[አንድ ለቅዳሜ] የአዲስ ርእዮተ ዓለማዊ ትንተና ጅማሮ

(ይህ ጽሑፍ ደረሰ ጌታቸው ካስነበበን መጣጥፍ ጋራ ተያይዞ ሊነበብ የሚችል ነው። ሐሳቡ ቀደም ሲልም ሲብላላ የነበረ ቢሆንም የደረሰ ጽሑፍ አንዳች ነገር እንድል አነሳስቶኛል። እንደ ወጉ ቢሆን እኔም በእንግሊዝኛ መጻፍ ነበረብኝ፤ ሆኖም ቢያንስ “አንድ ለቅዳሜ” በአማርኛ ብቻ እንድትጻፍ የተሠራውን ስርአት ማክበር አለብኝ። ባይሆን አስፈላጊ ከሆነ ወደ እንግሊዝኛ እመልሰዋለሁ።)

የማንኛውንም ማኅበረሰብ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በተለያየ መንገድ መከፋፍል እና ማጥናት ይቻላል። ከማኅበረሰቡ ክፍሎች ማንነት በመነሣት፣ አለዚያም ጎልተው ከሚንጸባረቁት ርእዮተ ዓለማዊ ልዩነቶች አንጻር ነገሩን መመልከት ይቻላል። እንደ አጥኚው ፍላጎት የሚለዋወጡ ሌሎችም ብዙ መንገዶች ይኖራሉ። በርእዮተ ዓለማዊ ልዩነት መነሻነት የሚደረገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንተና ላለፉት 40 ዓመታት የራሱን ኡደት ማድረጉ አልቀረም። ሆኖም አከፋፈሉ ማኅበረሰቡ የተቀየረውን ያህል መሻሻል አላሳየም። ምናልባት ለዚህ ችግር ቀዳሚውን ሐላፊነት መውሰድ ያለባቸው የሶሲዎሎጂ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ናቸው።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የርእዮተ ዓለም ትንተና በግርድፉ ብንቃኝ ዓለምን በበዝባዥና ተበዝባዥ መደብ ለሁለት በመክፈል ለመረዳት የሚሞክረው አመለካከት ፍጹማዊ የበላይነት ይዞ እንደቆየ እንረዳለን። በመካከል በግራ ዘመሞቹ ፓርቲዎች መካከል የነበረው ልዩነት ርእዮተ ዓለማዊ ይዘት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ቢያሳይም በመሠረቱ ግን ተመሳሳይ ነበር። ለዚህም ነው ዋናው ልዩነታቸው የትንተና ሳይሆን የስልት ሆኖ የቆየው። ኢሕአፓ፣ ሜኤሶን፣ ኦነግ፣ ህወሓት፣ ህግሓኤ/ሻእቢያ ዝርዝሩ ረጅም ነው።

አነሳሳቸው ላይ ተመሳሳይ ይመስሉ የነበሩት እነዚህ ቡድኖች በሒደት በአንዳንድ ጉዳዮች መሠረታዊ ልዮነቶችን ማሳየት ጀምረዋል። ኦነግን እና ህወሓትን የመሳሰሉት ቡድኖች በሒደት የመደብ ትንተናን ወደ ጎን እየገፉ የብሔር ትነተናን የርእዮተ ዓለማቸው ማዕከል አድርገው መንቀሳቀስ ቀጠሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያን በብሔሮች ግንኙነት እንጂ በኢኮኖሚና በታሪክ መስተጋብር ማንበብ ሙሉ በሙሉ አቆሙ። የትነተናቸው የመጨረሻ ማብቂያም የኢትዮጵያ ችግር “የቅኝ ግዛት ጥያቄ” ከዚያ መለስ ካለ ደግሞ “የብሔረሰቦች እስር ቤት”ን የማፍረስና “እስረኞቹን” ነጻ የማውጣት ሆነ። እነዚህን ቡድኖች “የግራ ጽንፈኞች” የሚሏቸው ሰዎች አሉ። በአጭሩ ሌኒንን እና ስታሊንን ሊያስንቁ የተነሱ የግራ ግራ ሰልፈኞች ነበሩ። (በነገራችን ላይ ዝነኛዋ የዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ ሐሳቧ የእርሱ [ብቻ?] እንዳልነበረች፤ ነገር ግን የዋለልኝ ብሔረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ጀርባ – አማራ የባላባት ልጅ- ጽሑፉን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ እንዳስመረጠው የሚናገሩ አሉ። የጉዳዩን የሰላ ገጽታ የሚያሳይ ታሪክ ነው።)

በተቃራኒውም የነበሩት ደግሞ በአብዛኛው የግራ ጋራ ሰልፈኞቹን ጥያቄ (የብሔር-ቅኝ ግዛት ትንተና) ከመሠረቱ በመቃወም ማንኛውም ጥያቄ በኢትዮጵያ አንድነት ማእቀፍ ውስጥ የሚፈታ መሆኑን አስረግጠው ተነሱ። ጥያቄውንም በአመዛኙ በወትሮው የማርክሲስት ትንተና ብቻ ማስተናገድን መረጡ፤ በዝባዣ-ተበዝባዥ፣ ፊውዳል-ጭሰኛ…። በአመዣኙ ኢህአፓን የመሳሰሉትን ቡድኖች እዚህ መመደብ ይቻል ይሆናል። ለዝርዝሩ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በሒደቱ የተንጸባረቁትን ልዩነቶች በስፋት እንደሚነግሩን ተስፋ አደርጋለሁ።

የዘመነ ደርግ የፖለቲካ ትንተና በአመዛኙ በዚሁ ይዘት ዘልቋል። በሒደቱ ግን አዳዳሲ እይታ ያላቸው ቡድኖች መምጣታቸው አልቀረም። ይህ ጎልቶ የታየው ደግሞ ከደርግ ውድቀት በኋል ነው። የኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል “የኢትዮጵያን አንድነት” ሲያቀነቅን የቆየው ቡድን (ከዚያ በፊት የነበሩት የአገሪቱ መሪዎች ሁሉ ማለት ይቻላል) የቆመበትን እና የሠራውን ሁሉ በማፈራረስ ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ዙሪያ መለስ የቀደመውን ርእዮተ ዓለም መሠረቶች የማፍረስ ፕሮጀክት ውስጥ ኦነግ እና ህግሓኤ (ከህውሓት ጋራ የጀመሩት የጫጉላ ሽርሽር በመሸዋወዳ እስኪጠናቀቅ ድረስ) “በየሰፈራቸው” ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ አንድነትና በብሔር ትንተና ጉዳይ ከሕወሓት/ኦነግ/ህግሓኤ ጎራ በተቃራኒ የቆሙትን ብድኖች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻል ይመስለኛል። አንደኛውና ጎልቶ የወጣው ከሞላ ጎደል የብሔር ጥያቄን ከመሰረቱ በትነተና መሣሪያነት የማይቀበልና ቀሪው ችግርም መተንተን ያለበት በኢትዮጵያ አንድነት ማእቀፍ ውስጥ ብቻ መሆኑን የሚያምን ነው። በሂደት ድምጹ መሰማት የጀመረውና የሁለቱንም ጎራዎች ቀልብ መሳብ የቻለው አመለካከት ደግሞ በሁለቱ አማካይ መስመር ላይ ለመራመድ የሚሞክር ነው፤ የብሔር ትንተናን በተወሰነ መልኩ ይቀበላል፣ “ልዩነቱ መፈታት ያለበት ግን በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ ነው” ይላል። ብዙ ጊዜ ከዚህ አመለካከት ጋራ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እየተደባለቀ የሚቀርበው ሌላው እይታ “ከሊበራሊዚም” የግለሰብ ትንተና የሚነሳ ነው። በከረረ ትርጉም ካየነው የግለሰብ ነጻነት ትንተና ለብሔር ትንተና መሠረታዊ መነሻዎች ቀጥተኛ እውቅና አይሰጥም። በምርጫ 97 እንደታየውም እነህወሓት “የግለሰብንም የብድንም መብት እናስከብራለን” የሚል አዲስ ትንተና እንዲያቀርቡ የገፋፋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ “ለየትኛው ቅድሚያ ትሰጣላችሁ?” የሚለው ጥያቄ ለሁለቱም ጎራዎች ፈታኝ ነው። ከጥቂት ፖለቲከኞች በቀር ብዙዎቹ ይህን ጥያቄ በቀጥታ አይመልሱትም፤ እርግጥ በቀጥታ መመለስ አይኖርባቸውም ይሆናል።

በመሠረቱ፣ ደረሰም በጽሑፉ እንደጠቆመው፣ እነህወሓት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ መንግሥት (ስቴት) የቆመበትን ርእዮተ ዓለማዊ መሠረት ከስሩ ለመናድ ሲነሱ በምን እንደሚተኩት አላሰቡበትም፤ መተካት እንዳለባቸውም አያምኑም ነበር። ይህ በቸር አገላለጽ ትእቢትና አለማወቅ ከመባል የዘለለ ስም ሊሰጠው የሚችል አልነበረም። አገርን ለማፍረስ አገር የቆመበትን “ትንተና” (ትምህርተ ጥቅሱ ትንተናው አፈታሪክም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ለማስታወስ ነው) ሊቀናቀን የሚችል “ትንተና” መፍጠርን ይጠይቃል። ግራ ሰልፈኞቹ ይህን አልሞከሩም አልልም። አገሪቱ ካለፈችበትና ከደረሰችበት፣ ከውስጣዊና ውጫዊ እውነታዎች አንጻር ግን “ትንተናውን” ማሻሻል እንጂ ከስሩ መናድ እንደማይቻል ወይም እንደማያስፈልግ ባለፉት 20 ዓመታት በተግባር አይተናል።

የለውጡ መጠን የሚያነጋግረን ቢሆንም  በሁለቱም ጎራዎች ርእዮተ ዓለማዊ ለውጥ መደረጉ ግልጽ ይመስለኛል። እርግጥ ለውጡ በእርግጥ ርእዮተ ዓለማዊ ነው ወይስ የስልት ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው። ለዚህ ጥያቄ ለጊዜው መልስ የለኝም።

እውነቱን ለመናገር በድኅረ አብዮት ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነጻነታቸው ተገድቦ የነበሩ ዜጎች መኖራቸው ባይካድም ሃይማኖትን የርእዮተ ዓለሙ መሠረት አድርጎ የሰበከ ፓርቲ መኖሩን እጠራጠራለሁ። በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መሠረት ባይኖራቸውም ሃይማኖትን የብሔር ትንተናው ማብላያ (ማባባሻ) አድርገው በመጠቀምም የግራ ግራዎቹ የሚደርስባቸው ያለ አይመስለኝም፤ ዛሬም ድረስ። በአጠቃላይ ግን የሃይማኖት ቀጥተኛ ተጽእኖ እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት በፖለቲካችን ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወቱ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል ማለት አይደለም። (በሌላ ጽሑፍ እንመለስበት ይሆናል።)

ብዙውን ጊዜ ስለርእዮተ ዓለም ልዩነት ሲነሳ ለውይይት የሚቀርበው የብሔር ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና የመሬት ባለቤትነት ጉዳዮች ናቸው። እርግጥ ሁለቱም የአንድን አገር መሠረታዊ ህልውና የሚወስኑ እንደመሆናቸው በቀዳሚነት መነሳታቸው ስህተት አይደለም። ምናልባትም ገና እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ገና በሚያቀራርብ መልኩ ስላልመለስን በዚሁ ተጠምደን መቆየታችን የማይቀር ነው። ይህ ግን ፖለቲከኞች ሌሎችንም የሕይወት ገጽታዎችና አማራጮች የሚተነትኑበት የተሟላ ርእዮተ ዓለማዊ መነጽር አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም። ስንት ፓርቲዎች ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፣ ስለ ግለሰባዊ ነጻነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት፣ ስለ ሕግ፣ ትምህርት ወዘተ በደፈናው ከሚነገር መፈክር መሰል “ትንተና” ባለፈ ጠለቅ ያለ ግንዛቤና ርእዮተ ዓለማዊ ትንተና እንዳላቸው አላውቅም። በጋዜጠኝነት ያነጋገርኳቸው ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ግን ገና ብዙ የሚቀራቸው መሆናቸውን መደበቅ አልችልም። “አይዞን ይሻሻላል!” ብለን እንለፈው።

አዲሱ ትንተና የታለ?

የድኅረ አብዮት ኢትዮጵያ ትውልድ አባላት እና የድኅረ ደርግ ፖለቲካ ተዋናዮች አዲሱ ሁኔታ፣ አዲስ ወይም የተሻሻሉ ርእዮተ ዓለማዊ ትንተናዎችን እንደሚሻ የዘነጉት ይመስላል። በአንድ በኩል አንድም ርእዮተ ዓለማዊ ታማኝነት የሌላቸው የፖለቲካ ደላሎች ፓርቲ እያቋቋሙ አደባባይ ሲቆሙ ማየት ስለፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን ስለማኅበረሰባችንም ብዙ ነገር ይናገራል። በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካን የምር ይዘው ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሰዎች አዲሱን እውነት በብቃት የሚተነትን እና አዲሱን ትውልድ የሚያሳምን ርእዮተ ዓለማዊ ምልከታ ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ ነው። ምሁራኑ ገና ርእሰ ጉዳዩ ሊጠና እንደሚገባውም ያስታወሱ አይመስልም፤ አለዚያም ጥናቶቻቸውን አላደረሱን ይሆናል።

በእኔ እምነት የብሔር ጥያቄ በፖለቲካው መድረክ አንኳር ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ይቆያል። ሆኖም ጥያቄው በ1960ዎቹ በተነሳበት ስሜት እና ግብ በአሁኑ ሁኔታ ትርጉሙን ያጣ አሮጌ ንትርክ ነው። ጥያቄው አግባብ ሆኖ ለውይይት የሚጋብዘውና መሠረቱ ሊሰፋ የሚችለው የኢትዮጵያ አንድነት ተቃራኒ ተደርጎ ካልቀረበ ብቻ ነው። በተቃራኒውም እውነታው ተመሳሳይ ነው። ይህ የርእዮተ ዓለምም የስልትም ለውጥን ይጠይቃል። በዚህ በኩል ኢሕአዴግም ሆኑ ሌሎቹ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች የርእዮተ ዓለም ሽግሽግ ማድረጋቸው በግልጽ የሚታይ ነው። ሽግሽጉ ከልብ ይሁን ካንጀት ለመፈተን የሚያስችል የውይይት መድረክ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ተገቢ ሽግሽግ ነው።

የዚያኑ ያህልም የብሔር ጥያቄ መኖሩን ከጅምሩ የማይቀበል ያለውን ያህል ጥያቄው መኖሩን ነገር ግን ከኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ሊፈታ እንደሚቸል የሚያምን አለ። ከዚህ በተለየ ግን የቀደመውን የመደብ ክርክር በመተው፤ በምትኩ የሊበራሊዝምን የግለሰብ ነጻነት ፍልስፍና በመተርጎም የብሔር ጥያቄን የማይቀበለው አመለካከት የበለጠ ጠንካራ ሆኖ የመውጣት አቅም ሊያገኝ ይችላል። ወቅቱ የብሔር ጥያቄ አመለካከት የፖለቲካ ስልጣን የያዘበት በመሆኑ ካልሆነ ይህ አመለካከት ዋናው ተፎካካሪ መሆኑ የማይቀር ነው። በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ ነጠላ የሊበራሊዝም ፍልስፍና ዘለላዎች ቀስ በቀስ የአገሪቱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅኝት ተቀላቅለዋል፤ ከጊዜው አኳያም በተለይ በከተሞች ለመታወቅ ችሏል። ይህም የኢኮኖሚ አማራጩንም በስፋት ለውጦታል። ኢሕአዴግ እና በአጠቃላይም የግራ ግራው ሁሉንም “በደርግነት” ቢፈርጅም ዋናው ርእዮተ ዓለማዊ ተግዳሮት እየመጣበት የሚገኘው ከሊበራሊዝም ነው (ሁሉንም በደፈናው ኒዎሌበራል እያለ የሚጠራውን የምርጫ ማጭበርበሪያ ትተነው መሆኑ ነው፤ ውሸት ስለሆነ።)

እዚህ ላይ “አማካይ” ርእዮተ ዓለማዊ አማራጫ መቅረብ/መገኘት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገራል። ተገቢም ነው። እኔም ይህን እደግፋለሁ፤ ፖለቲካ በአንድ በኩል ሙከራ ስለሆነም ጭምር። ነገር ግን ሁሉም በአማካይ ፍለጋ ብቻ መጠመድ የለበትም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ወይም የተሻለው አማራጭ አማካዩ ላይሆን ይችላልና። ለዚህም ነው በሌኒናዊ ግራ አመለካከት ታፍኖ የቆየው ፖለቲካ በመሠረቱ የተለየ የሆነውን የቀኝ/ሊበራል አመለካከት ለማስተናገድ ረጅም ጊዜና ትግል ያልጠየቀው። ከትምህርት እና ከከተሜነት መስፋፋት ጋራ የሚወለዱ አዳዲስ ፍላጎቶች ተፈጥረዋል፣ ይፈጠራሉም። ስለዚህም እነርሱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅርጽ እየሰጡ የሚተነትኑ አማራጮች ያስፈልጋሉ።

በመጨረሻ አንድ ሌላ ጥያቄ ላንሳ። ለመሆኑ “ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከርእዮተ ዓለም በላይ የህልውና ጥያቄ አለባት” ለሚሉት ሰዎች ምን ምላሽ አለ? ለካስ ይህም ራሱ ርእዮተ ዓለማዊ አቋምን ታሳቢ ያደረገ ክርክር ነው!

[በነገራችን ላይ]

ሰሞኑን ባለሥልጣናት ንብረታቸውን ማስመዝገብ መጀመራቸው ተዘግቧል። ለሌሎቹም አርአያ መሆን የሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ንብረታቸውን አስመዝግበው ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል መባሉ ተሰምቷል። እሰየው የሚያሰኝ ዜና ነው። ብዙዎች ግን ጓጉተዋል። የአቶ መለስ ንብረት ዝርዝር ምን ይሆን? መቼም የባንክ ደብተር አይኖራቸው። በስማቸው የተመዘገበ ንብረት ይኖራቸው ይሆን? ከየት አምጥተው! ሀብታቸው መጻሕፍት ብቻ ናቸው። ምስኪን። “ሲጋራ እንኳን የምትገዛለት እኮ ሚስቱ ናት” አለኝ አንድ የእርሳቸው ብጤ ምስኪን።