የአዲስ አበባ መሥተዳድር ዕድሮች ላይ የገንዘብ ኮታ ጣለ

(ሙሉ ገ.)

የአዲስ አበባ መሥተዳድር ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር  ከአዲስ አበባ ሕዝብ እና የንግድ ድርጅቶች  ለመሰብሰብ የያዘውን እቅድ ዳር ለማድረስ የአዲስ አባባ እድሮች  ላይ የገንዘብ ኮታ ጣለ፡፡

የመስተዳደሩ  ምንጮች ለአዲስ ነገር እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ደረጃ የተቋቋሙ  ዕድሮች በመላ የሚወከሉባቸው የእድር ምክር ቤቶች ከመሥተዳድሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሣምንት በማዘጋጃ ቤት ተወያይተዋል፡፡  በስብሰባው ላይ  የተገኙ ምንጮች  የአዲስ አበባ መስተዳደር “ በአምስት ዓመት ላሰበው የልማት እቅድ”  ዕድሮች የበኩላቸውን እንዲያዋጡ  ኮታ እንደተጣለባቸው እና በሥራቸው የሚገኙትን ዕድሮች እንዲያሳውቋቸው  ተነግሯቸዋል ብለዋል።

የኮታ ድልድሉ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የአክሲዮን ዕድሮች በማለት የተለየ ሲሆን ዝቅተኛ ተብለው የተመደቡት የሴት እድሮችና አነስተኛ ካፒታል ያላቸው በቅርብ ጊዜያት የተመሠረቱ ዕድሮች  አምስት መቶ ብር፤ መካከለኛ ለተባሉት እንደ ካፒታላቸው ሁኔታ ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር እንዲሁም  ከፍተኛ ለተባሉት እድሮች ደግሞ ከሦስት ሺህ ብር እስከ አምስት ሺህ ብር የሚደርስ ኮታ እንደተጣለባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲሰ አበባ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የዕድር አመራሮች ባለፈው እሁድ ታኅሣሥ 17 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ አባሎቻቸውን የሰበሰቡ ሲሆን ከእድሮቹ ግምጃ ቤት ለአዲስ አበባ መሥተዳድር ለሚወጣው ገንዘብ ማካካሻ ኅብረተሰቡ የተወሰነ ድጎማ እንዲያደርግላቸው  ጠይቀዋል፡፡