በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ፥ የትግራይ ተወላጆች ለየት ያለ ሚና አላቸው ተባለ
በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ለየት ያለ ሚና አላቸው ሲል ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ አጋልጧል።
የመዲናይቱ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከአንድ ዘውግ በተውጣጡ ሰዎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ እና፤ ይህም አደረጃጀት ያለ ጠያቂ እንዲመላለስ እንዳስቻለው በአገዛዙ ውስጥ የሚገኙ የግንቦት 7 ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል። ይኸው መረጃ ጨምሮ እንደሚያሳየው፥ በዘር ላይ የተዋቀረው አስተዳደር በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ለትግራይ ተወላጆች ለየት ያለ ቦታ አለው።
አንዳንድ በከፍተኛ ጥበቃ ስር የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች በትግራውያን ብቻ እንዲጠበቁ እንደሚደረግ የጠቀሱት ምንጮች፤ ሃኪሞቻቸው ሳይቀሩ ትግራውያን እንዲሆኑ ሆን ተብሎ ተወስኗል ብለዋል። በ2001 አመተ ምህረት ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በመተባበር መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ሞክረዋል በሚል የታሰሩት ግለሰቦች በዚህ አይነት ጥበቃ ስር እንደሚገኙም እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።
ከነዚህ እስረኞች ውስጥ አንዱ የሆኑት ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የእስር ቤቱ ሰራተኞች አማራነታቸውን እንደሰደቡ እና እንዳንቋሸሹ ፍርድ ቤት ቀርበው አቤቱታ ማሰማታቸው ይታወሳል።