የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ውሃ እያገኘን አይደለም አሉ

በአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየሞች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊ አገልግሎቶችን እያገኘን አይደለም ሲሉ ለግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

የወያኔ አገዛዝ የመንግስትን አቅም ከግምት ሳያስገባ እና ያለ በቂ ጥናት፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እና ለካድሬዎቹ የሙስና እድል ለመፍጠር ሲል ሰፊ ግንባታዎችን እንደሚያካሄድ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እንደሚጀምር ይታወቃል። እነዚህ ፕሮጀክቶችም ወይ አገልግሎት ያልተሟላላቸው፣ ወይም ጭራሽ ተጠቃሚ የማያገኙ ሲሆኑ ተስተውሏል። ለምሳሌ በተለያዩ የክፍላተ ሃገራት ከተሞች ያለ በቂ ጥናት የተገነቡ በርካታ የኮንዶሚኒየም ህንጻዎች ገዢ አጥተው የከብቶች እና የአህያዎች ማደሪያ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

የተጠቃሚዎች እጥረት በሌለባት አዲስ አበባ ደግሞ በርካቶች ኮንዶሚኒየም እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው እና መነሻ ክፍያ ከፍለው ለአመታት እየጠበቁ ሲሆን፣ እድል ደርሷቸው ያገኙት በአገልግሎት እጥረት እየተንገላቱ ነው። ሰሞኑን ዘጋቢያችንን ያናገሩት አንድ የኮንዶሚኒየም ነዋሪ፥ የውሃ አገልግሎት በሁለት ሳምንት አንዴ እንደሚደርሳቸው ገልጸው፣ “የመብራት እንኳ አይነገር” ብለዋል። የኮንዶሚኒየም ህንጻዎች ደግሞ ዘመናዊ ተብዬ በመሆናቸው መጸዳጃ እና ማእድ ቤቶቻቸው በአግባቡ እንዲሰሩ እነዚህ አገልግሎቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው።