የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ተፈረደባቸው
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የላንቻ አካባቢ ማዛዥ ጣቢያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶን ጨምሮ አራት ግለሰቦች በተመሠረተባቸው የሙስና ወንጀል በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ፣ ፍቃዱ ኦልጅራ፣ አብዱራዛቅ ዑመርና ዓለም ገብሬ በተባሉ ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ፣ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃዎች በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔው መተላለፉን የኮሚሽኑ ማስረጃ ያብራራል፡፡
ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ በሁለት ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራትና በ1500 ብር፣ ፍቃዱ ኦልጅራ በሦስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ1000 ብር፣ አብዱራዛቅ ዑመር በአምስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ5500 ብርና ዓለም ገብሬ በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ፅኑ እስራትና በ500 ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ ግለሰቦቹ የፈጸሙትን የሙስና ወንጀል የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው፣ ፍቃዱ ኦልጀራ ታህሳስ 9 ቀን 2001 ዓ.ም የግል ተበዳይ የሆኑትን ዓለማየሁ እሸቱ የተባሉትን ግለሰብ፣ ‹‹የሰጠሁህን ቼክ መልስልኝና በምትኩ ገንዘብ እሰጥሀለሁ፤›› በማለት በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ቀበሌ 12 ልዩ ቦታው አዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት በቀጠሮ ለመገናኘት ይስማማሉ፡፡
በቀጠሮው ቦታ ፍቃዱ ኦልጅራ፣ አብዱራዛቅ ዑመርና ዓለም ገብሬ ካልተያዙ ሁለት የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ከለበሱ ግብረ አበሮቻቸውና ማንነቱ ካልታወቀ ሾፌር ጋር በመሆን ተበዳዩን ግለሰብ ‹‹ትፈለጋለህ›› በማለት በካቴና አስረው፣ በአብዱራዛቅ ኮብራ መኪና ውስጥ አስገድደው ካስገቧቸው በኋላ፣ ወደ ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ይወስዷቸዋል፡፡ ተበዳዩን ይዘውት የመጡት ቼክ ‹‹አምጣ ወይም 400,000 ብር ወስጃለሁ ብለህ ፈርም›› በማለትም ይደበድቡዋቸዋል፡፡ ተበዳዩ ግን ‹‹አልፈርምም›› ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ግለሰቦቹ ተበዳዩን በካቴና አስረው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዷቸዋል፡፡ የጣቢያው አዛዥ ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ ሕግን የማስከበር ግዴታቸውን ሳይወጡ፣ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ተበዳዩ ታስረው እንዲያድሩ ለተረኛ ፖሊስ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡
የግል ተበዳይ አቶ ዓለማየሁ እሸቱ ከሕግ አግባብ ውጭ በካቴና ታስረው በፖሊስ ጣቢያው ወንበር ላይ እንዲያድሩ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም ፍርደኞቹ ግለሰቡን አፍነው በመውሰድና ነፃነታቸውን በማሳጣት በመብታቸው ላይ ከፍተኛ በደል በማድረሳቸውና ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም በፈጸሙበት ሰውን የመጥለፍና ታስቦ በሚፈጸም ከባድ የአካል ጉዳት የማድረስ ወንጀል ተከሰው፣ ውሳኔው እንደተላለፈባቸው የኮሚሽኑ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡