የአፍሪካ አባት አጼ ኃ/ስላሴ እንጂ ክዋሜ ንክሩማ አይደሉም ከያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)

አፍሪቃውያን በአረቦች እየተፈነገሉ ለነጮች ተሽጠው ባህር ሲሻገሩ ንብረታቸውም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሲጋዝ ብዙ ምዕተ ዓመታት እንዳስቆጠሩና ከሃያ ሚልዮን ያላነሱ አፍሪቃውያን በዓለም ዙሪያ እንደተበተኑ ታሪክ ዘግቦአል፡፡ እነዚህኑ አፍሪቃውያን ባህር ማዶ ለማሸጋገር፣ በመርከብ ውስጥ ከታጨቁበት ቀን አንስቶ የተለያዩ ግብታዊ አመጽ ቢያካሄዱም ወደ ካሬ ቢያን የተጋዙት ባሮች እንዲሁም ዘግይተው ነፃ የወጡት ተሳብስበው በ18ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ መላው ጥቁር አቀፍ የነፃነት እንቅስቃሴ (PANAFRICANISM) ጀመሩ፡፡

ይህንን የነጻነት ፍላጎት ለጥቁር ሕዝብ ያስረዱ የመጀመሪያው ረድፍ መሪዎችን ትተን ትግሉን በውል የተያያዙት ብንጠቅስ ጆርጅ ፓድሞር ፍሬዴሪክ ዳግላስን፣ ማርክስ ጋርቬይ፣ ጆሞ ኬንያታና ኪዋሜ ኑኩሩማ ከፊት መስመር የሚሰለፉ ናቸው፡፡ በጊዜው በቀኝ ገዥዎች ተከብባ ነፃነትዋን ላለማስደፈር ደፋ ቀና ትል የነበረችዋ ኢትዮጵያ በዚህ እንቅስቃሴ ተጨባጭ የሆነ አስተዋጽኦ ባይኖራትም፤ ለእነዚህ የነጻነት ታጋዮችና ለመላው የጥቁር ሕዝቦች መሪ ኮከብ በመሆን ለነፃነት የነበራቸው ተስፋ እንዲለመልም አድርጋለች፡፡ በተለይም ዓለምን ያስደነቀው ትልቁ የአድዋ ድል ነጭ በጦር ሜዳ በጥቁር ዘር ሊሸነፍ አይችልም ተብሎ ይታመንበት የነበረው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ከመቅጽበት ተሸንፎ የጥቁሮች የነፃነት ትግል ኃይልና እምነትን አዳበረ፡፡ ይህም ሲባል አንዳንድ በውጭ አገራት ይኖሩ የነበሩ እነሃኪም ወርቅነህን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን ለፓን አፍሪካኒዝም ያደረጉት አስተዋጽኦ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ የቀደምት የነፃነት ታጋዮች ፓንአፍሪካኒስቶች ኢትዮጵያ በአድዋና በተለይም በማይጨው በጣልያን በተወረረች ጊዜ ወዶ ዘማቾችን በመመልመል በዓለም የዲፕሎማትክ መድረኮች የግፍ ወራሪዎቹን በማጋለጥ¬¬¬ ለጣልያን የሞራል ድቀት ብሎም ለኢትዮጵያ ነፃነት የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃነት ሁለገብ እንቅስቃሴ በማያሻማ ሁኔታ እጅዋን የከተተችው እ.ኤ.አ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ለነጻነት ታጋዮች መጠለያ በመሆን አንዳንዴም የጦር ሥልጠና በመስጠት (ለምሳሌ ማዴባ ማንዴላን ይመለከታል) በገንዘብና በጦር መሳርያ በመርዳት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት (ዘረኛው የደቡብ አፍሪቃ መንግስት ናሚብያን እንዲለቅ ክስ መሥርታ የረታችበትን ይመለከታል) የአገራቱ ነፃነት እውን እንዲሆን በብዙ ጥራለች፡፡ ከ1950ዎቹ ዓ.ም ወዲህ ከቅኝ ግዛትነት ነፃ የወጡ አፍሪቃውያን አገራትን ይብዛም ይነስም፣ በቁስም ይሁን በዲፕሎማሲው በኩል ድጋፍ በማድረግ ትግላቸውን ኢትዮጵያ ያልረዳችበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡

የአፍሪቃ አንድነት አመሠራረትና የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሚና

አፍሪቃውያን በመተባበር ኃይላቸውን ለማጠናከር፤ በየአገሮቻቸው መልካም አስተዳደር ከመመሥረት፤ የሕግ ልዕልና ለማስረገጥ፤ አህጉሪቱን በልማት ለማበልጸግ፣ ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ በአፍሪቃ ሕዝቦች መሃከል ትብብር መደጋገፍና መቀራረብ ለመፍጠር እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን መሠረቱ፡፡ ይህን ትልቅ ጉዳይ ከግቡ ለማድረስ ብዙ ድካምና የዲፕሎማሲ ጥበብ እንደጠየቀ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሁሉም የአፍሪቃ መሪዎች በአፍሪቃውያን መሃከል አንድ ዓይነት ሕብረት ወይንም ትብብር መኖር እንደሚገባው በመሠረተ ሐሳቡ ቢስማሙም በሕብረቱ ጥንካሬና ልልነት እና ሕብረቱን ዕውን ለማድረግ የሚወሰደው የጊዜ ቀመርን በተመለከተ የካዛብላንካና የሞንሮቪያ ቡድን በሚል በሁለት ጎራ ተሰልፈው ነበር፡፡ በክዋሜ ኑኩርማ ይመራ የነበረው የካዛብላንካው ቡድን በአጭሩ የአፍሪቃ አገራት አሁኑኑ ተዋህደው በአንድ መንግስት ስር በሚተዳደር የተባበሩት የአፍሪቃ መንግስታት (United states of Africa) መቋቋም አለበት የሚል ሲሆን ኢትዮጵያ ትገኝበት የነበረው የሞንሮቪያው ቡድን ደግሞ የአፍሪቃ አገራት ኢኮኖሚያቸውን በማስተሳሰር ቀስ በቀስ በሂደት ወደ ሙሉ ውህደት ቢያዝግሙ ይሻላል በሚል በሁለት ተጻራሪ ሃሳቦች ተከፋፍለው ነበር፡፡

በአዲስ አበባም በጊዜው ቅርጹ ገና ያልታወቀውን ውህደት ለመመሥረት በተሰበሰቡበት ወቅት እነዚህ ሁለት ተጻራሪ ሃሳቦች አላራምድ ብሏቸው ስብስቡን ሊበትን የሚችል ቅርቃር ውስጥ ገብተው ወደፊት መግፋት ተስኖአቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲል ይህ ክፍፍል ለውህደቱ መሳካት ትልቅ ሳንካ መሆኑን የተረዱት አጼ ኃይለ ሥላሴ አቶ ከተማ ይፍሩንና ዶክተር ምናሴ ኃይሌን በተለያዩ የአፍሪቃ አገራት በማሠማራት ሁኔታውን ለማለሳለስ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ልዩነቱ በስብሰባው ላይ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ በኋላም ስብሰባው ወደ መበታተኑ ተቃረበ፤ መላው የአፍሪቃ ሕዝቦች ቻርተሩ ይፈረም ይሆን አይሆን በሚል ጭንቀት ተዋጡ፡፡ ዓለም በሙሉ ‹‹ስብሰባው አለ ውጤት ይበተናል›› በሚል አይኑን አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪቃ አዳራሽ ላይ ተከለ፡፡ ማለቂያ የሌለው ስብሰባ ተካሄዶ በመጨረሻው ቀን አፄ ኃይለ ሥላሴ ቻርተሩ ሳይፈረም ከዚህ አንወጣም በሚል በተሰብሳቢዎቹ ላይ የማገት ያህል እርምጃ ወስደው በመጨረሻም ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት መሪዎቹ ቻርተሩን እንደፈረሙ በቦታው የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በተለያየ ጊዜ የተናገሩት ነው፡፡ ተሰብሳቢዎቹም ሆኑ የዓለም አቀፍ ሕብረተሰብና ሚዲያው የቻርተሩ መፈረምና የስብሰባው በድል መጠናቀቅ ሙሉ በሙሉ የአጼ ኃይለ ሥላሴና የረዳቶቻቸው የረቀቀ የዲፕሎማሲ ትግል ውጤት እንደነበረ በጊዜው በተደጋጋሚ የገለጡት ሀቅ እንደነበረ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይኸ ድካማቸውም የአፍሪቃ አባት የሚያሰኝ ክብር አጎናጸፏቸዋል፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪቃ አባት

አጼ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪቃ አባት የተባሉት በእኛ በኢትዮጵያውያን ሳይሆን ምንም በማይዛመዱአቸው ወገንተኛ ባልሆኑ በአፍሪቃውያን ነው፡፡ [በሥራ ምክንያት የጥቁር አፍሪቃን ያዳረስኩ ሲሆን በሄድኩበት ሁሉ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ስም ያልተሰየመበት ሀገር የለም፡፡ ከጥቁር አፍሪቃውያን አገሮች መካከል የአፄው መታሰቢያ ያሌለበት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪቃ አባት ተብለው በተሰየሙበት ጉባኤ ላይ ተገኝተው የነበሩት በጊዜው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ምስማኩ አስራት በዓይናቸው በብረቱ ያዩትንና የሰሙትን እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡]

‹‹ይኼ ሁሉ የሆነው እ.ኤ.አ በ1972ዓ.ም ከጁን 12 እስከ 15 ባሉት ሦስት ቀናት በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በራባት ሞሮኮ ባደረገው የመሪዎች ጉባዔ ነው፡፡ በዚሁ ጉባዔ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት ጉዳይ ስላለ በሚል የኢትዮጵያ መልክተኞች ከስብሰባው እንድንወጣ ተነገረን፡፡ ከሰዓት በኋላም ወደ ስብሰባው ስንመለስ መልእክተኞቹ በሙሉ ቆመው እያጨበጨቡ ‹እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ሰማንያኛው የልደት በዓላቸውን የሚያከብሩት አጼ ኃይለ ስላሴ ‹‹የአፍሪቃ አባት›› ተብለው በስብሰባው ተመርጠዋል፡፡ መላው አፍሪቃም ደግፎታል፡፡ በተጨማሪም በስማቸው ሜዳልያ እንዲቀረጽ የእያንዳንዱ አፍሪቃ አገር ዋና ዋና ጐዳናዎች በስማቸው እንዲሰየም፣ በስማቸው ቴምብር እንዲታተም፣ የልደት በዓላቸውም በመላው አፍሪካ እንዲከበር ተወስኖአል› ሲሉን በደስታ ፈነደቅን አሉ፡፡››

የአፍሪቃ ሕብረት ሕንፃና የቀድሞው የጋናው ፕሬዝደንት ሐውልት

የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ አባቶቻችን እናቶቻችንና አያቶቻችን ከኮሎኒያሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግልና የአጼ ኃይለ ሥላሴና የረዳቶቻቸው የረቀቀ የዲፕሎማሲ የድል ፍሬ ስለሆነ እንኮራበታለን፡፡
በዚሁ ዋና ከተማችን ባለፈው ሳምንት እጅግ ውብ የሆነ ሕንፃ በቻይናዎች ወጪ ተገንብቷል፡፡ ቻይናዎች ይህንን ያማረ ሕንፃ በሁለት መቶ ሚልዮን ዶላር ገንብተው፣ ለአፍሪቃ ሕብረት ያስረከቡት ለነፍሳቸው ብለው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ቻይናዎች በነፍስ አያምኑም፡፡ ይህ ሕንፃ በአፍሪቃውያን በራሳቸው ወይንም በአንድ አፍሪቃዊ ባለሀብት ወጪ ቢገነባ እንዴት ባማረ፤ ነገሩም እንዲህ ‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅም›› ባልሆነም ነበር፡፡ ነገር ግን አፍሪቃውያን ይህን ያላደረጉት ለዚህ ሕንፃ መገንቢያ ገንዘብ ቸግሮአቸው ሳይሆን ፍላጎቱ ባለመኖሩ ነው፡፡ እነዚሁ መሪዎቹ አንዳንዶቹ የዚህ ዓይነት ሶስትና አራት ሕንፃ ሊያስገነባ የሚያስችል ከሕዝብ የዘረፉት ገንዘብ አላቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሕንፃው ያምራል፡፡ ለከተማችንም ትልቅ እሴት ነው፡፡

በቅጥር ግቢው ቀልብ ከሚስቡ ነገሮች መካከል የቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት የክዋሜ ንኩሩማ ሐውልት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከሐውልቱ ግርጌ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽእ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር›› ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ብሂል ተቀርጾበታል፡፡ የዚህ ጥቅስ መኖር መልካም ቢሆንም ነገሩን ይበልጥ ግራ የሚያጋባ የሚያደርገው ጥቅሱ በእንግሊዘኛ ብቻ መቀመጡ ነው፡፡ ይህ ብሂል ክዋሜ ንክሩማ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የጻፉት ድርሰት እርዕስ ነው፡፡
ክዋሜ ንክሩማ አገራቸውን ከኮሎኒያሊስቶች ክራንቻ ፈልቅቀው አውጥተው ለነፃነት ያበቁ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ መሪ ናቸው፡፡ ይህ የሚካድ አይደለም፤ ሆኖም ለአፍሪቃ አንድነትና ሕብረት ስኬታማ ስራዎች እና በአፍሪቃውያን መሃከል ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ አንድ የሚበልጧቸው መሪ አሉ፤ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፡፡

እዚህ ላይ ልናነሳ የምንፈልገው ጥያቄ ለቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ለኩዋሜ ንክሩማ በአዲሱ የአፍሪቃ ሕብረት ቅጥር ግቢ ሃውልት ሲታነጽላቸው፤ የአፍሪቃ አባት የተባሉት አጼ ኃይለ ሥላሴ እንዴት ወደ ጎን ተገፉ? የሚለውን ነው፡፡ አፍሪቃውያን ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸው ከፍተኛ ከበሬታ ከስሌት ሲገባ አፍሪቃውያኑ አላስታወሷቸውም ማለት ይቸግራል፡፡ ሊሆን የሚችልው ኢህአዴግ በዚህ ሐሳብ አልገፋበትም ወይንም ከናካቴው ሌሎች ሀገራት ሲያነሱት ተቃውሞውን ሳያሰማ ቀርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም አጼ ኃይለ ሥላሴ የዓለም መሪዎች በተገኙበት በክብር እንዲቀበሩ ለቀረበው ጥያቄ ኢህአዴግ ፈቃደኛ እንዳልነበረ የትላንት ትዝታ ነው፡፡ በዚህም ጉዳይ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንዴት እንደተዘለሉ ጊዜ ያወጣዋል፡፡
በተቀረ በሕንፃው ቅጥር ጊቢ ለየትኛው አፍሪቃዊ መሪ ሃውልት መቆም እንደሚገባው ቻይናዎቹ የሚወስኑት ጉዳይ እንዳልሆነ ደግሞ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ በአዲሱ ሕንፃ ውስጥ ከኩዋሜ ንክሩማ በፊት ወይንም ሁለቱም መሪዎች እንዲዘከሩ ይገባ ነበር ስንል የአጼ ኃይለ ሥላሴ የግል ዝናን ለማዳበር ከመሻት ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ በሕንፃው ውስጥ ከመትከል፤ ኢትዮጵያ በአፍሪቃውያን የተቸራትን ክብርና ሞገስ የታሪካችን አካል ከማድረግና ለመጪው ትውልድ ከሚሰጠው ክብርና ኩራት በመነሳት መሆኑን በአጽንኦት ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ ብዙዎቻችን የዛሬዎቹ ገዢዎችንም ጨምሮ በተለይም በ1960ዎቹና 70ዎቹ አካባቢ እንገኝ የነበርን ወጣቶች፣ የአጼ ኃይለ ሥላሴን ፊውዳል ሥርዓት በጽኑ ተቃውመናል፡፡ ያ ሁሉ አልፎ የታሪክ ማህደር ገብቶአል፡፡ የነበረው ሥርዓትም ተመልሶ ይመጣል የሚል ስጋትም የለንም፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ አጼ ኃይለ ሥላሴ በጊዜው በዘረጉት ዛሬ በሞተ ሥርዓት ምክንያት በጎ ሥራቸውን ከኢትዮጵያ ታሪክ ለመደምሰስ መሞከር ወይ አላዋቂነት ነው አሊያም ጭፍን ጥላቻ ነው፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪቃ ያደረጉአቸው በጎ ሥራዎች ባለመዘከራቸው የተጎዱት አጼ ኃይለ ሥላሴ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ነች፡፡ አጼ ቴዎድሮስ በፈጸሙአቸው አንዳንድ የጭካኔ ተግባራት ወይንም አጼ ዮሐንስ በጎጃም ሕዝብ ላይ ባደረሱት ጥፋት ልንወቅሳቸው ብንችልም በጎ ስራዎቻቸውንም እያስታወስን እንኮራባቸዋለን፡፡ ይህ የተያዘው ታሪክን የማዋረድ አባዜ ቢያዝ እነርሱም ጋ አለመድረሱ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከብሔረሰቦች ጥርቅምነት ውጭ ሌላ ትርጉም የላትም የሚሉ ግራ ዘመም ፖለቲከኞችና ዓይናቸው በጎጠኝነት የተጋረደው የጎሳ ብሄርተኞች ኢትዮጵያዊ የሆነ ማንኛውንም ነገር ማጥላላትና ማናናቅ እንደተጠናወታቸው አሉ፡፡ ከእነዚህ የጎሳ ብሔርተኞች ይልቅ ለኢትዮጵያ ታሪክና ገድሎች አንዳንድ ፈረንጆች የበለጠ አድናቆትና ከበሬታ አላቸው፡፡ እነዚህ አቋሞቻቸውና ተግባሮቻቸው አገርን በማስገንጠልና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ በማድረግ ብዙ ኪሳራ አድርሰውብናል፡፡ ይህም በአፍሪቃ ሕብረት ሕንፃ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ብሎም ለኢትዮጵያ አንዲት መታሰቢያ እንዲኖር አለመሟገት ወይንም ዕድሉን ለሌላ አሳልፎ መስጠት ሲከፋም መቃወም የራሳችንን የማናናቅና የማጥላላት አባዜ አካል ነው፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ማዋረድና ታሪኳን ማንኳሰስ ይብቃ ማለት መቻል አለብን፡፡