የአማራ ክልል ገበሬዎች በትምህርት ጥራት ጉድለት ላይ ቅሬታ አሰሙ

የአማራን ህዝብ ለዘረኛው የወያኔ ቡድን በማስገዛት ስራ የተመደቡት የብአዴን ባለስልጣናት በቅርቡ በጎንደር ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ባልገመቱት መንገድ ከአካባቢው ገበሬዎች በጥያቄ መጣደፋቸውን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች ልጆቻቸው በአግባቡ እየተማሩ እንዳልሆነ በማንሳት ምሬት ማሰማታቸው ታውቋል። ገበሬዎቹ፥ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት በቂ ትምህርት አግኝተው ስራ በመያዝ ህይወታቸው እንዲለወጥ እና የራሳቸውም ሸክም እንዲቀንስ ቢሆንም፤ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የተማሩት ልጆች ደብዳቤ እና ማመልከቻ እንኳን ሊጽፉልን የሚችሉ ሆነው አልተገኙም በሚል ስሞታ አንስተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጊዜ ማባከን በመሆኑም እቤት ቀርተው ከብቶች ቢጠብቁ እና እርሻ ቢያርሱ እንደሚሻላቸው ለባለስልጣናቱ ነግረዋል። አንዳንድ ገበሬዎች በወያኔ አገዛዝ ስር ባለው የትምህርት ጥራት ዝቅተኛነት ላይ ያላቸውን ንቀት ሲገልጹም፥ እንኳን ተማሪዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መምህራን እየሆኑ የሚመደቡት ወጣቶች እራሳቸው የመንግስት ማመልከቻ ጻፉልን ብለን ጠይቀን ባግባቡ ሊከውኑት አልቻሉም ሲሉ አውግዘዋል።

በዘረኛው አገዛዝ ስር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምሁራን በየአመቱ አገራቸውን ጥለው እንደሚሰደዱ እና የትምህርት ጥራት እጅግ ከመውረዱ የተነሳ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አንዳንድ ቅጾችን በአግባብ መሙላት እንደማይችሉ ይነገራል።