የዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ፌዴራሊዝምን በተመለከተ ቅጥፈት ተያይዘዋል

አምስተኛው አለማቀፍ የፌዴራሊዝም ኮንፈረንስ ባለፈው ማክሰኞና ረቡ ዕ በአዲስ አበባ ውስጥ መካሄዱን አስመልክቶ፤ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ያሰፈነው ፌዴራሊዝም ለሌሎች አገራት ምሳሌ እንደሚሆን የአገዛዙ ባለስልጣናት መናገራቸው የገዢው ቡድን ቋሚ ቀጣፊነት አካል ነው ተባለ።

ባለፈው ሳምንት በዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቃሉን የሰጠው ሹመኛ ሽፈራው ተክለማሪያም፤ እሱ የሚያገለግለው አገዛዝ በኢትዮጵያ ያሰፈነው ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል የሚነሱ ጥሎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አስችሏል፤ በዚህም አገሪቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ ትሆናለች ብሏል።

የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዛ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን በህዝቦች መካከል ግጭቶች መፈጠራቸው እና አሰቃቂ እልቂቶች እንደተከተሉም ይታወቃል። በርካታ ተመራማሪዎችም አገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከቀጠለ፣ አንድ ችግር ሲነሳ የእርስ በርስ ግጭት በቀላሉ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በመተንበይ ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

ሽፈራው ጨምሮ እንደተናገረው፥ የወያኔ አገዛዝ አሁን በስራ ላይ ያዋለው ስርአት ዴሞክራሲን እና እድገትን የሚያስፋፋ፤ ተሳትፎን የሚያበረታታ እና ብሔር ብሔረሰቦችን የሚጠቅም ነው።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እውነተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸው የማያውቅ ሲሆን፤ እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውም ባለመከበሩ እስካሁን ድረስ ነፃ ምርጫ ለማካሄድ እና መሪዎቻቸውን ለመምረጥ እንኳ አልቻሉም። በተጨማሪም፥ መዋቅራዊ ዘረኛነትን በማንሰራፋት አገሪቱን በጉልበት የሚገዛው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የአገሪቱን ሃብት አድሎ በተመላበት መንገድ እንደሚያከፋፍል እና የህዝቦቿን የተፈጥሮ ሃብት በመዝረፍ ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደቆየ ይታወቃል።

ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በአገሪቱ ውስጥ አስፍኜዋለሁ የሚለው እኩልነት ሃሰት በመሆኑም፣ በህዝቦቻቸው ላይ የሚካሄደውን ግፍ እና ኢ-ፍትሃዊነት ለመዋጋት የተነሱ በርካታ የትጥቅ ቡድኖች አሉ። ከነዚህም ውስጥ፥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የሲዳማ ነፃነት ግንባር፣ እና የመሳሰሉት ናቸው።

በሽፈራው ተክለማሪያም ቃል ላይ የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ ይህ ከአገዛዙ የዘወትር ቀጣፊነት ባህሪ የወጣ አይደለም ብለዋል።