በዘር በተዋቀረ ቡድን በሚመራው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ዘግናኝ የሆኑ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው ተባለ

በዘር የተዋቀረው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር፣ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ዘግናኝ የሆኑ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ እንደሆነ በአገዛዙ ውስጥ ካሉ የግንቦት 7 ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ አመልክቷል።

የመዲናይቱ ማረሚያ ቤት አስተዳደር፥ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በስራ ላይ የዋለውን የወያኔን ዘረኛ ፖሊሲ በመከተል በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ስር ባለ አመራር እንደተሞላ መዘገባችን ይታወሳል። ዘገባው ጨምሮ እንደሚገልጸው፣ ይህ በዘር ላይ የተደራጀ አመራር፣ በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም ቆይቷል። ማረሚያ ቤቶቹ እንደ አንድ መንግስት ተቋም ሳይሆን እንደ ማፊያ ቤተሰብ ንብረት በወንዝ ልጅነት በሚደጋገፉ ግለሰቦች የሚተዳደሩ በመሆናቸውም፤ ወንጀሎቹ በማናለብኝነት፣ ያለ ጠያቂ ሲካሄዱ ከርመዋል።

የመረጃው አቀባዮች እንደሚሉት፣ በእስረኞች ላይ ከፍተኛ ድብደባን መፈጸም የተለመደ ተግባር ሲሆን፤ በድብደባው ብዛት የሞቱ፣ አካለ ጎደሎ የሆኑ እና ለአእምሮ በሽታ የተዳረጉትን ለመቁጠር ያዳግታል። በርካታ እስረኞችም ያለ ክስ በጨለማ ቤቶች ውስጥ ታጉረው የሚገኙ ሲሆን፤ በድብደባ የቆሰሉት ሆስፒታል ሄደው እንዳይታከሙ እና በቤተሰብ እንዳይጎበኙ ተከልክለዋል።

ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጽም መቆየቱ በውጭ እና አገር በቀል የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በየአመቱ እንደሚመዘገብ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በመረጃ እጥረት ምክንያት እንዲህ አይነቱ ወንጀል የሚካሄድበትን ከፍተኛ ደረጃ ለማጋለጥ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

መረጃ ማግኘትን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱም፣ የመንግስት ተቋማት በዋነኛነት የሚመሩት በችሎታቸው ህዝብን እንዲያገለግሉ በተቀጠሩ ታማኝ ዜጎች ሳይሆን በጎጥ በተዋቀሩ እና ለገዢው የማፊያ ቡድን እና ለራሳቸው ጥቅም ታማኝ በሆኑ ዘረኞች በመሆኑ እንደሆነ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።