መለስ ሞቱ ታየዉ መሰለኝ- በሸንቃጣዉ ዘካሊፎርኒያ

አምባገነኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለብዙ ጊዜያት ህክምና ከዱባይ እያገኘ ሳለ ድንገት ስትሮክ (strokeየጭንቅላት ዉስጥ ደም መፍሰስ ማለትም ዋገምት የማያድነዉ) መቶት የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ህክምና የሚያስፈልገዉ መሆኑ ስለታወቀ እ. አ. አ. በነሀሴ ወር 2009 ዓ. ም. የቤልጂየም ዋና ከተማ ወደ ሆነችዉ ወደ ብራሴልስ በአስር ታጣቂዎች ታጅቦ በጥድፊያ ተጓዘ። የተቀላጠፈ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ህክምና ባይደረግለት ኖሮ ይሄኔ መለስ ቆሞ ባልሄደም ነበር። ከዚህ ህክምናም በፊት የአእምሮ መታወክ በተደጋጋሚ ደርሶበት እንደሆነ በሰፊዉ ባይዘገብም ተወርቷል። እንደ በረከት ስምኦን ደቡብ አፍሪካ ለአእምሮ መታወክ ህክምና ባይሄድም በአገር ዉስጥ ባሉት የታወቁ የህክምና ባለሙያዎች እንደታከመም ተሰምቷል።በስትሮክና በአእምሮ መታወክ ተደጋግሞ መከሰት መለስ የሞት እምቢልታዉ ሳይሰማዉ የቀረ አይመስልም። ይህ ከሆነ ደግሞ በትረ-መንግቱን ለሚቀጥለዉ ግለሰብ ለማስረከብ በምርቃና ሳያስብበት እንደማይቀር አልጠራጠርም።

መለስ የህወሀት ነባር መሪዎችን በዘዴ ጥግ ያስያዛቸዉ እሱ ከሞተ ከእሱ ቤተሰብ ዉጪ ማንም ስልጣን ላይ እንዳይቀመጥ ለማድረግ ያቀደዉ ፕላን ሳይሆን ይቀራል እንዴ? መለስ እንደሚለዉ ወጣት ምሁራንን ለማስገባት ነዉ ወይ የስልጣን ሽግሽግ ያደረገዉ? ከስልጣን ድልድሉ እንደታየዉ ከሆነ የአመራር ልምድ የሌላቸዉና ፍጹም ታዛዦች የሆኑ እንጂ ለምን ይህ ነገር ወይም ያ ነገር ተደረገ ብለዉ የማይጠይቁ “አቤት ባዮች” እንደሆኑ ነዉ የምንረዳዉ። ከድሮዎቹም የህወሀት አመራር አካላት ቢሆን 47% የሚሆኑት በተለያየ የስልጣን ደረጃ ተመልሰዉ የተመደቡት ለቁልፍ ስልጣን አስጊ በማይሆኑበትና የመለስንም ስልጣን በአይነ ቁራኛ መጠበቅ በሚችሉበት ሁኔታ ተደርጎ የተመደቡ እንደሆነ ነዉ የሚገባኝ። የጦር ሀይሎችንና የደህንነት መዋቅሩን በሚተማመንባቸዉ ሰዎች አመራር ስር እስካደረገ ድረስ መለስ ለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ማንንም አይፈራም። የተጠናከረና የተደራጀ ተቃዋሚ በሌለበት ምድር ሊያስፈራዉ የሚችለዉ ምናልባት የዉስጥ ወታደራዊ ተቀናቃኞች ካልሆኑ በስተቀር አሁን በህወሀትና በኢህአዴግ አመራር ላይ ያሉት እንኳ አይደሉም። እነዚህ የታዘዙትን አቤት ጌታዬ እያሉ ከመስራት በቀር ምንም ማድረግ የማይችሉ መሆዶዎች ናቸዉ። ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአልጋ ወራሽነት ያለች ትመስላለች እንደ አዲሱ የስልጣን ድልድል ከሆነ። መለስ ድንገት ስትሮክ መቶት ቢሞት ያለምንም ጥርጥር ወ/ሮ አዜብ ስልጣን ላይ ጉብ እንደምትል አልጠራጠርም።

ዊኪሊክስ ከሰሞኑ ባጋለጠዉ የዲፕሎማቲክ ኬብል መረጃ መሰረት የመለስ ጤንነት እያሽቆለቆለ እንደሆነ ነዉ የምንረዳዉ። የዩናይትድ ስቴትና ምዕራባዉያን አገሮች የወደፊቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሳያሳስባቸዉ እንደማይቀር እገምታለሁ ከዚህ መረጃ አኳያ ስመለከተዉ። መለስ ፊቱን ወደ ቻይና እንዳዞረ በሚገባ ሁኔታ በተለይም ዬዩናይትድ ሰቴትስ መንግስት እንደተረዳዉ መገመት አያዳግትም። በስልጣን ሽግሽጉ ስዩም መስፍንን በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለማድረግ መለስ ሞክሮ የተሰጠዉ መልስ ቢኖር ነባር አብዮተኞችን አንፈልግም የሚል ነበር። ይህ ሙከራ ለመለስ በቂ መልስ ሊሰጠዉ ይችል ነበር።ሆኖም ግን ምናልባት አባይ ጸሀይን ከተቀበሉልኝ ብሎ እንደገና ሲሞክር ነባር አብዮተኞችን አንቀበልም የሚል መልስ ነበር በድጋሚ ከስቴትስ ዲፓርትሜንት የተሰጠዉ። ዶ/ር ግርማ ብሩን ግን እንደሚቀበሉ ስቴት ዲፓርትሜንት ጨምሮ ገልጾ ነበር። ይህ የስቴት ዲፓርትሜንት መልስ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር መለስ ፊቱን ወደ ቻይና መልሶ እርዳታ ከምዕራቡ ለማግኘት የወጠነዉን ስትራቴጂ ለመቃወም እንደተደረገ በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል። የመለስ ስትራቴጂ ሳይሰራ ቀረና ስዩም መስፍን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሲሆን አባይ ጸሀይ ደግሞ በኢትዮጵያ የስኳር ሚኒስትር ሆነ። ጉድ ያሰኛል! አባይ ጸሃይ “ጓል አስመራይ ጓል አስመራይ ማለት ሹቓር ነሽ” እያለ በአደባባይ እዳይዘፍን ብቻ ፍሩልኝ።

መለስ አንድ ቀን ወይም አንድ ጊዜ እንኳ “እናት አገራችን ኢትዮጵያ” ሳይል ለኢትዮጵያ ልዑልና ከልብ የተቆረቆረ ለመምሰል ከግብጽ ጋር እንካ ሰላንትያ ተያይዟል። የአባይ ወንዝን ጉዳይ ሳያንቀሳቅስ ሞተ እንዳይባል ነዉ ወይንስ ለሌላ ነገር ? ይህ እንኳን በእኔ ግምት ዲያስፖራዉን ሊያታልል ወይም የምርጫ 2010 ማረሳሻ እንዲሆን የወጠነዉ ስትራቴጂ ይመስላል። መሞቻዉ የታየዉ ሰዉ ቀና ቀና ያሳስበዋል፣ ይቅርታም የመማጸን ሁኔታ ይታይበታል። መንግስቱ ሀይለማርያም በቀይ ሽብር ወቅት መሞቻዉን ሳያዉቅ እንኳ አብዮት ልጅዋን ትበላለች እያለ በቀይ ሽብር ለተጨፈጨፉት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቋል። መለስ ግን ፍንክች አይልም ሞቱ እየተቃረበ ሲመጣ።

መለስ ሌት ተቀን እንዴት አዜብዬ በ2015 ምርጫ እርሱን ተክታዉ እርሱ ደግሞ ቤተመንግስት ተቀምጦ በሪሞት ኮንትሮልና በምርቃና ብርታት አመራር መስጠት እንደሚችል የሚጨነቅ ይመስለኛል። የ”አልሸሹም ዞር አሉ” ፖለቲካ አይደለም ብሎ እነደሚከራከር አልጠራጠርም። ምክንያቱም አንድ ነገር ትክክል ሆነ አልሆነ መረጃ መፈለግ አያስፈልግም መለስ አንድ ነገር ከተናገረ። ልክ 99.6% ድምጽ በማግኘት ምርጫዉን አሸንፈናል እንዳለዉ ሁሉ አዜብዬ ደግሞ ስትመረጥ ሌላ ወቅታዊና ተስማሚ ሊሆን ይችላል የሚለዉን ምክንያት ይሰጠንና ከተቀበላችሁ ተቀበሉ፤ እምቢ ካላችሁ ደግሞ ገደል የመግባት መብታችሁ የተጠበቀ ነዉ ይለናል። ልጆቻቸዉ ወይም የቤተሰብ አባላቸዉ የተኳቸዉ አምባገነኖች በተራቸዉ ልጆቻቸዉን ከመተካት ወደሗላ አይሉም። ምክንያቱም ስልጣን፣ ገንዘብና ሙስና የጥማሉና። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚባለዉን ተረት መለስና አዜብ በሚገባ የተረዱት ይመስላል።

እስከ ምርጫ 2015 ድረስ ወ/ሮ አዜብዬ ብዙ ሴሚናሮችን በምርቃና ልትከታተልና ልታጠና ነዉ፣ በህወሀትና በኢህአዴግ የፖሊት ቢሮዎች አባልነት እንዲሁም በትግራይ ልማት ድርጅት መሪነት በቴልቪዥንና በሬዲዮ እየቀረበች መግለጫዎች ልትሰጥ ነዉ፣ ድስኩሮችንም ልትደሰኩር ነዉ፣ ብዙ አገሮችን ደግሞ ከመለስ ጋር አብራ በመጎብኘትና ከአገር መሪዎች ጋርም በመገናኘት የዉጪ ፖሊሲ ልምዷን ልታስፋፋ ነዉ ልክ ሂለሪ ክሊንተን ለፕሬዚደንነት ስትሮጥ የስራ ልምዷን እንደገለጸችዉ። እስከ ምርጫዉ ድረስ ወዲ አርማጭሆኢቷ አዜብዬ ብዙ የስራ ልምዶችን ታከማቻለች ማለት ነዉ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሪፑበሊክ ሴት መሪ ለመሆን።

ሟርተኛ እንዳትሉኝ እንጂ እኔ እየታየኝ ያለዉ ነገር ቢኖር ይህ ነዉ። መለስ መሄጃዉ የታየዉና የተቃረበ መሰለኝ። መልኩም በቴሌቪዥን ሲታይ እንደ በፊቱ አይደለም። የሆነ የሚያጠራጥር ገጽታ ፊቱ ላይ የሚነበብ ይመስላል። መለስ ድንገት ካመለጠ ልንፈራ የሚገባን ስለአዜብ ስልጣን ላይ መዉጣት አይደለም። ስለወታደራዊ ብጥብጥ እንጂ። እግዚኦ እናት አገራችንን ከመጥፎ አደጋ ጠብቃት እያልን እንጸልይ። አሜን!

[email protected]