በዘረኛው ወያኔ እስር ቤት የሚፈጽመው አስከፊ ሰቆቃ በደህንነት እና በፖሊስ አባላት ተጋለጠ
ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የሚፈጽመውን አስከፊ ሰቆቃ የሚያጋልጥ ፈር ቀዳጅ ሪፖርት በፖሊስ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በደህንነት አባላት ተጽፎ ይፋ መውጣቱን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት – ኢሳት – ዘግቧል።
“ከውርደት ህይወት ሞት ይሻለናል” በሚል ድፍረት በመገፋፋት ሪፖርቱን ማውጣቱን የገለጸው ቡድን፤ ሃያ አንድ ገጾች የወሰደ ሰፊ የሰቆቃ መዝገብ ማውጣቱን የኢሳት ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። ሪፖርቱ፥ በተለይ በማእከላዊ እስር ቤት የኦብነግ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ከኦጋዴን፤ የኦነግ ደጋፊዎች በሚል ከኦሮምያ፤ እንዲሁም በ2001 አመተ ምህረት ከግንቦት 7 ጋር በመመሳጠር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል ተብለው በታሰሩት ዜጎች ላይ የሚደርሱትን በብዛት ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማያውቁ የሰቆቃ አይነቶች ዘርዝሯል።
በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ክስ ከታሰሩት ውስጥ አንዷ የሆኑት እና የሶስት ልጆች እናት እና የአንድ ልጅ አያት ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ላይ የደረሰው ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍ የማእከላዊ መርማሪዎች “እናትና እህት” የላቸውም ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን የሪፖርቱ ጸሃፊዎች አትተዋል። መርማሪዎቹ፥ የወ/ሮ እማዋይሽን አይኖች በጨርቅ ሸፍነው እና እጆቻቸውን በካቴና አስረው ለምርመራ እንደሚወስዷቸው፤ እየሰቀሉ የውስጥ እግራቸውን፣ እጆቻቸውን፣ ታፋቸውን፣ መቀመጫቸውን እና ጀርባቸውን በቃላት ለመግለጽ በሚቸግር ጭካኔ እንደገረፏቸው፤ ልብሳቸውን አስወልቀው ጡቶቻቸው እስኪደሙ ድረስ በኤሌክትሪክ ገመድ እንደገረፏቸው የአሰቃዮቹ ባልደረቦች በጽሁፉ መስክረዋል።
በወ/ሮ እማዋይሽ ላይ የደረሰው ግርፋት የቀሰቀሰው ስቃይ እና ህመም ወደ ቃሊቲ ከወረዱ በኋላም እንዳላቆመ እና አሁንም የሚኖሩት የስቃይ ማስታገሻ ክኒን እየዋጡ እንደሆነ ታውቋል። እናቲቱ ስቃያቸውን ለማስቆም ሲሉ ገራፊዎቻቸው በፈለጉት ኑዛዜ ላይ መፈረማቸውም በዘገባው ተገልጿል።
እንደ ምሳሌ ከተጠቀሱት ውስጥ፥ አቶ ሃሰን የሚባል እና ከደጋሃቡር ታፍኖ የመጣ ኦጋዴኒ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በእስር በቆየባቸው ሁለት አመታት፤ ለስድስት ወራት ሙሉ እጁ በካቴና፣ እግሩ በብረት ታስሮ እንደቆየ፤ በድብደባ ብዛት የግራ ዘር ፍሬው ማሙቶ እንደጠፋ ለማወቅ ተችሏል። ሪፖርቱ፥ “እንደ ከብት የወንድን ልጅ ብልት በመቀጥቀጥ ዘር አልባ ማድረግ በዛ ክፉ በሚባለው የደርግ ግዜ እንኳን ያልነበረ ነበር።” እንደሚል ኢሳት ገልጿል።
ከነቀምት፣ ከአምቦ፣ ከምስራቅ ሀረርጌ እና ከከሚሴ ታፍነው መጥተው ማእከላዊ ምርመራ ጣቢያ ከ6 ወራት በላይ ከፍተኛ ስቃይ 13 ኦሮሞ ወጣቶችም ሪፖርቱ ይናገራል። “እጃቸው በካቴና ታስሮ በግድግዳ ላይ ይሰቀላሉ፣ ይዘቀዘቃሉ፣ በኤሌክትሪክ ይገረፋሉ። ከነዚህ መሃል ሶስቱ ብልታቸው ላይ በደረሰባቸው ግርፋት ምክንያት ሽንታቸውን መቆጣጠር አይችሉም። አንዳንዶቹ ብልታቸው ላይ በደረሰባቸው ግርፋት የተነሳ ተኮላሽተዋል። አንዳንዶቹ አካላቸው ጎድሏል፤ አይናቸው ጠፍቷል፤ እጃቸው ተሰብሯል፤ ጥፍራቸው ተነቅሏል። ከአስራ ሶስቱ መሃል ሁለቱ በሰርጋቸው እለት ነው የታፈኑት። ከእነዚህም ሌላ እጃቸውንና እግራቸውን በካቴና ታስረው ቀንም ለሊትም በጨለማ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው እዛው እስር ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሁለት እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ወጣት ልጆች አሉ።” ይላል።
በዚህ የሰቆቃ መዝገብ ውስጥ የበርካታ እስረኞች ስም እና የደረሰባቸው ግፍ ዝርዝር መገለጹን የኢሳት ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የግንቦት 7 ድምጽ የመረጃውን ሙሉ መልዕክት ከሚቀጥለው እትም ጀምሮ ለህዝብ ያቀርባል