን ናት። ጋዜጣዋን በብዛት ለማተም በስፋት ለማሰራጨት የአንድነት ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል።