እየተባባሰ የመጣው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአድስ አበባ ከተማ ውስጥ ውጥረትን ፈጥሮአል
የሃይል እጥረት፣ የኑሮ ውድነት፣ የአንዳንድ ምርቶች ከገበያ ላይ መጥፋት፣ የትራንስፖርት ችግር እና የደህንነት ጉዳዮች አዲስ አበባን ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በሄደ ውጥረት ውስጥ ከተዋታል ስትል የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ለዝግጅት ክፍላችን ባስተላለፈችው ዘገባ ገልጻለች።
በከተማይቱ ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ ወፍጮ ቤቶች ሳይቀሩ ከተወሰኑ ሰአታት በኋላ እንዳይሰሩ እየተከለከሉ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። የኑሮ ውድነት ህዝቡን ለከፍተኛ ጭንቀት እና በርካቶችን ለረሃብ ከማጋለጡ በተጨማሪ አገዛዙን እርቃን እንዳወጣውም ዘጋቢያችን ከላከቺው ሪፖርት ለመረዳት ተችሎአል ። በየቀኑ ገበያ በመውጣት እህል ምን ያህል መወደዱን የሚያውቀው ህዝቡ ሆኖ ሳለ በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ዋጋ አሳንሰው እና ንረቱ እንደቀነሰ አድርገው መናገራቸው አገዛዙ በህብረተሰቡ ውስጥ የባሰ እንዲዋረድ እያደረገው መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ ።
በተለያዩ ምክንያቶች ምርቶች ከገበያ ላይ እየጠፉ እንደሆነም የታወቀ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ሙዝ እና ቲማቲም ማግኘት ጭራሹን እንዳልተቻለ፤ ይሁን እንጂ ህዝቡን ከገጠሙት ችግሮች ይኸኛው ትንሹ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል። ለረዥም ጊዜ መፍትሄ አጥቶ የቆየው የከተማይቱ የትራንስፖርት ችግር በተለይ የመንግስት ሰራተኞችን ለእንግልት እና ለጭንቀት እየዳረገ ነውም ተብሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመዲናይቱ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፥ ከሰሞኑ በኦርቶዶክስ እና በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ ችግር ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች የመካረር ችግር እንደተፈጠረ እና አንድ ቀን ሊፈነዳ በሚችል መንገድ ታምቆ አንዳለ ለማወቅ ተችሏል። የተቀሰቀሰው ችግር ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም፤ አንዲት የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን በፌዴራል ፖሊስ ተከባ መደበኛ የአምልኮ ዝግጅትቷን አካሄዳለች።
ሪፖርተራችንን ያናገሩ አንድ ግለሰብ፥ የወያኔ አገዛዝ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ግጭት የመፍጠር ታሪክ እንዳለው አስታውሰው፤ ህዝብ እየደረሰበት ባለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተማሮ በአገዛዙ ላይ በህብረት አንዳይነሳ የህዝቡን ሃሳብ ለመከፋፈል ሆን ተብሎ የተወጠነ ሴራ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።