በቦሌ አካባቢ በሚገኝ የአፈና ጣቢያ ንጹሃን አንደሚሰቃዩ ታወቀ

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በቦሌ አካባቢ ባቋቋመው የሰቆቃ ጣቢያ በርካታ ንጹሃን እየተሰቃዩ እንደሚገኙ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መረጃ አስታውቀዋል።

ዘረኛው አገዛዝ ባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ በርካታ የምስጢር እስር ቤቶችን በአገሪቱ ዙሪያ ከፍቶ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዜጎችን እያፈነ ሲያስር እንደነበር ሲነገር ቆይቷል። ሰሞኑን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ከነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ይገኛል።

ይህ ጣቢያ በበብሔራዊ መረጃ እንደሚመራ እና ትግርኛ ብቻ የሚናገሩ አስራ አንድ ሰራተኞች እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ሰራተኞች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እና ያለ ፖሊስ መጥሪያ ዜጎችን አፍነው ፊታቸውን በጨርቅ በመሸፈን እና አፋቸውን በፕላስተር በማሸግ፤ ጥቁር መስታወቶች እና ቁጥር 2 ታርጋ ባሏቸው ኮብራ መኪናዎች ወደ እስር ቤቱ እንደሚወስዷቸው መረጃው ያስረዳል።

ወደ አፈና ጣቢያው በደረሱ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ የሰቆቃ ተግባራት የሚፈጸሙ ሲሆን፤ የተሰነዘረባቸውን ወንጀል የማይቀበሉት ተገድለው እንደሚቀበሩ እና ያመኑት ወደ ማእከላዊ እስር ቤት እንደሚዘዋወሩ በአገዛዙ የደህንነት ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ምንጮች ገልጸዋል። ከሞት ከተረፉት ውስጥ በርካቶች እስካሁን በማእከላዊ እስር ቤት፣ በፌዴራል ማረሚያ ቤት እና በየጦር ካምፖች ውስጥ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ነው።

ወደዚህ ጣቢያ ተወስደው ለስቃይ ከተዳረጉ ዜጎች ውስጥ ከኬንያ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከሱዳን ታፍነው የመጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙ እንደሆኑ ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል።