መድረክ የሊዝ አዋጁን የሚቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ እጠራለሁ አለ (ሪፖርተር)

ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአገሪቱ አነጋጋሪ ጉዳዮች በላይ የሊዝ አዋጁ አወዛጋቢነት ተፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት፣ የኢሕአዴግ ዋነኛው ተቀናቃኝ ነኝ የሚለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በአዋጁ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ይዞ ቀርቧል፡፡

አዋጁን የሚቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

መድረክ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤቱ አዋጁን በፅኑ የሚቃወም መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ የተቃውሞ መግለጫ በተጨማሪ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ የሊዝ አዋጁን የሚቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ የመድረክ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ በፊት የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በአዋጁ ላይና የመሬት ሥሪትን በተመለከተ ከምሁራን ጋር ዛሬ በእየሩሳሌም ሆቴል ለመምከር ቀጠሮ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡

የሊዝ አዋጁ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና በመንግሥት መካከል የፈጠረውን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ በዚህ አጋጣሚ መድረክ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ያቀደ መስሏል፡፡ ሕዝቡ መኖሪያ ቤቱን የሠራበት መሬት ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥለትና የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለማሳካት ከተያያዘው ትግል ጎን እንዲቆም መድረክ ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን፣ በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ድምፁን እንዲያሰማ ጠይቋል፡፡

‹‹የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር›› በሚል ርዕስ መድረክ ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ በአዋጅ ቁጥር 721/2004 ነባር ይዞታዎች ሲሸጡ ወደሊዝ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ [አንድ ሰው] ነባር ይዞታን ሲገዛ ባለንብረቱ ከሚከፍለው ክፍያ በተጨማሪ፣ ለመንግሥት የዚያኑ ቦታ የሊዝ ዋጋ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ አሠራር ንብረት በማስተላለፍ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለማንም ግልጽ ነው፤” ይላል መድረክ፡፡

የነባር ይዞታው ባለቤት ቦታውን በመሸጥ ሌላ አነስተኛ ቦታ ገዝቶ በተረፈው ገንዘብ ሕይወቴን ልምራ ቢል፣ አዋጭ አይደለም በማለት ተቃውሞ ያቀረበው መድረክ ነባር ይዞታዎች ከሊዝ የሚያመልጡት እንዴት ነው; ሲል ይጠይቃል፡፡ ይዞታ ሳይሸጥ፣ ሳይለወጥ፣ ንብረት ዋጋ ሳይኖረው እንደ ጉልቻ በመቀመጡ ብቻ ከሊዝ አመለጠ ማለት ነውን; ሲል ጥያቄውን በጥያቄ ያጠናክራል፡፡ ይህ አዋጅ ወታደራዊው መንግሥት እንኳ ያልተከተለው አሠራር ነው ብሏል፡፡

መድረክ እንደሚለው፣ ወታደራዊው አስተዳደር (ደርግ) ባወጣው አዋጅ 47/67 አንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ለመኖሪያ ቤት መሥርያ የሚያውለው እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርስ የከተማ ቦታ ሊሰጠው ይችላል ይላል፡፡ አዋጁ በመቀጠልም የከተማ ቤት ስለማስተላለፍ በሚደነግገው ክፍል አንድ ቤተሰብ፣ ግለሰብ ወይም ድርጅት በከተማ ቤቱ የመጠቀም፣ የማውረስ፣ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አለው ይላል፡፡

ወታደራዊው መንግሥት እንኳ ያልነፈገውን የዜጎች መብት ኢሕአዴግ ለምን በአዲሱ በሊዝ አዋጅ ነፈገ በማለት የመድረክ አመራር አባል ዶ/ር መራራ ጉዲናና ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ገብሩ አስራት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር መራራ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ኢሕአዴግ ይህንን አዋጅ ያወጣው ሕዝቡን ይበልጥ ለመቆጣጠር በመፈለግ ነው፡፡ ‹‹ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁጥጥር የማካሄድ አንድምታ አለው፤›› ይላሉ ዶ/ር መራራ፡፡

“እኛ እየተናገርን ያለነው ስለባዶ መሬት አይደለም፤” ሲሉ አቶ ገብሩ አስተያየታቸውን ይጀምራሉ፡፡ “እኛ እየተናገርን ያለነው ስለ ቤት ነው፡፡ በድሮ ይዞታ ላይ ቤት ተሠርቷል፡፡ ቤት ደግሞ አየር ላይ አይሠራም፡፡ ቤት ከመሬት ጋር ተጣብቆ የሚሠራ ነው፡፡ ቤት ከመሬት ጋር ባለው ቁርኝት እንጂ ከዚያ ውጭ ቤት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ዜጎች ያፈሩትን ቤት የመሸጥና የመለወጥ መብት አላቸው፡፡ መንግሥት በዚህ ጣልቃ ገብቶ መሬቱ የእኔ ነው፤ ጣራና ግድግዳው የእናንተ ነው እያለ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የተሳሳተና የሕዝብን መብት የሚጋፋ ሕዝብንም የሚያስቆጣ ነው፡፡ ሕዝብንም ወደ ድህነት አዘቅት የሚያስገባ ውሳኔ ነው፤” ብለዋል፡፡

ከመነሻው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ቁጥጥር ለማካሄድ ያለመ ገጽታ አለው ያሉት አቶ ገብሩ፣ “ሕዝብን የመቆጣጠር አካሄድ ነው፡፡ በአንድ በኩል በአደረጃጀት አንድ ለአምስት እያለ ኢሕአዴግ በቤተሰብ ጭምር እያደራጀ ነው፡፡ ይህ ቁጥጥር ደግሞ ግቡን እንዲመታ ኢሕአዴግ ኢኮኖሚውንም መቆጣጠር አለበት፡፡ በገጠርም ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር መሬት የሕዝብና የመንግሥት የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመጣስ፣ ኢሕአዴግ መሬትን የመንግሥት ብቻ አድርጎታል፡፡ በከተማም ሰዎች የኢኮኖሚ ነፃነት በኖራቸው ቁጥር በዚያው መጠን የፖለቲካ ነፃነትም ስለሚኖራቸው፣ ኢሕአዴግ ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር ፍላጎት አሳድሯል፡፡ የሊዝ አዋጁ እንደ ፀረ ሽብር አዋጁ ሁሉ ሕዝቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያለመ ነው፤” ሲሉ አቶ ገብሩ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

የአዋጁ አስኳል ነው በሚል ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ይገባል የሚለውን ክፍል አፅንኦት ሰጥቶ የሚቃወመው መድረክ፣ አዋጁ የፀደቀበትን መንገድም እንዲሁ በፅኑ ይቃወማል፡፡ በመግለጫው እንደሚገልጸው፣ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 3፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይሆናል፤›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ መሬትን በመሰለ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነውና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው ሕዝብ፣ ጉዳዩ ቀርቦለት በነፃነትና በግልጽነት እንዲወያይ አልተደረገም ይላል የመድረክ መግለጫ፡፡

“ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥነ ምግባር ደንብና አሠራር የአንድ አዋጅ ረቂቅ ከ48 ሰዓት በፊት ለምክር ቤት አባላት መድረስ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የምክር ቤት አባሉ በዚህ ጊዜ ውስጥ አዋጁን መርምሮና ከባለሙያዎች ጋር ተማክሮ ይቀርባል፡፡ ረቂቅ አዋጁም ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል፡፡ ኮሚቴው ባለሙያ ጋብዞና አማክሮ ለሕዝብና ለሚዲያው ክፍት አድርጎ ያወያያል፡፡
ሐሳቡን አዳብሮም በድጋሚ ለፓርላማ ያቀርባል፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርላማው ያሻውን ውሳኔ ያሳልፋል ይላል የሥነ ምግባር ደንቡ፡፡ አሠራሩ ይህ ሆኖ ሳለ አዲሱ የሊዝ አዋጅ ግን እነዚህን መንገዶች አልተከተለም፤” ይላል የመድረክ መግለጫ፡፡