የመለስ ቦላሌ!

ግርማ ደገፋ ገዳ

የመለስ ቦላሌ “ቦላሌ” ከመሆኑ በፊት ቁምጣ ነበር። አዲስ አበባ ለትምህርት ሲመጣ ቦላሌ ሆነ። ማገብት ጠርቶት ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ሲመለስ እንደገና ወደ ቁምጣ ተለወጠ። ዳግም ወደ ቁምጣ ሲቀየር፣ ሃሳቡ ኃይለኛ ቁምጣ ሆኖ ለመቅረት ነበር። ይሁንና አንዴ ቦላሌ አንዴ ቁምጣ እየሆነ፤ ራሱን እየቀያየረ በረሃ ከረመ። የሓርነት ድርጅቱ ተለዋጭ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ደረጃም ደረሰ። ድርጅቱ በገንዘብ ጠብሽ በተቃጠለበት በአንድ ወቅት፣ የአድዋን ባንክ መዝረፍ አማረው። አምሮትም ዝም አላለም፤ ድርጅቱን ሚሊዮን በሚሊዮን የሚያደርጉ ዘራፊዎችን መረጠ።