የመለስ ዜናዊ የሃብት ምዝገባ ህዝብ ማታለያ ብቻ ነው ተባለ

መለስ ዜናዊ በቅርቡ በጸደቀው የሃብት ምዝገባ አዋጅ መሰረት ንብረቱን ማስመዝገቡ ህዝብ ለማታለል የተሸረበ ሴራ ብቻ ነው ሲሉ አንድ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ሰራተኛ ለግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ተናግረዋል።

ግለሰቡ እንደሚሉት ከሆነ፥ በኮሚሽኑ ውስጥ የአገዛዙ ሹመኞች የሆኑትን ሰዎች ጨምሮ፥ መለስ ዜናዊ እውነተኛ ሃብቱን እያስመዘገበ ነው ብሎ ያመነ የለም። “ሽር ጉዱ ሁሉ ባዱ የፕሮፓጋንዳ ስራ እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል፤ አብዛኛው የመለስ ዜናዊ ሃብት ያለው ከአገር ውጪ ነው። ይሁን እንጂ እንኳን ውጭ ያኖረውን አገር ውስጥ ያለውንም ሁሉን እንዲናገር የሚጠብቀውም፤ የሚጠይቀውም የለም” ብለዋል።

ግለሰቡ ጨምረውም፥ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ተብዬው እራሱ ሲጀመር ዘረኛው አምባገነን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን እና የማይደግፉትን ዘብጥያ ለመወርወር የሚጠቀምበት ተቋም እንጂ ገለልተኛ የሆነ ባለመሆኑ፣ መለስ ዜናዊን ተከታትሎ እውነት መናገሩን ያረጋግጣል የሚለው ሃሳብ ቧልት ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ በርካታ የሙስና ጥቆማዎች እንደሚደርሱት እና የፖለቲካ መሳሪያ በመሆኑ ከመለስ ዜናዊ ትእዛዝ እስኪመጣለት ድረስ ምርመራ ለማድረግ ምንም እይነት ተነሳሽነት እንደማያደርገም ገልጸዋል።

የአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን የሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው ዘገባ፥ የጸረ-ሙስና ኮሚሽነር የመለስን ሃብት ማስመዝገብ አስመልክቶ አዲስ ስለወጣው አዋጅ ሲናገር፥ አዋጁ የሃገር ንብረት በባበልስጣናት እጅ ነው ያለው የሚለውን አስተሳሰብ እንደሚያስወግድ እና በህዝብ ዘንድ አመኔታን ለመፍጠር እንደሚረዳ ተናግሯል።

ዘጋቢያችንን ያናገሩት ምንጭ እንደሚሉትም፥ በሳቸው ቋንቋ “ይህ ሁሉ ድራማና ሽር ጉድ” የሚካሄደው ህዝብን አታሎ አመኔታ ለማግኘት ነው። ይሁን እንጂ የባለስልጣናቱ ሙስና ወሬ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ በአይኑ የሚያየው ጉዳይ ስለሆነ፤ ሙከራቸው ከንቱ ነው ብለዋል።

በአዲሱ የወያኔ ካቢኔ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ምንስቴር ዴታ ሆኖ የተሾመው ብርሃኔ ገብረክርስቶስ በአሜሪካ የወያኔ አምባሳደር ሆኖ ይሰራ በነበረበት ወቅት ከባለቤቱ ጋር በነበረበት የ40 ሚሊዮን ዶላር ንብረት ክፍፍል ክርክር ገንዘቡ የራሱ ሳይሆን የመለስ ዜናዊ እንደሆነ ፍርድ ቤት ቀርቦ ማስረዳቱ ሲታወቅ ፊይናንሻል ታየምስ የተባለው አንድ የ እንግሊዝ ጋዜጣ በ1998 አም ውስጥ መለስ በዩናይትድ ክንግደም ባንክ ውስጥ ከ80 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ አንዳለው ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል። መለስ ዜናዊ አሁን አስመዘገበ በተባለው ንብረት ውስጥ ይህ ገንዘብ አንዳልሰፈረ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።

ለአገዛዙ ቅርብ የሆነው ሪፖርተር ግዜጣ ባለፈው ሳምንት ለንባብ ባበቃው ህትመት ፣ በዚሁ ሽር ጉድ እንኳ እስካሁን የተሳተፉት አራት ባለስልጣናት ብቻ መሆናቸውን ገልጿል።