ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ዜጎች በፌዴራል ፖሊስ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው
ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ዜጎች ለችጋር እና እንግልት መዳረጋቸው ሳያንስ በትግራዪ ገዢ ጉጅሌ ፌዴራል ፖሊስ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ከመዲናይቱ የደረሰን ዘገባ አሳይቷል።
የግንቦት 7 ድምጽ ሬድዮ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ በላከው ዘገባ እንደገለጸው፥ ባለፈው አርብ በተለምዶ መገናኛ፣ ሜክስኮ እና አራት ኪሎ ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች የፌዴራል ፖሊስ ሱቅ በደረቴዎችን ዘርፏል። አካባቢው የጦር ቀጠና እስኪመስል የፖሊስ ሃይሉ በሙሉ ትጥቅ ወጥቶ ሱቅ በደረቴዎቹን እንደከበበ የታወቀ ሲሆን፤ ንብረታቸውን የተቀሙት የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ሲያለቅሱ ተስተውለዋል።
በስፍራው ተገኝቶ የአይን እማኝ የነበረውን ዘጋቢያችንን ያናገሩት ሰለባዎች፥ ተስፋ ቢስ እንደሆኑ እና አንዳች እንደሌላቸው በምሬት ተናግረዋል። በርካቶቹ ቤተሰቦቻቸው ከግብርና የሚያገኙት ገቢ በቂ ስላልሆነ እራሳቸውንም ለማትረፍ እና ወላጆቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ከክፍለ ሃገራት የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰ የከተማ ውስጥ ድህነት፤ የኑሮ ውድነት፤ የመሬት እና የንብረት ቅሚያ፤ ረሃብ እና ችጋር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ተባብሰዋል። መንግስት ሰራተኞች፣ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች እና ስራ አጦች ሁሉ በምሬት የተጎዳኙ ሲሆን፤ በርካቶቹም ለሚደርስባቸው ችግር ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ተጠያቂ ነው ብለው እንደሚያምኑ የህዝብ አስተያየት አሰሳዎች ያመለክታሉ።