አዲሱ የኢትዮጵያ ቦይንግ 777 በኤሜሬትስ አውሮፕላን ተገጨ

በዘካሪያስ ስንታየሁ | ሪፖርተር

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የገዛው ብሉ ናይል የተባለው ቦይንግ 777-200 LR አውሮፕላን በቆመበት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ በኤሜሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላን ትናንት ከሰዓት በኋላ ተገጨ፡፡

የኤሜሬትስ ኤርባስ A340 አውሮፕላን ከዱባይ ተነስቶ አዲስ አበባ ካረፈ በኋላ ወደ ኢንቴቤ ለመሄድ በሚያኮበኩብበት ወቅት፣ ስታንድ 17 ላይ ቆሞ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላንን ገጭቶታል፡፡

በኢት ኤኤንኤን ቦይንግ 777-200 LR ኤልአር የተመዘገበው አውሮፕላን ትናንት ጧት 3፡10 ላይ ከአሜሪካ በበረራ ቁጥር ET 501 ገብቶ የቆመ ሲሆን፣ የኤሜሬትስ አውሮፕላን በግራ ክንፉ በኩል የአውሮፕላኑን የኋላ ጭራ ጪስ ማውጫውን (ኤፒዩ) በመግጨት አውሮፕላኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በመሆኑም የኤሜሬትስ አውሮፕላን ክንፍ በመጨሱና በመጐዳቱ ሳቢያ ሳይነሳ ወዲያው ቆሟል፡፡ ይሁንና ትናንት ምሽት አውሮፕላኑ ተጠግኖ ለመብረር በዝግጅት ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 በበረራ ቁጥር ET 500 ወደ አሜሪካ ትናንት ምሽት 4፡15 ላይ የነበረው በረራ ግን ተስተጓጉሏል፡፡

የአውሮፕላኑ ጭራም 15 ሴንቲ ሜትር የተቀደደ ሲሆን፣ በጉዳቱ ምክንያት አውሮፕላኑ እዚሁ አገር ውስጥ ይጠገን ወይም ወደ ቦይንግ ኩባንያ ሄዶ የመሠራቱ ጉዳይ እስካሁን ሊታወቅ እንዳልቻለ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777-200 LR በ500 ሚሊዮን ዶላር ባለፈው ጥቅምት 2003 ዓ.ም. ከቦይንግ ኩባንያ መግዛቱ ይታወሳል፡፡

አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ከሲያትል ባስመጣበት ወቅት የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ ሄደው ማምጣታቸው ይታወሳል፡፡ አየር መንገዱም ቦይንግ 777 በመግዛት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ነው፡፡ ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ወጋየሁ ተረፈ አስተያየት እንዲሰጡን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ብንደውልም፣ ሕትመት እስከገባንበት ድረስ ምላሻቸውን ባለማግኘታችን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡