የኢትዮጲያ የውጭ ዕዳ ከ134 ቢሊዮን ወደ 200 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡ ተነገረ የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ነው (ሪፖርተር)
የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ክምችት በከፍተኛ እያሻቀበ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የነበረው 134 ቢሊዮን ብር ወደ 200 ቢሊዮን ብር ማደጉን መረጃዎችና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎች አመለከቱ፡፡ የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳም ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 134 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃዎቹ አመልክተው፣ ሪፖርቱ በሚጠናቀርበት ሦስት ወራት ውስጥ የተለቀቁ ብድሮች እንዳልተካተቱ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ እንደ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች ገለጻ ከሆነ፣ በዚህ ሪፖርት ያልተካተቱ ብድሮችን ጨምሮ ከሰኔ ወር በኋላ የተለቀቁ ብድሮች፣ እንዲሁም ለባቡር መስመር ዝርጋታ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የተፈራረመው ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ሲለቀቅ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ የተበደረው 300 ሚሊዮን ዶላር፣ ለስኳርና ለማዳበሪያ ፋብሪካዎችና ለሌሎችም የሚለቀቀው ብድር ሲደማመር ዕዳው ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የአገሪቱ የውጭ ዕዳ እ.ኤ.አ. በ1998 ወደ 10.3 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ አበዳሪ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና አገሮች፣ ለድሃ አገሮች የቀረጹት ‹‹Highly Indebted Poor Country Initative›› (HIPC) የዕዳ ቅነሳ ፕሮግራም መሠረት የአገሪቱ የውጭ ዕዳ እ.ኤ.አ. በ2008 ወደ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበረ፡፡ እ.ኤ.አ. 2007 ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ወደ 8.0 ቢሊዮን ዶላር ማሻቀቡ ተገልጿል፡፡
እስካለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ በወቅቱ ምንዛሪ ከተገኘው 134 ቢሊዮን ወይም ስምንት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ 85 ቢሊዮን ብር የተገኘው ከዓለም አቀፍ አበዳሪ የገንዘብ ተቋማት ሲሆን፣ ቀሪው 49 ቢሊዮን ብር ከአበዳሪ አገሮች ማለትም ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከኩዌት ፈንድና እንዲሁም ከግል አበዳሪዎች የተገኘ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የብድሩ ዋነኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች የተገኘው ብድር የመክፈያ ጊዜው ከ40 እስከ 50 ዓመት ሲደርስ፣ የብድሩ የችሮታ ወይም እፎይታ ጊዜ 10 ዓመት ነው፡፡ አማካይ የወለድ መጠኑ 0.75 በመቶ ነው፡፡
ከግል አበዳሪዎች በተለይም ከቻይናው ኤግዚም ባንክና ከህንዱ ኤግዚም ባንክ የተገኙ ብድሮች በ20 ዓመት ተጠቃለው የሚከፈሉ ሲሆን፣ የችሮታ ጊዜያቸው በአማካይ ሰባት ዓመት ነው፡፡ በእነዚህ ብድሮች ላይ የሚከፈለው የወለድ መጠን ሁለት በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡ የቻይናው ኤግዚም ባንክ የሚያስከፍለው የወለድ መጠን ሌሎች የግል አበዳሪዎች መነሻ ከሚያደርጉትና ከታወቀው የለንደን ኢንተር ባንክ ማርኬት (LIBOR) መነሻ በሁለት እጅ የበለጠ መሆኑን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
የፌዴራሉ መንግሥት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አማካይነት የሚያደርገው የብድር ስምምነት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና አበዳሪ አገሮች ጋር ነው፡፡ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽንና ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከቻይናና ከህንድ ባንኮችና ብድር ይዘው ከሚመጡ (Suppliers Credit) ኩባንያዎች ጋር በተናጠል ድርድር እንደሚያደርጉና ይኸም በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ድርድር ውስጥ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም እንደሚገቡም ተገልጿል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር ለመደራደር በቂ ችሎታ የሌላቸው በመሆኑ፣ ከብድሩ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ አደጋዎች (Exchange Rate Risk) እንዲሁም የወለድ አደጋ (Interest Rate Risk) ከግምት ውስጥ የማያስገቡ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ብድሮች የግልጽነት ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉባቸው መንገዶች እንደሚኖሩ ባሙያዎቹ አልሸሸጉም፡፡ በተናጠል የሚደረጉ ብድሮች ችግር ካለባቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለምን እንደማያስቆማቸው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በተናጠል የብድር ስምምነቶች የሚያደርጉ ድርጅቶችን የሚመሩ ከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲ ባለሥልጣናት ስለሆኑ መሥርያ ቤቱ ብድሮቹን ለማስቆም ይቸገራል፤›› በማለት ባለሙያዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው የብድር መጠን በተጨማሪ አገሪቱ በየዓመቱ ለዋና ብድርና ወለድ (Principal and Interest) ክፍያ የምታወጣው ክፍያ በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት አገሪቱ ዋናውንና ወለዱን ጨምሮ 604 ሚሊዮን ብር የከፈለች ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ዋናውና ወለዱን ጨምሮ 3.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ እንዳሚጠበቅባት ተመልክቷል፡፡ የቻይና ባንኮች አንዳንድ ብድሮች የችሮታ ወይም እፎይታ ጊዜያቸው እየተገባደደ በመምጣቱ፣ የዋና ብድርና ወለድ ክፍያ በሚቀጥሉት ዓመታት እያደገ እንደሚመጣ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
እንደ ባለሙያዎች ግምት ከሆነ በዘንድሮውና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሊገነቡ የታቀዱ ፕሮጀክቶች በተለይም ተጨማሪ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችና ግድቦች ሲጀመሩ፣ የአገሪቱ ብድር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 500 ቢሊዮን ብር ወይም ግማሽ ትሪሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ መንግሥት የህዳሴውን ግድብ ከውጭ ድጋፍ ይልቅ በራስ የውስጥ አቅም እገነባለሁ ቢልም፣ ተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ማስፈለጉን በመሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች ስለሚያመለክቱ፣ የአገሪቱ የውጭ ብድር ከላይ ከተጠቀሰው ግምት በላይ ሊጓዝ እንደሚችል ባለሙያዎቹ አስምረውበታል፡፡ ምንም እንኳን አገሪቱ የምትበደረው ለልማት ሥራዎች ቢሆንም፣ ከልማቱ የሚገኘው ገቢ ስለሚዘገይ በአሁኑ አካሄዷ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ዕዳ ጫና መዘፈቋ የማይቀር መሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ማሻቀቡን መረጃው በተመሳሳይ መንገድ ገልጿል፡፡ የማዕከላዊ መንግሥት ውዝፍ ዕዳ የመነጨው ከብሔራዊ ባንክ በተገኘ ቀጥታ ብድር (ገንዘብ በማተም) ሲሆን፣ ይኼም 46 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከብሔራዊ ባንክ በቦንድ መልክ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በድምሩ 55 ቢሊዮን ብር እስካሁን መንግሥት መበደሩ ታውቋል፡፡
ከግል ባንኮች፣ ከመንግሥት ባንኮች፣ ከማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲና በግምጃ ቤት ሰነድ አማካይነት ከስምንት እስከ አሥር ቢሊዮን ብር ብድር የተበደረ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ የግል ባንኮች ከሚያበድሩት እያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ የሚሆነውን የብሔራዊ ባንክ ቦንድ ወይም ቢል እንዲገዙ ከተወሰነ በኋላ፣ እስካለፈው መስከረም ወር ስምንት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ መግዛታቸው ታውቋል፡፡ ይኼም ወደ መንግሥት ብድር እስካሁን ባይቀላቀልም ወደፊት መቀላቀሉ የማይቀር በመሆኑ የመንግሥትን የአገር ውስጥ ብድር እንዲያሻቅብ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በባንኮች ያለኝ ገንዘብ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ነው ቢልም፣ ባለሙያዎች ሚኒስቴሩ በባንክ ያስቀመጠው ገንዘብ ለበጀትና ለክፍያ የሚውል እንጂ፣ ቋሚ ተቀማጭ ገንዘብ አይደለም ይላሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው 60 ቢሊዮን ብር የመንግሥት የአገር ውስጥ ብድር በተጨማሪ፣ አንዳንድ የልማት ድርጅቶችና ክልሎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦንድ እያስያዙ የሚወስዱት የብድር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የብድር ክትትል ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቦንድ መልክ የወሰደው የብድር መጠን ወደ 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሲሆን፣ ይኼም መጠን እያሻቀበ እንደሚሄድ ተገምቷል፡፡ ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊ፣ የኮርፖሬሽኑ ብድር በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ባያውቁም፣ በየጊዜው ለልማት ፕሮጀክቶች ገንዘብ አሰባስቡ ስለሚባል በውጥረትና በጭንቅ ውስጥ እንገኛለን ብለዋል፡፡
መንግሥት የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመተግበር በበጀት መልክ 407 ቢሊዮን ብር፣ ከበጀት ውጭ ደግሞ 569 ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ 976 ቢሊዮን ብር በዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከበጀትና ከበጀት ውጭ በተለይም ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይገኛል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው የገንዘብ መጠን ምኞት እንጂ ሊሳካ የማይችል መሆኑን ባለፈው ዓመት መገባደጃ በሪፖርቱ መጥቀሱ ይታወሳል፡፡ አይኤምኤፍ ይኼን የገንዘብ ዕቅድ ለማሳካት ቢፈለግ እንኳ አገሪቱ በየዓመቱ ቢያንስ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 15 በመቶ የሚሆን ብድር ማግኘት እንዳለባት፣ ይኼ ተስፋ የማይጣልበት የብድር ፍላጐት ቢሳካ እንኳ አገሪቱ ከማትወጣው የብድር ወጥመድ ውስጥ እንደምትወድቅ አስጠንቅቋል፡፡
ከበጀት ውጭ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው ገንዘብ ውስጥ 30 በመቶ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይገኛል ተብሎ በመንግሥት የተወጠነውን የገንዘብ ዕቅድ የማይሆን ነው ያለው አይኤምኤፍ፣ ባለፈው ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ይህም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 0.7 በመቶ ኪሳራ ያሳየው የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንዴት የገንዘብ ምንጭ ሊሆን ይችላል በማለት የመንግሥትን የገቢ ዕቅድ ውድቅ አድርጐታል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የመንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ ዕዳ አገሪቱን የማትወጣው የዕዳ ጫና ሊያሳርፍባት የሚችል የዋጋ ግሽበትና የግል ዘርፉን ማዳከም ሊያስከትል እንደሚችል፣ አይኤምኤፍ ባለፈው ዓመት ሪፖርቱ በፅኑ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡