ልማታዊ ሎሌዎች
ከሙሉነህ አያሌው
ሩሲያውያን እስከዛሬ ያሳለፏቸውን የምርጫ ሂደቶች አስመልክቶ ተንታኞቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ከምርጫው ሁነት በፊት የገነቧቸውን መሰረታዊ አደረጃጀቶች ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ በሀገሪቱ ምርጫ ፖለቲካ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የሀገሪቷን የፖለቲካ መሪዎች በምርጫ ላይ ያላቸውን አቋም ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ
‹‹የምርጫዎቹ ውጤት የሚወስነው ለመፎካከር በሚቀርቡ አሳማኝ አጀንዳዎች ሳይሆን በመሰረትከው የኃይል ሚዛን ነው››፡፡
የኃይል ሚዛኑን ከምርጫው በፊት መቆጣጠር ያቃታቸው የቀድሞው የሩስያ ፕሬዚደንት ቦሪስ የልሲን ስልጣናቸውን ለፑቲን ካስረከቡ ወዲህ የፑቲን ቁማር ፓርቲው ትክክለኛውን የአካሄድ መስመር እንዲከተል አስችሎታል፡፡ ለፑቲን ፖለቲካ አመራር ጥንካሬ እና ለፓርቲው ቀጣይ የህልውና መሰረት ተደርጐ የሚወሰደው ግለሰቡ የገነባው ‹‹የሎሌነት ስርዓት›› ነው ይላሉ ለሩሲያ ፖለቲካ ቅርብ የሆኑ ተንታኞች፡፡
ልማታዊ ሎሌነት
በኢትዮጵያ ታሪክ የጥቅመኝነት ፖለቲካ በግርድፉ አሁን ያለበትን ጨምሮ የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፡፡ የመጀመሪያው ዘመን ተደርጐ የሚወሰደው ሀገራችን በዘውዳዊ አገዛዝ ትተዳደር የነበረበትን ወቅት ሲሆን በዚህም ነገስታቶቹ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በደም የሚዛመዷቸውን ግለሰቦች (Nobilities) በፖለቲካው ድጋፍ በማሰለፍ፣ ታማኝ አገልጋይ እንዲሆኑ እና ለስልጣን ማራዘሚያቸውም በሰዎቹ ዙሪያ የተገነባውን የቤተሰብነት ትስስር በአግባቡ ይጠቀሙበት የነበረው ወቅት ሲሆን ሁለተኛው ዘመን አድርገን ልንወስደው የምንችለው የአብዮቱ መፈንዳት ተከትሎ ባሉት አመታት ያለውን የጥቅመኝነት ፖለቲካ ትስስር ሂደት ነው፡፡
የሁለተኛው ዘመን ሎሌነት ከቤተሰብነት ትስስር ይወጣና ስልጣንን ለስርዓቱ ታማኝ ለሆኑ የማህበረሰብ ልሂቃን በማካፈል እነዚህን ግለሰቦች ከታቀደላቸው ወይም ከተፈቀደላቸው ኃላፊነት ውጭ ሌላ ስራ ውስጥ እንዳይገቡ በከፍተኛ ቁጥጥር ስርዓቱን በታማኝነት እንዲያገለግሉ የማድረግ ሂደት ነው፡፡
የሎሌነት ፖለቲካ ዋነኛ ግቡ ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑ፣ ጠንካራ አቋም ያላቸውን የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ልሂቃንን እና ተቋማትን በጥቅመኝነት ከትቦ ታዛዥ የማድረግ ሂደትን የሚያካትት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሀገራችን ያለው የሎሌነት ፖለቲካ ስርዓት ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ማዕከል ያደረጉ ይመስለኛል፡፡
ኢህአዴግን በበላይነት የሚመራው ከግንባሩ አንዱ የሆነው የህወሓት ፓርቲ ካለው በቁጥር አነስተኛ የብሔር ተዋፅኦ አንፃር ረጅም ጊዜ ተቀባይነቱን ሳይደበዝዝ ያለአንዳች ተገዳዳሪ በስልጣን ላይ እንዲቆይ ለማስቻል ሲባል ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ብሔሮች የሚወከሉ ልሂቃን፤ ልሂቃኑ የሚመሯቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የዚሁ ድርጅት አንዳንድ አባላትን በሎሌነት መያዝ አንዱ አካሄድ ነው፡፡
ችግሩ እነዚህ ግለሰቦች በማናቸውም ወቅት ወደ ህሊናቸው ሲመለሱ አሊያም የህዝብ ግፊት መቋቋም ሲያቅታቸው ለስርዓቱ አስጊ የመሆናቸው ጉዳይ አይቀሬ መሆን ነው፡፡ በዚህ ትንታኔ መሰረት ሊከሰቱ ይችላሉ ከሚባሉ የስርዓት ለውጥ ሙከራዎች መካከል የሆነውን ‹‹የመፈንቅለ መንግስት አልያም በአገዛዙ ላይ የሚያሳድሩት የሴረኝነት ስሜት›› አንዱ ሲሆን ይህንን ስሜት ለማደብዘዝ ሲባል የሎሌነቱን ስርዓት መዘርጋት እና መቆጣጠር በመንግስት አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የህወሓት አመራሮች ወደፊት ለሚመጣው የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች የሚወክሉ ተቋማትን እና ልሂቃንን በጥቅመኝነት ይዞ የጥያቄዎቹን በሮች አስቀድሞ መዝጋት የመጀመሪያው አማራጭ ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው የስጋት መቀነሻ አማራጭ ደግሞ ዝቅተኛ ቁጥር ያለውን የካቢኔ እና የሚኒስትሮች ውክልና ለስርዓቱ ታማኝ በሆኑት ልሂቃን በመተካት አና ሌሎች አዳዲስ አባላትን በመጨመር ሊከሰቱ ይችላሉ የሚላቸውን ስጋቶች መቀነስ ነው፡፡
ሚኒስትሮቹ ለምን በዙ?
ሊዮናርድ አሪኦላ “Patronage and political stability in Africa” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፉ ላይ ‹‹ያልተረጋጉ መሪዎች ያለባቸውን የፖለቲካ ስጋት መፍትሄ ለመስጠት ሲሉ የሹመኞችን ቁጥር ያበዛሉ›› ሲል ይሞግታል፡፡ እንደ አሪኦላ ትንታኔ ከሆነ አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች በመንግስት የከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚቀመጡ የባለስልጣናት ቁጥር ማነስ በራሱ ለስርዓቱ ከፍተኛ ስጋት ናቸው ብሎ ያምናል፡፡
ለዚህም ዋነኛው መከራከሪያ የባለስልጣኖቹ ቁጥር ማነስ በውስጣቸው ሊከሰት የሚችለውን የሀሳብ ልዩነት በእጅጉ የሚቀንስ ከመሆኑም በተጨማሪ እርስ በርስ ተናበው አቋም ለመውሰድ ጊዜ አይፈጅባቸውም ብለው እንዲያምኑ ይገፋቸዋል፡፡
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች እና በዚህ ስልጣን ደረጃ ላይ ያሉትን አስተዳዳሪዎች ቁጥር ለዚህ ትንታኔ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በሚኒስትር ማዕረግ ያሉትን ከ20 በላይ ሹመኞች ጨምሮ ወደ 48 የሚጠጉ ሚኒስትር ደኤታዎች አሉ፡፡
በአዲሱ የሚኒስትር አደረጃጀት መዋቅር ላይ ሁለት ነገሮችን በዋቢነት ማንሳት እንችላለን፡፡ ለቁጥራቸው ከፍ ማለት እንደ አንድ ምክንያት ልንወስደው የምንችለው በፊት በጥምረት የነበሩ የሚንስትር መስሪያ ቤቶች ‹‹ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስ እና ስራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል›› በሚል ለሁለት እየተከፈሉ በቀድሞዎቹ ምትክ አዳዲስ ሹመኞችን በቦታው በመተካት የቀሩትን ደግሞ እንደ ስጋታቸው መጠን እየታዩ የቀድሞውን ወንበራቸውን እንዲይዙ የተደረገበት አካሄድ ሲሆን ሁለተኛው አካሄዱን ከፖለቲካው አንደምታ አንፃር ካየነው ከሚኒስትሮቹ በታች በሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ የተሾሙት ባለስልጣናት በዋና ሚኒስትሮቹ ተቆጣጣሪነት ወደ ታች (Top-down) የሎሌነቱን ስራ ለተቀረው የበታች ሰራተኛ በኃላፊነት ስሜት በቁጥጥር እንዲይዙት ለማድረግ የሚወሰድ የእርምጃው አካል ነው፡፡
የኢትዮጵያን የሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዴኤታ አወቃቀር ከኢህአዴግ የፖለቲካ ጥንቁቅነት ባህሪ አንፃር ካየነው ሁለት አንድምታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የቁጥራቸው መብዛት በውስጣቸው ያለውን የሀሳብ ልዩነት ማስፋት ስለሚሆን፣ በሀሳብ አንድነት ምክንያት ሊነሱ ከሚችሉ ወጥ የፖለቲካ ሴራ የግንባሩን ከፍተኛ አመራሮች ለመታደግ ይጠቅማል፡፡ እዚህ ጋር ልብ ልንል የሚገባን በቁጥር የበዙት እና እንደ አዲስ የተቀላቀሉት የአመራር ልሂቃኖች ካላቸው የፖለቲካ ሎሌነት ባህሪ አንፃር ሊመረጡ እንደሚገባ መዘንጋት የለብንም፡፡
ሁለተኛው የቁጥራቸው መብዛት አንድምታ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኩትን የ‹‹ብሔር ተዋፅኦ›› ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ከሚል ነው፡፡ የባለስልጣኖችን ቁጥር በማብዛት ሹመኞቹ ቦታው ከሚጠይቀው ልምድ እና ችሎታ ይልቅ የብሔር ተዋፅኦን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል ብቻ ከአገር ጥቅም እና ደህንነት፤ ስልጣን ልዕልና (regime security) ለመጠበቅ አይነተኛ ስትራቴጂ አድርገው ይወስዱታል፡፡
የጥቅመኝነት ፖለቲካ በሁሉም ሀገራት በተመሳሳይ ሁኔታ አይሰራም፡፡ በጥቅሉ ካየነው የፖለቲካውን ስርዓት ከጥቅም ጋር አያይዞ ለረጅም አመታት ለመምራት የሚቻልባቸው ሀገራት የሚከተሉትን ባህሪያት የሚያሟሉ ናቸው፡፡
1. በኢኮኖሚ እድገታቸው በጣም ኋላ ቀር የሚባሉ ሀገራት ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ መዋዕቅር ሰጥቶ የመቀበል ደረጃ ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ ያለውን ክፍተት ገዢዎቹ ለግል ጥቅማቸው በሚጠቀሙባቸው ጊዜያት
2. የፖለቲካ ስልጣኑን ለተተኪው ትውልድ ቶሎ ቶሎ ለመቀያየር እድል በሌለበት እና በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሀገሪቷን በብቸኛ አማራጭነት ለረጅም ጊዜ ለመምራት ቁርጠኛ ሲሆን
3. በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሀገራት ውስጥ ካሉት ብዙሃኑን ከሚወክለው የብሔር ቁጥር ሳይሆን ሲቀር አልያም በብዙሃኑ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ሲያንስ
እነዚህ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኳቸው ባህሪያት የሀገሪቷ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ መገለጫ በሚሆኑባቸው ሀገራት የሎሌነት ፖለቲካ በሚገባ ይሰራል፡፡ የሀገራችን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታም ከዚህ የዘለለ አይደለም፡፡
እንዲህ አይነት አካሄድ የሚመርጡ መንግስታት በአብዛኛው የሚታወቁት ለረጅም ጊዜ ለመግዛት ካላቸው የስልጣን ጥማት አንፃር ነው፡፡
ተቋማት በማደራጀት ላይ የተመሰረተው ኢህአዴግ በጥቅሉ በስልጣን ላይ ረጅም ጊዜ ለመቆየት ሲል ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን ሁሉ የሚያስተባብር አንድ ‹‹ባለራዕይ›› መሪ (The strong man) ፤አንድ የበላይ ገዢ ፓርቲ፣ ጥቅመኛና ሎሌ ግለሰቦችን ልሂቃንን እና ድርጅቶችን፣ እንዲሁም ገጠርን መሰረት ያደረገ በግማሽ ነፃ-ኢኮኖሚ የሚያራምድ (Pro-capitalist) አስተዳደር መደላደል ፈጥሯል፡፡
ከኤፈርት ጀርባ
በሩስያ የሶሻሊስት መንግስት ማብቃት ተከትሎ አገሪቷ ወደ ምዕራቡ ካምፕ መቀላቀል ቅፅበት ላይ የተወሰዱት የማሻሻያ እርምጃዎች ጥንቃቄን የተሞሉ ናቸው፡፡ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ ትላልቅ ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ይግቡ ሲባል መጀመሪያ በፖለቲካው ተጠንቶ የተወሰነው ለማን መስጠት አለበት? የሚለው ነበር፡፡ ከዚህ መዋዕቅራዊ ጥናት በኋላ ወደፊትም ቢሆን የገዥውን ፓርቲ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሊደርሱ ይችላሉ ከሚባሉ አደጋዎች እና ከውድቀት ሊታደጉ ይችላሉ የሚባሉ ተቋማት ተመርጠው ድርጅቶቹን በኃላፊነት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በሩስያ ውስጥ በነዳጅ ማውጣት፣ በማዕድን ሀብት እና የተለያዩ የግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ባለቤቶች አብዛኞቹ ድጋፋቸው እና ጥቅማቸውን ከመንግስት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ሆኖ የምናገኘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የፓርቲው አመራሮች ለሚያስፈልጋቸው ማናቸውም ወጪ እነዚህ ግለሰቦች ከጐናቸው ይቆሙላቸዋል፡፡ እንደዚህ አይነት የ‹‹እከክልኝ ልከክልህ›› ግንኙነት እስካለ ድረስ ፓርቲው ለረጅም ጊዜ በስልጣን እንደሚቆይ እርግጠኛ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ የተመሰረተው የትግራይ ህዝብ መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ (ኤፈርት) አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ18 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በውስጡ ያቀፈው ይኸው ድርጅት በቦርድ የሚመሩት የመንግስት ባለስልጣናት ከጀርባቸው ላለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መደላድል ከዚህ ድርጅት የሚገኝ ተዝቆ የማያልቅ ትርፍ መሆኑን ይነገራል፡፡ የዚህ ድርጅት ህልውና ከትግራይ ህዝብ ይልቅ ስርዓቱን ከሚመሩት የብሔሩ ፖለቲካው ልሂቃን ጋር የተቆራኘ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ኤፈርት ካለው ተቋማዊ ይዘት እና ቀጣይነት አንፃር ኢህአዴግ እንደመንግስት እየቀጠለ ህልውናውን ካላስጠበቀለት፣ ኢህአዴግን በሚተኩ መንግስታት አስተዳደር ውስጥ የሚኖረው ተቀባይነት አጠራጣሪ ነው፡፡
ኤፈርትን በተመሳሳይ መንገድ ልናነፃፅር የምንችለው የግንባሩ ፓርቲ አባላት የሆኑ ድርጅቶች ከብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን እና የመሳሰሉት በየክልላቸው የራሳቸው ደጋፊ ድርጅቶች ያላቸው ቢሆንም የኤፈርትን ያህል እጃቸው ረጅም አይደለም፡፡ በሁሉም አይነት የንግድ ዘርፍ የመሳተፍና ራሳቸውን የማደራጀት ቀጥተኛ ነፃነት የላቸውም፡፡ እንዲኖራቸውም አይፈለግም፡፡ ይህም ህወሓትን ከሚደግፈው ኤፈርት በተሻለ ለራሳቸው ብሔር የሚኖራቸውን ተዋፅኦ በእጅጉ አሳንሷል፡፡
ኢህአዴግም ቢሆን ከሶሻሊስታዊ ደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ ከካቢኔ አባላት ታማኝነት በተጨማሪ የሀገሪቷን ዋነኛ የንግድ ሚዛን ተቆጣጥረዋል የሚባሉ ታላላቅ ባለሀብት ከጐኑ ማድረጉ የዚህ አካሄድ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ኢህአዴግ እስካለ ጊዜ ብቻ ህልውናቸው ቀጣይ እንደሚሆን የሚያምኑ ግለሰቦቹ እና ተቋማት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተበራክተዋል፡፡ ከምንም አንስቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሳቸውን ፓርቲ እስከ ደም ጠብታ ድረስ ዋጋ ሊከፍሉለት ዝግጁ መሆናቸውንም ያውቃል፡፡ እነሱም ህልውናቸው ከፓርቲው ማብቃት ጋር እንደሚያበቃላቸው ያውቋታል፡፡ ለዚህ ደረጃ መድረሳቸው ከህጋዊነቱ ይልቅ አቋራጭ መንገድ ተጠቅመው የበለፀጉበት ሀብት አንድ ቀን ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ጠንቅቀው ይረዱታል፡፡ ያለው ብቸኛ አማራጭም ኢህአዴግን እየተንከባከቡ መቀጠል ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እነዚህ የግል ተቋማት እና ድርጅቶች በግልፅ የተለያዩ ፎረሞችን በመመስረት ፓርቲውን በፋይናንስ ሲደግፉ መመልከት ችለናል፡፡ አንዳንዶቹም በግልጽ በአደባባይ ኢህአዴግ ከራሱ ውጭ ለሚገኝ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እድል መስጠት እንደሌለበት እያስገነዘቡ ይገኛሉ፡፡ የአቶ በረከት መጽሐፍ ምረቃ ወቅት ሼህ አላሙዲን ያደረጉት ንግግር ልብ ይሏል፡፡
‹‹አንዳንድ ሰዎች ኢህአዴግን ትወዳለህ ይሉኛል፡፡ አዎ እወዳቸዋለሁ፡፡ በምርጫ 97 ወቅት ከተሰደቡት ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ ሳይቸግረኝ የአረብ ሳተላይትን አስገብቼ በየቀኑ ሰዎቹን እሰማቸው ነበር፡፡ በረከትም በሩን ብርግድ አድርጐ ሰጣቸው…. እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ አብረንን ነን፡፡›› እንደዚህ አይነት ጥቅመኞችን ተንታኞቹ ‹‹ልማታዊ ሎሌ›› ይሏቸዋል፡፡
ኪራይ ሰብሳቢ
ከልማታዊ ሎሌ መርህ ትንታኔ አንፃር መንግስት የኪራይ ሰብሳቢነትን ሚና በማዕከላዊነት ይመራዋል፡፡ የዚህ ዘረፋ ተፅዕኖ በአብዛኛው የሚስተዋለው ሀገሪቷ ባላት እምቅ አቅም ላይ ነው፡፡ በተለይ መሬት፡፡ ፕ/ር መስፍን የሚሉትም ይህንኑ ነው ‹‹ኢትዮጵያ ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ ማዕድን ስለሌላት ከቡናና ከቆዳ የበለጠ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የተገመተው መሬት ነው፣ መሬትን በመሸጥ ወይም እያከራዩ ኪራይ በመሰብሰብ መበልጸግ ይቻላል ተብሎ ታስቦአል፤…….፡፡››
የኢህአዴግ አመራሮች ሌሎች ሎሌዎችን የሚቆጣጠሩበት አካሄድ አጭርና ግልፅ ነው፡፡የኪራይ ሰብሳቢነትንም ባህል በረጅም ገመድ እንደታሰረ ዶሮ ልንመስለው እንችላለን፡፡ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት በተለያዩ ህገ ወጥ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ውስጥ መጥቅም እንዲተሳሰሩ ይደረጋል፡፡ ለፓርቲው ህልውና ሲባል ግለሰቦቹ ራሳቸውን በገንዘብ ኃይል ያጠናክራሉ፡፡ የላይኛው የመንግስት ኃይሎች በዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት ውስጥ መዘፈቃቸው ከታች ላሉት ባለስልጣናት ራሱን የቻለ ምሳሌ ስለሚሆን እነርሱም የድርሻቸውን ይወስዳሉ፡፡ ለህብረተሰብ ጥቅም ሊውሉ ይገባቸው የነበሩ ዋነኛ መሰረተ ልማቶች በቅርምቱ ሳቢያ አስታዋሽ ያጣሉ፡፡
በተለይ የብሔር ፓርቲ ተወካይ የሆኑ የአመራር አባላት ለዚህ ስርዓት ይመቻቹ ዘንድ አስቀድሞ እጃቸውን በሙስና እና ተያያዥ በሆኑ በህግ ፊት ሊያስጠይቃቸው በሚችል ወንጀል ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ፓርቲውን በታማኝነት ከማገልገል ጀምሮ በወከላቸው ህዝብ ላይ አፀያፊ እና ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በታዛዥነት እንዲፈፅሙ ይደረጋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹ሳይጠሯቸው አቤት፣ ሳይልኳቸው ወዴት›› እንደሚባለው አይነት ሆነው ይሾራሉ፡፡እንዲህ ውለታ የተዋለላቸው ባለስልጣናት ከእለታት አንድ ቀን የሎሌነቱ ስርዓት አንገሸገሸን ቢሉ ‹‹የእናት ጡት ነካሽ›› ተብለው የተበላሸ ፋይላቸው ይዘረዘራል፡፡ እዚህ ጋር የቀድሞው የቤኒሻንጉል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ያረጋል አይሸሹም በሙስና ተከሰው ቃሊቲ የገቡበትን ሂደት ማስታወስ በቂ ነው፡፡
የቻይና ሞዴል?
የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ አመራር የድርጅታዊ መዋዕቅር ጥንካሬ አንዱ ግብአት የሀገሪቱ ማህበረሰባዊ አንድነት እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ ቻይና እንደ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ሀገር አይደለችም፡፡የብሄር ፖለቲካ ሳይንስ ጣጣው ዘሏቸዋል፡፡የሀገሪቱ ምሁራኖቹ አንድ ወጥ በሆነ ርዕዮተ አለም ተቀጥቅጠው የተያዙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የብሄርተኝነቱን ስሜት ከልባቸው ይደግፉታል፡፡
ለፓርቲው ህልውና ይሄው የምሁራኖቹ ሀገራዊ ፍቅር ከፍተኛ መተማመኛ ይሆነዋል፡፡ስለዚህ አንድ ወጥ በሆነ የብሄር ስብጥር ባለባቸው፤ እንደ ቻይና ባሉ ሀገራት ህብረተሰቡን ለጥቅመኝነት ፖለቲካ ተጋላጭ የሚያደርጉት ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚባሉት ምሁራን ናቸው፡፡ በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ አደረጃጀት ከተራው ግለሰብ አንስቶ እስከ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ምሁራን ወጥ በሆነ መንገድ ተንበርካኪ ያደርጓቸዋል፡፡ ይህ ነው የ‹‹ቻይና ሞዴል›› እየተባለ የሚጠራው፡፡
ኢህአዴግ በየጊዜው ከአንድ ርዕዮት አለም ወደ ሌላ በሂደት የሚለወጥ ፓርቲ ከመሆኑ አንፃር በራሱ ውስጥ የሚገኙ አመራሮች እንኳን አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ማንፀባረቅ ሲሳናቸው እንመለከታለን፡፡በአንድ ወቅት አቶ ሬድዋን ሁሴን ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲያብራሩ ‹‹የግለሰብ መብትንም ይጠብቃል›› ሲሉ ቢያብራሩም በቅርቡ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በትግራይ ሲከበር አቶ አባይ ፀሐዬ ደግሞ‹‹የግለሰብ ጥያቄ የተሸነፈ ግን ያልሞተ እይታ›› ሲሉ በውስጣቸው ያለውን የርዕዮተ አለም መደናበር አሳይተውናል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ካላት የብሄር ተዋጽኦ አንፃር ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የ‹‹ቻይና ሞዴል››ን ማውረድ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ስለዚህ የምሁራንን ተገዢነት ምሳሌ ከቻይና በመውሰድ አያይዞም የብሔር ውክልናን በመጨመር ሁለቱን በአንድ አጣምሮ የማስኬድን ሂደት ‹‹የኢህአዴግ ሞዴል›› ልንለው እንችላለን፡፡ በተለይ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ገና ምኑንም ሳይዙት የአባልነት ፎርም በማስሞላት የጥቅመኝነቱን ለጋ አካሄድ መሰረት ያስይዙታል፡፡ ጥቅመኝነቱ ደረጃውን ጠብቆ በረከቱ የሚደርሳቸው ትምህርታቸውን ጨርሰው የስራ እድል በር በፓርቲ አባልነታቸው ብቻ ተሰናድቶ ሲጠብቃቸው ነው፡፡
የልሂቃን ሎሌነት
እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት ፓርቲ አደረጃጀት ሞዴል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕቀፍም ከአጠቃላይ ህዝብ ተሳትፎ ይልቅ የጥቂት ልሂቃን ተዋፅኦ ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ የጨዋታው አድራጊ ፈጣሪም እነዚሁ አብዛኛውን ህብረተሰብ እንወክለዋለን የሚሉት ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ ማናቸውም ዘውግ ተኮር የሆኑ የፓርቲ አገዛዝ ስርአት የሚከተሉ አገራት(የኢህአዴግ አመራሮችንም ጨምሮ) የልሂቃን ሎሌነትን በሁለት አይነት መንገድ ይጠቀምበታል፡፡
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ልሂቃን የመብት ታጋዮች መሰረታዊ ፍላጐታቸው የራሳቸውን ግለሰባዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ብቻቸውን ረጅም ጉዞ ማድረግ ሲሳናቸው የሚወክሉት ህዝብ ይኖራቸው ዘንድ ወደ ተወለዱበት ስፍራ አልያም ወደ ሚመስላቸው ብሔር መሸሸግ ይመርጣሉ፡፡ ህዝቡን ከኋላ አስከትለው የፈለጉትን ማግኘት ሲጀምሩ ከታች ለዚህ ደረጃ ያበቃቸውን ህዝብ ‹‹አይንህን ለአፈር›› ማለታቸው አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው የህብረተሰቡን ችግር ከማድመጥ ይልቅ በህብረተሰቡ ውስጥ ተሰሚ ናቸው የሚባሉትን ልሂቃን ምቾት በማሟላት የሚመርጠው ኢህአዴግ፡፡
የተለያዩ ብሔሮችን እንወክላለን የሚሉ ልሂቃንን በጥቅም አስሮ ተንበርካኪ ማድረግ በተዘዋዋሪ የቀረውን ህብረተሰብ ድምፅ ለማፈን በአቋራጭነት ይጠቀሙበታለ፡፡ከዚህ በተጨማሪም በጥቅም ተሳስረው ወደ አንድ ማዕቀፍ ውስጥ የገቡት የብሔር ልሂቃኖች እርስ በርስ የሚኖራቸው ፉክክር እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ይህም የብሔር መብት፣ እታገልለታለሁ የሚሉትን የስርዓት-ብልሹነት እና የመሳሰሉትን ወደጐን የማስተው ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል፡፡ ታዋቂው የፖለቲካ ተነታኝ ሳሙኤል ሃንቲንግተን እንደሚለው ‹‹ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ እና የተረጋጋ ፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት እነዚህን ከመያዝ የተሻለ አማራጭ የለም››ብለው ስርአቱን ይቀጥላሉ፡፡