የአዲስ አበባው የወያኔ ሹመኛ ኩማ ደመቅሳ የበታቾቹን መቆጣጠር እንደተሳነው ታወቀ

የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ በዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የተሾመው ኩማ ደመቅሳ የበታቾቹን መቆጣጠር እንደተሳነው አንድ የመዲናይቱ መስተዳደር ባለስልጣን ለግንቦት 7 ድምጽ ተናግረዋል።

ከኩማ አማካሪዎች ውስጥ አንዱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ የክፍለ ከተማዎች ባለስልጣናት ለከንቲባው ቁጥጥር ተገዝተው አያውቁም። የከተማይቱ የስልጣን መዋቅር መሰበሩን እና ዝብርቅርቁ መውጣቱን የሚናገሩት ግለሰብ፤ ይህም ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ የሆነውን ሙስና እያባባሰው ሄዷል ብለዋል።

በከተማይቱ ውስጥ ዜጎችን በንብረት ቅሚያ እያስፈራሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ መቀበል እጅጉን የተስፋፋ አሰራር መሆኑም ታውቋል። የክፍለ ከተማ ባለስልጣናት በተለይ ለረዥም አመታት የቆዩ ትላልቅ ህንጻ ያላቸውን ግለሰቦች ኢላማ በማድረግ እና ንብረታቸው ለሆነ ልማታዊ እንቅስቃሴ እንዲፈርስ መወሰኑን በመግለጽ፤ አልያም ጭራሹኑ የነሱ ስለመሆኑ ህጋዊ ማስረጃ እንደሌለ ነግሮ በማስፈራራት እስከ መቶ ሺሆች ብር የሚቆጠር ጉቦ እንደሚቀበሉ ምንጫችን ገልጸዋል።

ግለሰቡ እንደሚሉት፥ ኩማ ደመቅሳ ምንም እንኳ በሙስና የተዘፈቀው አገዛዝ አካል እና ፈቃደኛ ተሳታፊ ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ዘረፋ ግን ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኗል። በወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ዘንድ የተለመደው የሙስና አሰራር፤ የበታቾች እየዘረፉ የሚያመጡትን ከአለቆቻቸው ጋር መካፈላቸው ነው ያሉን ምንጭ፤ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ባለስልጣናት ግን የየራሳቸውን ድርጅት የሚመሩ ይመስል በዘፈቀደ እና ከከንቲባው ጋር ሳይመሳጠሩ የሚፈጽሙት ሌብነት ከንቲባውን ከማስቆጣት አልፎ ስጋት ውስጥ ከቶታል ብለዋል።

የክፍለ ከተማ ባለስልጣናት ከንቲባውን አልታዘዝ ብለው ሲያስቸግሩ አገዛዙን አይፈሩም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ የነገሩ ሁሉ ቁልፍ ዘረኛነት እንደሆነ አስረድተዋል። ኩማ ደመቅሳ ያውም በኢሉባቦር ተወልዶ ያደገ ግማሽ ትግሬ ነው ያሉን አማካሪው፤ የክፍለ ከተማ ባለስልጣናቱ ግን ከሱ ይልቅ ለአገዛዙ ቅርበት የሚሰማቸው የትግራይ ተወላጆች ናቸው ብለዋል።