አንድነት በሊዝ አዋጅ ላይ የጠራውን ስብሰባ ለመጪው እሑድ አስተላለፈ (ሪፖርተር)
– መድረክ የአደባባይ ስብሰባ እጠራለሁ እያለ ነው
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ባለፈው እሑድ የሊዝ አዋጅን ለመቃወም የጠራው ስብሰባ ሳይካሄድ ቀረ፡፡ ነገር ግን ይኼንኑ ስብሰባ የፊታችን እሑድ ለማካሄድ ዕቅድ ይዟል፡፡ ፓርቲው አዲሱ የሊዝ አዋጅ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚመለከት ከምሁራን ጋር ለመምከር በእየሩሳሌም ሆቴል ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል፡፡
ይህንን ስብሰባ ለማካሄድ የፓርቲው መሪዎችና ምሁራን በማለዳ በሆቴሉ ቢደርሱም፣ የሆቴሉ የሥራ ኃላፊዎች በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ምክንያት በዕለቱ ስብሰባው እንደማይካሄድ ስለገለጹላቸው፣ በዚህ ምክንያት ፓርቲው ያቀደውን ሰብሰባ ማካሄድ እንዳልቻለ የፓርቲው አመራሮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የተቋረጠውን ስብሰባ በሚቀጥለው እሑድ በዚሁ ሆቴል እንደሚካሄድ በድጋሚ ዕቅድ መያዙን የአንድነት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ገልጸዋል፡፡ በሊዝ አዋጅ ዙርያ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡ የመጀመርያው የሊዝ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያብራራ ሲሆን፣ ይህንን ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡት የአንድነት የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሁለተኛው ጥናታዊ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ የሚያተኩረው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ 721/2002 ላይ ነው፡፡ ይህንን ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ጽሑፎች ከቀረቡ በኋላ በጽሑፎቹና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን ጋር ውይይት ይካሄደል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአንድነት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ባለፈው እሑድ መካሄድ ያልቻለውን ይህን ስብሰባ በመጭው እሑድ ለማካሄድ መወሰናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአንድነት ፓርቲ ይህ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ስድስት ፓርቲዎች የፈጠሩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የአደባባይ ስብሰባ የመጥራት ዕቅድ አውጥቷል፡፡ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የአንድነት ተወካይ ኢንጂነር ዘለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መድረክ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ጥረት ቢያደርግም አዳራሽ ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት በቀጣይነት በአደባባይ ላይ የሊዝ አዋጅን የሚቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት እየተዘጋጀ መሆኑን ኢንጂነር ዘለቀ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በአንድ ንባብ ብቻ ያፀደቀው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡
በዋነኛነት የአዋጁ አርቃቂ የሆነው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአዋጁ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተቻለውን ጥረት ቢያደርግም፣ በአዋጁ ላይ የሚነሳው ጥያቄ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
መድረክ ይህንን አወዛጋቢ የሊዝ አዋጅ በተደራጀ መልኩ ለመቃወም እንቅስቃሴውን የጀመረ ሲሆን፣ ኢንጂነር ዘለቀ እንደገለጹት የሊዝ አዋጅን በሚመለከት መድረክ እስከ መጨረሻው ይገፋበታል፡፡