“ልማዱ ነው” – ደረጀ ሀብተወልድ
“በጎቼን ቀበሮ በላብኝ፤ድረሱልኝ…”እያለ መንደርተኛውን ሲያምስ የነበረው ውሸታሙ እረኛ፤ በስተመጨረሻ የምር ቀበሮ ሲመጣበትና የ”ድረሱልኝ”ጥሪ ሲያሰማ በመንደርተኛው፦” እሱ ልማዱ ነው”ተብሎ የሚደርስለት ጠፋ ይባላል።
ይህ ተረት በትክክል ኢህአዴግን እንደሚገልጠው፤ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች ጽፈው አንብበናል።
ይህን ነገር ያወሳሁት፤ አለመታመን፤ “ ህዘብን የማስተዳድር መንግስት ነኝ” ለሚል አካል ቀርቶ፤ ለአንድ ግለሰብም የሚኖረው አደጋ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ምሳሌ እየጠቀስኩ ለማብራራት አይደለም።
ከዚያ ይልቅ ፦“በጎቼን ቀበሮ በላብኝ” እያለ መንደርተኛውን ሲያስበረግግ እንደነበረው እረኛ፤ ኢህአዴግም እኛን በተደጋጋሚ እያስበረገገብን ስላለበት ጉዳይ ትንሽ ለማለት እንጂ።
ሁላችሁም እንደምትከታተሉት በተለየ መልኩ ካለፉት ሰባትና ስድስት ዓመት ወዲህ ውሸታሙ እረኛ(ኢህአዴግ) በተደጋጋሚ በአንድ ነገር እያስበረገገን ይገኛል-በኤርትራ። ለተረቱ ውሸታም እረኛ፤ ጎረቤትቶቹን ማስበርገጊያው “ቀበሮ” ነበረች። የአቶ መለስ ማስበርገጊያ “ቀበሮ” ደግሞ፤ ኤርትራ ነች።
ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የጥፋት ሰንሰለት መበጣጠስ አለበት…. የጥፋት ቡድኑ ኮር አስመራ ነው… በቅድሚያ ከዛው ከምንጩ ማድረቅ አለብን” በማለት ከ1998 ዓመተ ምህረት መግቢያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አቶ መለስና ኢህአዴግ በኤርትራ ላይ በትንሹ ለአስር ጊዜ ያህል የመረረ ዛቻ ሲያሰሙ ሰምተናል። እደግመዋለሁ በትንሹ።
የሩቁን ትተን ያለፈውን አንድ ዓመት እንኳ ብናይ፦
1- ኤርትራ፦አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ለማድረግ አቅዳ የላከቻቸው አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ”ተብሎ በኢቲቪ በተነገረ ሰሞን አቶ መለስ ፓርላማ ቀርበው የኤርትራ መንግስት ለዚህ ተግባሩ ዋጋውን ማግኘት እንዳለበት እየፎከሩ ተናገሩ። ክተት ለማወጅም ቃጣቸው። ህዝቡ ግን አልበረደውም፤አልሞቀውም። ይልቁንም ሆዱን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በማለት በኑሮ ውድነቱ ላይ ምሬቱን ቀጠለ።የክተቱ አጀንዳ የህዝብ ቀልብ ሊስብ አለመቻሉን ያዬት አቶ መለስም፤ በቀናት ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ-ምልልስ ሲያደርጉ፦” ኤርትራ ጋር የመዋጋት ሀሳብ የለንም። ነገር ግን ኤርትራ በምትፈጽምብን ትንኮሳ ልክ ፤ተመጣጣኝ አጸፋ እንሰጣለን።በኤርትራ ላይ ያለን ፖሊሲ ይኸው ነው” አሉ።
“የህዳሴ ግድብ”የሚል አዲስ አጀንዳ ፈጠሩ።
2- ከወራት በፊት አምባሳደር ብርሀነ ገብረ-ክርስቶስ ፤ኢህአዴግና መንግስት ‘ከእንግዲህ ለሻዕቢያን መሪዎች ያላቸው ትዕግስት መሟጠጡን’ እየፎከሩ ተናገሩ። “የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ሊረጋጋ የሚችለው፤ የሻዕቢያ መሪዎች ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ሲተነፍሱ ብቻ ነው” አሉ። አሁንም የሚበረግግ ጠፋ። ህዝቡ ፦”ውሸታሙ እረኛ ልማዱ ነው” አለ። እውነት ነው። በቀናት ውስጥ ጋዜጠኞች ፦መንግስት በኤርትራ ላይ የያዘው የተለየ አቋም እንዳለ ጠየቁ። አምባሳደር ብርሀነም፦ ኤርትራ ጥቃት ከፈፀመች፤ መንግስት ራሱን ለመከላከል አስፈላጊውን ነገር ከማድረግ ወደ ሁዋላ እንደማይል፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ቀድማ ጥቃት የመከፈት ሀሳብም፤ፍላጎትም እንደሌላት ቆጣ እያሉ ተናገሩ።”የውሸታሙ እረኛ” ነገር ሆኖ ነው እንጂ፤ የተናገሩትን ነገር ብታጤኑት ምንም ቁጣና ፉከራ አያስፈልገውምኮ።ማንም አገር ከተተነኮሰ ራሱን ለመከላከል እርምጃ ይወስዳል። እንኳን አገርን ያህል ነገር፤አንድ ህፃን ልጅም ያለጥፋቱ ሲጠቃ፤ራሱን ለመከላከል ሙከራ ያደርጋል። የሚበረግግ ካለ ተብሎ ነው በባዶው የተጮኸው።
3- ሰሞኑን የውጪ አገር ቱሪስቶች አፋር ውስጥ መገደላቸውን ተከትሎም ፦”ይህን ያደረጉት ኤርትራ ያስታጠቀቻቸው አሸባሪዎች ናቸው፤ በጥቃቱ የኤርትራ እጅ አለበት…ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራን ዝም ካለ፤ኢትዮጵያ እጆቿን አጣጥፋ አትቀመጥም!!”ወዘተ.የሚሉ ዛቻዎችና ጩኸቶች ተሰምተዋል።አሁንም ግን የበረገገ የለም።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን ይህንን የዛቻ መግለጫ አስመልክቶ ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያኖች በሰጡት አስተያዬት፦”ኢህአዴግ እንደዚህ ማለት ልማዱ ነው” ሲሉ ነው የሰማናቸው። አዎ! ውሸታሙ እረኛ፤ ውሸቱን መጮኸ ልማዱ ነው። በዚህ ዓመት እንኳ “ኤርትራን ያዙልኝ!” እያለ ሦስት ጊዜ በሀይል ጮዃል፤ወይም አልተሳካለትም እንጂ “ሀት ትሪክ” ለመስራት ሞክሯል።
ሁላችንም እንዳደመጥነው፤በነ መለስ በኩል የአሁኑ ዛቻ የተሰማው፤ሰሞኑን አፋር ውስጥ በታጠቁ ሀይሎች አምስት አውሮፓውያን ቱሪስቶች መገደላቸውን፣ሦስት መቁሰላቸውንና ሁለት ኢትዮጵያውያን መማረካቸውን ተከትሎ ነው።
በእርግጥ በቱሪስቶቹ ላይ የተፈፀመው አሳዛኝ ድርጊት፤ ሊወገዝ የሚገባው የሽብር ተግባር ነው።ይህ ብቻ ሳይሆን፤የኤርትራም ይሁኑ የኢትዮጵያ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሁኑ የአማፂ ቡድን መሪዎች፤ይህን ተግባር የፈፀሙትና ያስፈጸሙት ሀይሎች፤ በህግ ሊጠየቁና ሊቀጡ ይገባል።
ወደዚያ ለመሄድ ዋናውና በማያሻማ ሁኔታ መመለስ ያለበት ጥያቄ፦” ጥቃት የፈጸሙት ሀይሎች እነማን ናቸው?የነማንስ ናቸው?” የሚለው ነው።
ሆኖም ፤ ድርጊቱ መፈፀሙን ተከትሎ የነ መለስ ቡድን በብዙ አቅጣጫ እያሳያ ያለው ጥድፊያ ፤ ወንጀለኞቹን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ፈልጎና መርምሮ ለማግኘት የሚፈልጉ አካሎች በትክክል ወደ ወንጀለኛው እንዳያዩ የሚያደርግ ይመስላል።
በመጀመሪያ በቱሪስቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ኢቲቪ ከሁሉ ቀድሞ አወጀ። በዚሁ የዜና እወጃው ስለደረሰው የጉዳት መጠን ገና መረጃው እንዳልደረሰው እየተናገረ – ድርጊቱን የአፋር ታጣቂዎች እንደፈፀሙት ፤ከጥቃቱ ጀርባም ኤርትራ እንዳለችበት በእርግጠኝነት አሳወቀ። ነገሩ በዚህ ቢቆም፤ የተለመደ ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት እስከሆነ ድረስ ፤ወንጀለኞቹን ለመፈለግ በሚደረግ ምርመራ ላይ ይህን ያህል ተፅዕኖ ሊፈጥር አይችልም ሊባል ይቻል ነበር።ግን አልቆመም። በዚያው ዜናው ይፋ በሆነበት ቅፅበት፦”ኤርትራ ላይ እርምጃ እንወስዳለን” የሚል የውጪ ጉዳይ መግለጫ ተከተለ። የውሸታሙን እረኛ ነገር ያልተረዱ ምዕራባውያንም ፦”ሁለቱ አገሮች ዳግም ሊዋጉ ይሆንን?” የሚል ስጋት ሲያሰሙ፤ውሸታሙ እረኛ፦ “ቂቂቂቂቂ… የሚዋጋልህን በሬ ፈልግ..እንደዛ ያልኩት እየቀለድኩ ነው፤ ይልቅ ወደ አፋር ክልል ሽማግሌ ልኬ ቀሪዎቹን ታጋቾች ለማስለቀቅ እየተደራደርኩ ነው”አለና አረፈው።
በኢቲቪ፦”ጥቃትቱን ፈጽሟል” የተባለው የአፋር ህዝብ ፓርቲ “በተፈፀመው ድርጊት ማዘኑንና ድርጅቱ የዚህ ዓይነት ተግባርን እንኳን ሊፈጽመው፤እንደሚያወግዘው በመጥቀስ፤ “ከድርጊቱ ጀርባ የኢትዮጵያ መንግስት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም”የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ሲገልጽ፤ ኤርትራ በበኩሏ በኢትዮጵያ የተመሰረተባትን ክስ “የተለመደ የቅጥፈት ክስ ነው”በማለት ፤ስለጥቃቱ ምንም የምታውቀው ነገር እንደሌለ አስታወቀች።ይህ ብቻ ሳይሆን በአቶ መለስ የሚሰነዘርባትን ተደጋጋሚ ዛቻዎች አስመልክታ ኤርትራ አንድም ጊዜ የአጸፋ ምላሽ ሰጥታ አታውቅም። ግን ለምን ይሆን አንዴ እንኳ ሳት ብሏት መልስ የማትሰጠው ? እርሷም፦”ውሸታሙ እረኛ፤ ልማዱ ነው” ብላ ይሆን?
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተያያዘ ዜና፣ በሌላ በኩል… እውነትም ሆኖ ይገኝ አይገኝ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋር ህዝብ ፓርቲና በኤርትራ ላይ ያቀረበው ክስ፤ በገለልተኛ አካል ሊመረመርና ሊጣራ እንደሚገባው አምናለሁ።በአገራቸው ሰላም ያጡትን የነቢዩን መልዕክተኞች በእንግድነት በመቀበሏ ታሪክ የሚያውቃት ኢትዮጵያ፤ድንበርና ባህር አቋርጠው ሊጎበኟት የሚሄዱ ቱሪስቶችን በመግደል የምትጠቀስ አገር እንድትሆን ልንፈቅድ አይገባም።በመሆኑም ወንጀሉ በትክክል ተጣርቶ ከምንጩ ይደረስበት ዘንድ፤ ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብንዳሥሰው፣ብንጽፍበትና ብንወያይበት፤ የሚያጣራው አካል ጥሩ መነሻ ሊያገኝ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
ከላይ እንዳልኩትና ሁላችሁም እንደሰማችሁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቱሪስቶቹ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ፤ የራሱን ክስ አቅርቧል። ክሱ ሊመረመር የሚገባው እንደሆነም ጠቅሻለሁ።
ይሁንና ምርመራው ምሉዕ ይሆን ዘንድ ከኤርትራና ከአፋር ህዝብ ፓርቲ በተጨማሪ፤ ራሱ የኢትዮጵያ መንግስትም ሊመረመር ይገባል የሚል ወፍራም ጥርጣሬ አለኝ።ይህ ጥርጣሬዬ ዝም ብሎ ከጥላቻ የመነጨ ሳይሆን ፤በአገዛዙ እንደተፈፀሙ ከሰማናቸውና ሲፈፀሙ ካየናቸው ተጨባጭ ነገሮች የተነሳ ነው።
በተለይ የሚከተሉት የቅርብ ክስተቶች ጥርጣሬዬን ጨምረውታል፦
– በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ቪኪ ሀውድስተን፤ የኢትዮጵያ መንግስት ራሱ ፈንጂ በማፈንዳት-ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት ይከስ እንደነበር መግለፃቸው በዊክሊክስ ይፋ መሆኑ፣
– በምርጫ 97 ግርግር ጊዜ “በቅንጅት ደጋፊዎች በድንጋይ ውርወራ ተገደሉ” የተባሉት ስድስት ፖሊሶች -በምርመራ ጊዜ የተመቱት በጥይት ሆኖ መገኘቱ፤ ይህም ኢህአዴግ በግርግሩ ጊዜ ፖሊሶቹን ከፊት በማስቀደምና ከጀርባ በሌሎች ታማኞቹ በማስመታት ተቃዋሚዎችን ለመክሰሻ ያመቸው ዘንድ ደመ-ከልብ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ መረጃዎች መጠቆማቸው።
– አቶ መለስ በፓርላማ ቀርበው እነ አቶ አንዷለም አራጌ ‘አሸባሪዎች’ ስለመሆናቸው መናገራቸውን ተከትሎ ከተቃዋሚዎች ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው ፦” …አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ለማድረግ በማሰብ የኤርትራ መንግስት የላካቸው አሸባሪዎች መያዛቸውን ስንናገር፤ ማንም አላመነንም ነበር። እነሆ ሀቁ በተመድ አጣሪ ኮሚሸን ተረጋገጠ። አሁንም እመኑን።ያለ ማስረጃ ሰዎችን አላሰርንም…”ማለታቸው ።
ከታችኛው ብነሳ፤ አጣሪ ኮሚሽኑ እንዳለው፤ በእርግጥም የኤርትራ መንግስት ያን አድርጎት እንኳ ቢገኝ፤ አቶ መለስ በነ አንዷለም የፈጠራ ክስ ዙሪያ ለቀረበባቸው ተቃውሞ፤ የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት ለምን እንደ ማመሳከሪያ(justification)ሊመዙት ፈለጉ? የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት ። ምክንያቱም በእነ አቶ መለስ ላይ፦” በፈጠራ ትከሳላችሁ፣ታስራላችሁ፣ትገድላላችሁ” የሚል ተቃውሞ ሢሰነዘርባቸው፤ እርሳቸው እንዲያመቻቸው የጠቀሱት ይህ ክስተት፤ የመጀመሪያና ብቸኛ ጉዳይ አይደለም። ኢህአዴግ፤ ወደ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ በሀሰት ስለመክሰሱ፣ስለማሰሩና ስለመግደሉ ብዙ፤እጅግ ብዙ መልስ የማይገኝላቸው ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች ተሰምተዋል ፤እየተሰሙም ነው። ፕሮፌሰር አስራት፣አሰፋ ማሩ…እያልኩ እስከ ብርቱካን ሚዴቅሳ ድረስ፤ ያየናቸውንና የሰማናቸውን ጉዶች ልዘርዝራቸው ብል ፤ገጾች አይበቁኝም። በኢህአዴግ አገዛዝ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ ብቅ ማለት፤ለፈጠራ ከባድ ክስና እስር እንደሚዳርግ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው።ይህን ራሳቸው መለስም አሳምረው ያውቁታል። የሀሰት ምስክር እያቆሙ ስንቱን እንዳስለቀሱት ፤ ቤት ይቁጠረው። በነ አንዷለም እስር ለተነዘረው ተቃውሞ ምላሽ ሢሰጡ ግን፤ያን ሁሉ ጉድ ወደ ጎን በመግፋትና በመመፃደቅ የጠቀሷት አንዲት ምሳሌ፦ የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት ነው።እንደውም ቃል በቃል አይበሉት እንጂ የንግግራቸው ድምጸት፦ ”በኤርትራ ላይ ያቀረብነው ክስ በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ተቀባይነት ስላገኘ፤ እነ እስክንድርንና እነ በቀለ ገርባን በአሸባሪነት ብንከሳቸው ዓለም ያምነናል” ከሚል መነሻ ተነስተው እንዳሰሯቸው የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከድሮም ጀምሮ ኢህአዴግ፤እንዲህ ባለ የወረደ አስተሣሰብ ነገሮችን የሚያሰላ ቡድን ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ ሰሞኑን በቱሪስቶች ላይ የተፈጸመውስ ነገር፤ ከተመሣሳይ እሳቤ በመነሳት በራሱ በከሳሹ ቡድን ላለመፈጸሙ ምን ማረጋገጫ አለ? ፈንጂ እያፈነዳ ተቃዋሚወችን በአሸባሪነት እንደሚከስ በዊክሊክስ የተጋለጠ አካል የሚሰያሰማውን ክስ እንዴት እንመን?
ይህን ነገር ከመጫሬ በፊት ቢያንስ ከአራትና አምስት ጓደኞቼ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይቻለሁ። ሁሉም እንደኔው ኢትዮጵያውያን ናቸው።ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ በፖለቲካው መስክ ምንም ተሳትፎ የላቸውም። በጣም አስገራሚው ነገር ግን ፤በቱሪስቶች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ (የኢቲቪን ዜናና ክስ ቢሰሙም)የሁሉም ጥርጣሬ ያነጣጠረው፤ በኢህአዴግ ላይ መሆኑ ነው። ውሸታም እረኛን ማን ያምነዋል?
ባለፈው ኦክቶበር ፦ጦር መሳሪያ የጫነ የኤርትራ ሄሊኮፕተር በባይደዋ ታይቷል” በማለት የኬንያ መንግስት ክስ ማሰማቱ ይታወሳል። ከዚህ ክስ ጀርባ የኢትዮጵያ መንግስት እንዳለም ብዙዎች ያምናሉ። የተመድ አጣሪ ቡድን ባደረገው ማጣራት ግን ክሱ ውሸት እንደሆነ ማረጋገጡን ነው ያስታወቀው።
ይበልጥ ግልጽ በመሆን ነገሬን ሳጠቃልል፤ “ከዚህ ድርጊት በስተጀርባ የኤርትራ መንግስት ፈጽሞ አይኖርም”፤ ወይም “ጥቃቱ በአፋር ታጣቂዎች ፈጽሞ ሊፈፀም አይችልም “ የሚል ድምዳሜ አይደለም እየሰጠኹ ያለሁት።ከጥቃቱ በስተጀርባ ማን እንዳለና እና ጥቃቱን ማን እንደፈፀመው ሊነግረን የሚገባው፤ ተመድ ወይም ዜጎቻቸው የተገደሉባቸው አገሮች፤ ነገሩን ይመረምር ዘንድ የሚወክሉት አጣሪ አካል እንጂ ኢህአዴግ አይደለም ነው የምለው።ኢህአዴግ(ውሸታሙ እረኛ)፤ በዚህ ጉዳይ ራሱ አንድ ቀንደኛ ተጠርጣሪ እንጂ፤ከሳሽና ፈራጅ የመሆን፤ ምግባራዊም ሆነ ሞራላዊ ብቃት የለውም ነው ለማለት የፈለግኩት።
“ለራሷ ክርስትና አልተነሳች፤ልታቋቁም መጣች” አሉ እትዬ ብርቄ?