በየመን የኤምባሲ ተወካዮች ተዋርደው ከቤተክርስቲያን ወጡ…
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ሀበሻ በየመን ክፍል 10
የምጀምረው በሁለት አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ የመን ውስጥ ከሚታተሙት የግል ጋዜጣዎች አንዱ የሆነው አል–ሻራዕ የተባለው በ21/1 2012 ዕትሙ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ተገደሉ በሚል የያዘውን ዘገባ ተርጉሜ እንደሚከተለው አስነብባለሁ። በዚህ ሰሞን በባህር ወደ የመን ከገቡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መካከል ሰላሳ የሚሆኑትን ወደ ሳዑዲ ለመውሰድ የጫናቸው መኪና ላይ በተከፈተ ተኩስ ሶስቱ ሲሞቱ የመናዊ ሾፌሩን ጨምሮ የቆሰሉም መኖሩ ተረጋገጠ፡፡ ማንነታቸውን የሚገልፅ ምንም አይነት መረጃ ካልተገኘላቸው ሟቾች ጋር ከነበሩት መካከል አምስት የሚሆኑትን ደግሞ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል። የሟቾቹ ኢትዮጵያዊነትም የተረጋገጠው አብረዋቸው ካሉት ተጓዦች ነው፡፡