ፍትህ ጋዜጣ ርዕስ አንቀጽ – በኤርትራ ጉዳይ መመካከር ያስፈልጋል

የአለም አቀፍ ግንኙነት ፖለቲካን የሚያጠኑ ምሁራን በሁለት ሀገራት መካከል ስለሚኖር ግንኙነት ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ ‹‹በአለም አቀፍ መድረክ ዘላቂ ወዳጅም ይሁን ዘላቂ ጠላት የለም›› ፡፡ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በተመሳሳይ ስም በአንድ ገዢ የሚተዳደሩ አንድ ወጥ በሆነ የፖለቲካ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የነበሩ ወንድምና እህታማች አገራት ነበሩ፡፡ አሁንም በአንድ የታሪክ አጋጣሚ አንዱ ራሱን ቅኝ ተገዢ ሌላው ቅኝ ገዢ አድርጐ በመቀጠር ላልተፈለገ ጦርነት ተዳርገው መጨረሻውም የሚታወቀው ሆነ፡፡

ኤርትራ ነፃና ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን አምነን ከተቀበልን በርካታ አመታት ያለፉ ቢሆንም እንደ ወዳጅ ጐረቤት ሀገር አብሮ መኖር ግን ተስኖናል፡፡ ሁልጊዜም ከአብራካችን የወጣችው ሀገር በቀጠናው ካሉ ባዕዳን ይልቅ የስጋታችን ምንጭ ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ከኤርትራ ጋር በቀደሙት አመታት የነበረው ወዳጅነታችን ከህዝቦች አለመግባባት ይልቅ ሀገሪቱን በሚመሩ ልሂቃን መሀከል ውዝግቡ ተካሮ በመጨረሻም የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ደም ላፋሰሰ እልቂት ዳርጐናል፡፡እናም ከዚህ ጦርነት ምን አተረፍን? ምንስ አጣን? ብለን ለመነጋገር እንኳን ጊዜ አላገኘንም፡፡ ጦርነቱ የኤርትራ መንግስት ጠብ አጫሪነት ምክንያት ተጀመረ፣ ግዛት ተወሰደብን፣ ዜጐቻችን? ከሀብት መስዋዕትነት ጀምሮ እስከ ትልቁ የህይወት ዋጋ አስከፈለን፡፡ በስተመጨረሻም ይገባኛል= የምንለውን ግዛት እንኳን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተነታርከን ማሸነፍ አልቻልንም፡፡ በዚህም የተነሰ ከኤርትራ ጋር የነበረን የአንድ ሰሞን ወዳጅነት ዘላቂ መሆን ተሳነው፡፡ በፍትህ እምነት የሀገራቱ ህዝቦች በጦርነቱ ጠበሳ ምክንያት ዘላቂ ጠላትነት ያፈራሉ የሚል ጨለምተኛ እምነትም የለንም፡፡ ነገሩ ዝሆኖች ቢጣሉ የሚጐዳው ሳሩ ነው እንደሚባለው አይነት ነው፡፡አሁንም እንዲህ የከፋ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ ሆነን ኤርትራ ከችግሮቻችን በላይ እየሆነች እንደመጣች መንግስት በተደጋጋሚ በሚዲያ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ፍትህ የሀገር ደህንነትን በተመለከተ መንግስት በሚወስዳቸው ወቅታዊ እና አስፈላጊ እርምጃዎች ላይ ምንም ተቃውሞ የላትም፡፡ ነገር ግን በፍትህ እምነት የሀገር ጉዳይ ሀገሪቱን የሚመራው ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ የመንግስታዊው ህግ አስፈፃሚ፣ ህግ አውጭ፣ እና ህግ ተርጓሚ ተቋማት የውክልና ስራ ብቻቸውን የሚወጡት፣ የሚወስኑት ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገሩ በሰከነ እና ሁሉን አቀፍ በሆነ ሀገራዊ መግባባት ይፈፀም ዘንድ መንግስት በቅን ልቦና ሰፊ መድርክ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ተቻኩሎ ጦርነት ውስጥ መግባት ጥቅም ብቻ ሳይሆን መልሰን ልንተካቸው የማንችላቸው ጥፋቶችንም ያስከትላል፡፡

እንደዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ብቻውን ወስኖ ማቅ ውስጥ ከገባ በኋላ ህዝብን ስብስቦ ለማስረዳት መሯሯጥ በፍትህ እምነት ህብረተሰቡን ከሀገሩ ይገባኛል መንፈስ የሚነጥል አካሄድ ነው፡፡ የኢህአዴግ አመራር ካቀፋቸው ልሂቃን ያልተናነሱ ይህችን አገር ሊታደጉ የሚችሉ ምሁራንም ከፖለቲካ ተገለው ሰሚ አጥተው መኖራቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ኢቲቪም ቢሆን ነገሩን ለማራገብ፣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ከመታተር ይልቅ የሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት ማስተናገድ ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡

ፖለቲካውም እንዲሁ ነው፡፡ በህዝብ ዘንድ የጥላቻን መንፈስ ብቻ መዝራት ለሚመጣው ትውልድ አደጋ አለው፡፡ ኤርትራ ዘላቂ ጠላታችን የማትሆንበት ጊዜም እሩቅ አይደለም፡፡ አሜሪካ በጃፓኖች ላይ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የጣለቻቸው የኒውክለር ቦንቦች ጠባሳው እስከ አሁን ድረስ አለ፡፡ ጀርመንና ፈረንሳይ ሁሌም አንዱ ለሌላው የማይተኛ ባላንጣ ሀገራት ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡

እነዚህ ሀገራት በአሁኑ የፖለቲካ አላማቸው ከበፊቱ ፍፁም የተለዩ ሆነዋል፡፡ ትውልድ ያለፈውን እልቂት እንዲረሳ ከማድረግ ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ የጠበቀ ወዳጅነት መስርተዋል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከኤርትራ ጋርም ከዚህ የጠላትነት ስሜት ወጥተን ወዳጅ የማንሆንበት አንዳችም ምክንያት አይርኖም፡፡ ፍትህ ከሁሉ አስቀድሞ ለሰላምና ለእርቅ በሚሰጠው ዋጋ ላይ ከፍተኛ እምነት አላት፡፡ ከዚህ ቀጥሎም በማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰቡ ይሁኝታ ያልታከለበት እርምጃ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ትላለች፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መያዶችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የተቀሩትን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ማናቸውም ተቋማትን በአንድ ላይ አቀናጅቶ በጉዳዩ ላይ መንግስት ማወያየት ይጠበቅበታል፡፡

]ከዚህ ባለፈ ለሚመጣው ማናቸውም ሀገርን በተመለከተ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከፕሮፓጋንዳ ውጭ በአስተማማኝ እና በተጨባጭ የሀገር ደህንነት ስጋት አንፃር ከሆነ ድጋፋችን ሁሌም ከመንግስት ጐን መሆኑነ ደግመን ደጋግመን እንገልፃለን፡፡