የመሬት ቅሚያው የአንዳንድ ብሔረሰቦችን የአኗኗር ዘይቤ አደጋ ላይ ጥሏል ተባለ

የእንግሊዙ “ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ወይም ቢቢሲ ሰሞኑን አጠናቅሮ ባወጣው ሰፊ ዘገባ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የመሬት ቅሚያ የአንዳንድ ብሔረሰቦችን የአኗኗር ዘይቤ አደጋ ላይ መጣሉን አትቷል።

ቢቢሲ፥ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ተቃውሞ በማሰማታችን ተጠቅተናል የሚሉ ዜጎችንም ቃለ መጠይቅ አድርጓል። አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የጋምቤላ ነዋሪም፥ “ስለ መሬት ጉዳይ አሁን በነፃነት መናገር አትችልም፤ ልትታሰር እና ልትገደል ትችላለህ፤ ይህ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ብሔረሰቦች ሁሉ የጨለማ ዘመን ነው” ብሏል።

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ 3 ሚሊዮን ሄክታር ወይም ቤልጂየምን የሚያክል መሬት ለባዳ አገር ነጋዴዎች የማደል እቅድ ይዞ ተነስቶ፤ ለዚህም ይሆን ዘንድ በርካታ መንደሮችን እየነቀለ እና ዜጎችን እያፈናቀለ መሆኑን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ዘግበናል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህንን ተግባሩን እንዳጠናከረ እና በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የጠረፋማ ክልሎች ነዋሪዎችን በግዳጅ እያፈናቀለ መሆኑንም መዘገባችን ይታወሳል።

አገዛዙ እያደልኩ ያለሁት መሬት ማንም የማይጠቀምበትን ነው ማለቱን የጠቀሰው ቢቢሲ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲጠየቁ ግን አብዛኞቹ የሚተዳደሩት በከብት እርባታ ስለሆነ በየወቅቱ ከወዲያ ወዲህ በመዘዋወር ስለሚኖሩ የማይጠቅም መሬት ብሎ ነገር እንደሌለ መናገራቸውን ዘግቧል። አንድ ነዋሪም፥ “መሬት የምንጠቀመው ለተለያዩ ጉዳዮች ነው – ለእርሻ፣ ለአደን እና በረሃብ ወቅት እየተዘዋወርን ፍራፍሬ ለመልቀም” ብሏል። “ጋምቤላ ውስጥ ባዶ መሬት ብሎ ነገር የለም። መንደሮች ተነቅለዋል፤ መንደርተኞቹም መሬታቸውን እንዲሸጡ ጉቦ ተሰጥቷቸዋል። መሬቱን ግን ሊሸጡት አይችሉም፤ የነሱ አይደለም። መሬቱ የአያቶቻችን ነው።” ሲልም ጨምሯል።

አንዳንድ የአካባቢው ገበሬዎች የተወሰነ ካሳ ቢሰጣቸውም፤ ከብት አርቢዎች ግን ምንም እንዳልተቀበሉም ዘገባው አመልክቷል። የጋምቤላ ነዋሪዎች ይህ የባህላቸው መጥፊያ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ይህንን ፖሊሲ በአፋር እና በሶማሌ ክልልም እየፈጸመ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ አበራ ዴሬሳ የተባለ አንድ ሹመኛ፥ የከብት አርቢዎች አኗኗር ለእድገት ምቹ ስላልሆነ አገዛዙ ያንን ማጥፋት እንደሚፈልግ በግልጽ ተናግሯል።