ዘረኛው አገዛዝ የግብር አሰባሰብ ዘዴ አሻሻልኩ ይላል፤ ህዝቡ ተዘረፍኩ እያለ ነው

በ2003 አመተ ምህረት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ጊዜ ከተሰበሰበው ግብር በ150 በመቶ የሚበልጥ ገንዘብ እንደሰበሰበ በወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ያለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰሞኑን ማወጁ ይታወቃል።

ባለስልጣኑ ለዚህ የደረሰው የግብር አሰባሰብ ዘዴን በማሻሻሉ እንደሆነ ቢገልጽም፤ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ግን የዚህ አመለካከት ተገዢዎች አይደሉም። እንዳውም፣ ዘጋቢያችንን ያናገሩ በርካቶች፣ ይህ ግብር ከመሰብሰብ የተገኘ ገንዘብ ሳይሆን፤ የዘረፋ ውጤት ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ገብርኤል ሰፈር አካባቢ የኬክ ቤት ባለቤት የሆኑ ግለሰብ፥ “ግብር ከህዝብ መሰብሰብ የሚችለው የህዝብ ውክልና ያለው አካል ብቻ ነው። መንግስት ላይ ያለው ቡድን ደግሞ ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው በጉልበት ነው። ስለዚህ ዘረፋ አካሄድኩ እንጂ ግብር ሰበሰብኩ ማለት አይችልም” ብለዋል።

ወያኔ እንደ መንግስት ተቀባይነት ከማጣቱ በተጨማሪም፤ መንግስት ነው እንኳ ቢባል የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ስሞታቸውን ያሰሙ ደግሞ በርካቶች ነበሩ። ከዚህ ቀደም በርካታ የጥቃቅን ንግድ ባለቤቶች ለአገዛዙ ካድሬዎች እና ዘመዶቻቸው ዝቅ ያለ የግብር ትመና ሲሰጥ በነሱ ላይ ከአቅም በላይ የሆነ መጠን መጣሉን በመጥቀስ ቅሬታ ማሰማታቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

የአንድ የብረታ ብረት ንግድ ባለቤት የነበረ ወጣት ለዘጋቢያችን እንደተናገረው፥ ከአቅሙ በላይ የሆነ ግብር ስለተጣለበት፤ በገዛ እጁ ከመሬት አንስቶ የገነባውን ንግድ ለመዝጋት ተገዷል። ወጣቱ፥ መንግስት እንደሱ ያሉ ወጣቶችን አስገድዶ ንግድ ቤት ማስዘጋት ሳይሆን፤ እንዳውም የግብር ምህረት እያደረገ እና ብድር እየሰጠ መደገፍ እና መሸለም ነው ያለበት ሲል የወያኔን አገዛዝ አውግዟል። እንደዚህ ነጋዴ ገለጻ፥ በሌላ የንግድ ዘርፍ ቢሆንም በሱ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጓደኞቹ እና ሌሎች የሚያውቃቸው ሰዎች የፓርቲ አባልነታቸውን ወይም ዘራቸውን ተገን በማድረግ የሚከፍሉትን መጠን አስቀንሰዋል ወይም ጭራሹኑ አልከፈሉም።

ሌሎችም ዘጋቢያችንን ያናገሩ የጥቃቅን ንግዶች ባለቤቶች፣ የሚጠየቁት የግብር መጠን ከሚችሉት በላይ እንደሆነና ቤተሰቦቻቸውን ባግባቡ መደገፍ እንዳልቻሉ፤ በማንኛውም ጊዜ ትርፍ አጥተው ከስራ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመናገር አማረዋል። አንዳንዶቹም፥ ሆን ተብሎ ከንግድ እንዲወጡ እየተካሄደባቸው ያለ ሴራ አለ ብለው እንደሚያስቡ እና፤ ከወያኔ አገዛዝ ጋር ያላቸው ግንኙነትም የመንግስት እና የዜጋ ሳይሆን የጉልበተኛ ዘራፊ እና የሰለባ እንደሆነ ገልጸዋል።