የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ያለውን የሃይል እጥረት ቀውስ ለመፍታት ተስኖታል
ባለፈው ሐምሌ ወር የግልገል ጊቤ ሁለት ግድብን ጠግኖ ጨርሶ በመስከረም ወር ሃይል ወደ ጅቡቲ ማስተላለፍ እንደሚጀምር ቃል ገብቶ ሳይሳካለት የቀረው የወያኔ አገዛዝ፤ ባለፈው ሳምንት በሰጠው ቃል ደግሞ ጥገናውን በዚህ በታህሳስ ወር ጨርሶ የፈረንጆቹ አመት ሳያልቅ የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ ጅቢቱ መላክ እንደሚጀምር ገልጿል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሹመኛ የሆነው መኩሪያ ለማ ለብሉምበርግ ዜና እንደተናገረው፤ ሃይል ለጎረቤት አገራት የመሸጡ እቅድ ለአገዛዙ ቢሳካለት፤ የሚላከው መጠን የሚወሰነው አገሪቱ ተጠቅማበት የሚተርፋት ነው ብሎአል። የወያኔው ሹመኛ በሰጠው ሃሳብ የማይስማሙ በርካታ ዜጎች ላለፉት አመታት ከፍተኛ የሆነ የመብራት ሃይል ውስጥ እየማቀቀ ያለው ህብረተሰባችን ምንም ዓይነት አስተማማኝ የሆነ ሃይል እንዲያገኝ ሳይደረግ የሽያጭ ዜና መሰማቱ ወያኔ በአገር እና በወገን ሲቃይ ለመክበር ካለው ራዕይ ተነጥሎ የሚታይ ሴራ አይደለም ይላሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለግንቦት 7 ድምጽ የሰጡት አንድ የቀድሞ መብራት ሃይል ከፍተኛ አክስፔርት ስለ ወያኔ የሃይል ሺያጭ ሲናገሩ “አገዛዙ የኤሌክትሪክ ሃይል ለውጭ አገራት በመሸጥ የሚያገኘው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሚሆንና ከሁሉም በላይ መብራቱ የሚሸጥላቸው አገሮች ግዥውን የሚፈጽሙት ደረጃውን በጠበቀ እና አሳሪ በሆነ አለም አቀፍ የንግድ ውል መሰረት ስለሚሆን አቅርቦቱ በውሃ እጥረትም ሆነ በብልሽት ምክንያት ሊቋረጥ ከቻለ አልፎ አልፎ በፈረቃ የምናገኘውንም እስከማጣት ሊያደርሰን ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል። አክለውም አሁን በግንባታ ሥራ ላይ ናቸው የሚባሉት ግድቦች በሙሉ አንደተባለው ተጠናቀው አገልግሎት ላይ ከዋሉ እና ሺያጩም እውን ከሆነ ለህዝባችን የሚተርፍ ነገር ካለ የበይ ተመልካችነቱ ወደ መብራት ንግድ ሲዞር ማየቱ ብቻ ነው ብለዋል ።
በአምስት አመት የወያነ ትራንስፎርመሽን የወያኔ ሹመኞች አገር አቋራጭ በሆነ የመብራት ሃይል ንግድ አዲስ የዶላር ማግኛ መንገድ ይከፈትላቸዋል ፤ የኛው ሚስኪን ህዝብ አንደለመደው እጁን አጣጠፎ እነርሱ ሸራተን ሲንደላቀቁ እና ለአውሮፓም ሆነ አሜሪካ ሃብታሞች እንኳ ያልተዳረሱ ውድ መኪናዎችን ከፊቱ እያሽከረከሩ ስምንሸነሹ ለ20 አመታት ያህል ቁጭ ብሎ እንደታዘበው አሁንም ጨለማውን ታቅፎ “ይህቺንም አታሳጣን አምላኬ” እያለ ረጅም ዕድሜ ለራሱ መማጸኑን ይቀጥላል አለያም ማርም ሲበዛ የመራል ብሎ ይነሳና ለነጻነቱ ፤ ለሰብ አዊ ክብሩና ለአገር የባለቤትነት መብት ወያኔን ተናንቆ ድል ለመቀዳጀት ይነሳል ብሎአል።