የኦሮሚያ መንግስት ሰራተኞች በክልሉ የወያኔ ሎሌዎች ላይ ግልጽ ተቃውሞ እያሳዩ መሆኑ ታወቀ

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰራተኞች በወያኔ አገዛዝ ላይ ያላቸውን ቅሬታ እና ተቃውሞ መደበቅ ከሚችሉት በላይ እየሆነባቸው እንደመጣ ሰሞኑን የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ በላከው ዘገባ የኦሮሚያ ባለሥልጣኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚጠሩት የውስጥ ስብሰባ ለአመታት ታምቆ የቆየው የሰራተኞች ብሶትና እሮሮ እየገነፈለ መውጣት መጀመሩን ለማወቅ ከመቻሉም በላይ አዲሱ የክልሉ ፕሬዚደንት አለማየሁ አቶምሳ ጥቅምት 29 ቀን 2003 የጠራው ስብሰባ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተስተጓጉሏል። ፕሬዚደንቱ የክልሉን የቢሮ ሃላፊዎች በስድስት ኪሎ በመሰብሰብ ስለ እድገት እና ትራንስፎርሜሽን፤ እንዲሁም ስለ መልካም አስተዳደር ውይይት ለማድረግ እንደሚፈልግ በመግለጽ ስብሰባውን እንደጀመረ ታውቋል። የመግቢያ ንግግሩን ካደረገ በኋላም ሰራተኞቹ በተጠቀሱት አርእስቶች ላይ አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል። ይሁን እንጂ፥ ያገኘው ምላሽ ጸጥታን ብቻ ነበር ይላል የደረሰን ዘገባ።

ከወያኔ አለቆቹ ተቀብሎ ወደታች እንዲያስተላልፍ የተሰጠውን መልዕክት እንደጨረሰ ከተሰብሳቢው ሞቅ ያለ ተሳትፎ ጠብቆ የነበረው አዲሱ የክልሉ ፕረዝዳንት በቤቱ ውስጥ በሰፈነው ዝምታ እጅግ ግራ በመጋባቱ በንዴት ገንፍሎ “እኔ ውይይት ላካሄድ እንጂ መልክት ልነግራችሁ አልመጣሁምና ተናገሩ” ሲል ተሰብሳቢዎቹን በሃይለ ቃል መናገሩን ሪፖርተራችን ጠቅሶአል። ዘጋቢያችንን ያናገሩት አንድ የስብሰባው ተካፋይ “የክልሉ የቢሮ ሃላፊዎች እንደ ቦምብ የፈነዱት በዚህ ጊዜ ነበር” ሲሉ ተከትሎ የሆነውን ነገር ገልጸውታል። በዚህ ምክንያት ስለ ቀጣዮቹ አምስት አመታት ለመነጋገር የተጠራው ስብሰባ ከዛ ነጥብ በኋላ ወደ ሰራተኞች ምሬት መግለጫ ተለውጦ መስተጓጎሉን ለማወቅ ተችሎአል። ሰራተኞቹ፥ ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ሙስና እና ስለ ክልል መንግስቱ ብቃት ማነስ በማንሳት ስሞታቸውን ገልጸዋል።

ስብሰባው ከመስተጓጎሉ በፊት በርካታ ሰራተኞች በኑሮ ውድነት ምክንያት የሚኖሩት ከእጅ ወደአፍ መሆኑን እና ይኸም በህይወት እና በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ እንዳለ በመናገር አማረዋል። የኖሯቸው ሁኔታ ይሄ ሆኖ ሳለም የክልሉ መንግስት በስድስት ወራት ውስጥ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እሰጣችኋለሁ ብሎ ያለ የሌለ ገንዘባቸውን ሰብስቦ እንደወሰደ፤ ያ ከሆነ ግን ሁለት አመታት መቆጠራቸውን በምሬት ሲናገሩ ተስተውሎአል።

ከባለ ስልጣናት ጋር በመመሳጠር የተሻለ የስራ ምድብ ማግኘት እና ውሳኔዎችን ማስቀየር የተለመደ አሰራር ነው ያሉት ተሰብሳቢዎች፤ ይህ አይነቱ አድሏዊ አሰራር በነገሰበት ስለ መልካም አስተዳደር ማውራቱ እንዳልገባቸው ገልጸዋል። ጨምረውም፥ በርግጥም በክልሉ ፕሬዚደንት እና በመሰሎቹ ላይ ባነጣጠረ መልኩ፥ የተለያዩ ችግሮች በህዝቡ ላይ የፈጠሩትን ቁስል ማየት የሚችሉት አብረው በድህነት መቀመቅ ውስጥ የሚገኙት እንደነሱ ያሉ ሰራተኞች እንጂ፤ ሁለትና ሶስት መኖሪያ ቤቶች አስገንብተው እና የህዝብ መሬት ሽጠው ባካበቱት ሃብት ምቾታቸው ከልክ ያለፈው ባለስልጣናት አይደሉም ሲሉ ክፉኛ አውግዘዋል።

የስብሰባው ተካፋዮች በመጨረሻም፥ እነዚህ ችግሮች ባሉበት ስለ ትራንስፎርሜሽን እና መልካም አስተዳደር ማውራት እንደማይችሉ አስረግጠዋል። ክልሉን አስረግጦ እንዲያስገዛ በወያኔ የተሾመው አለማየሁም ከዋና ርእሱ ወጥቶ የሰራተኞቹን ጥያቄዎች ለመመለስ መገደዱን ዘጋቢያችን ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል።

የኦሮሚያ ክልል ሰራተኞች በየቦታው በአገዛዙ ላይ ያላቸውን ጥላቻ እና ንቀት መግለጻቸውን እንደቀጠሉም ለግንቦት 7 ዜና ምንጭ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ። ባለፈው ሳምንት ይኸው የክልሉ ፕሬዚደንት በቢሮው አካባቢ ያሉ ሰራተኞችን ሰብስቦ፥ ትራንስፎርሜሽን ማለት የውጭ ወራሪን እንደ መዋጋት ነው፤ በዚህ ውጊያ ውስጥ ደግሞ መስዋእትነት ሊኖር ይችላል ሲል ንግግር አድርጓል። ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ሲመልስም፥ “እንግዲህ እንደዚህ አይነት ጦርነት ውስጥ የሚገቡት የህዝብ ስጋ በልተው አጥንቱን የቆረጠሙት መሆን አለባቸው፤ እኛ ስጋችን ተበልቶ አጥንታችን የተቆረጠመውማ በምን አቅማችን” ብሎ እንደተሳለቀበት አንድ የውስጥ አዋቂ ምንጭ ለዘጋቢያችን መናገራቸውን ተያይዞ የደረሰን ዘገባ ያረጋግጣል።